1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአገራዊ የምክክር ጉባኤ ሃምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ መካሄድ ይጀምራል

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 6 2018

የምክክር ሂደቱ አካታችነትና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ከሂደቱ እራሳቸውን ካገለሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነውን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)ን “ከዚህ ምንም ይመጣል ብለን አንጠብቅም” በማለት በሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙትን ተመሳሳይ ሃሳብ እንጂ ልዩነት የሌላቸው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/5FL2M
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንምስል፦ Solomon Muche/DW

“ከዚህ ምንም ይመጣል ብለን አንጠብቅም” (ኦፌኮ)

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት  መግለጫ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ተስፋ የሚጠብቀው” ያሉት የአገራዊ  የምክክር ጉባኤ  የፊታችን ወርሃ ሃምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም. መዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ መካሄድ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

የምክክር ሂደቱ አሳታፊነትና ገለልተኝነት

ዋና ኮሚሽነሩ ብያንስ የሶስት ሳምንታት ያህል ጊዜን እንደሚወስድ የሚጠበቅ ያሉት  የምክክር ጉባኤው፤ ከአራት አመታት በላይ ጊዜ ከፈጀው አታካች ሂደቶች በኋላ የተደረሰበት ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኮሚሽኑ ላለፉት አራት አመታት ሲያካሄድ የቆየውንየአገራዊ ምክክር ሂደቱን “አሳታፊና አካታች” ብለው የጠሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በሂደቱ ውስጥ ቢያንስ 93 በመቶ የአገሪቱ አከባቢዎችን ለማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ “በመላው አገራችን ከሚገኙ ወረዳዎች 1ሺህ 234ቱን በምክክር ሂደቱ ማሳተፍ ተችሏል” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ይህም 93 በመቶ ያህል የአገሪቱን መላው ህዝብ እንደሚወክል ገልጸዋል፡፡ በምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት፣ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ 12 ክልሎች በ«ሰፊና ስኬታማ»ያሉት ተሳትፎ ነበረው  ነው ያሉት፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአገር ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሂደቱ ለማሳተፍ የተደረገውን ጥረት ሲኬታማ ሲሉ ነው የጠቀሱት፡፡

“የአገሪቱ ቋጠሮዎችን የሚፈታ ምክክር”

ዋና ኮሚሽነሩ በዚህ የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አከባቢዎችለዋናው ጉባኤ የሚወክሏቸውን መርጠው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ገልጸው፤ በግልጽ ሂደት ሲካሄድ የነበረ ነው ያሉት አገራዊ ምክክሩ፤ “አገሪቱ ወደፊት እንዳትራመድ ያደረጉ ቋጠሮዎችን የሚፈታ ነው” ብለዋልም፡፡ ፕሮፈሰር መስፍን፤ በሂደቱ ያጋጠሙት ተግዳሮትና ፈተናዎች ቀላል እንዳልነበርም አስረድተው፤ የነቃ ነው ያሉት የህዝቡ እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ግን ፈተናዎቹን በጥበብ ለማለፍ አስችሎታልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ “ቀጣዩ ዋናው ትኩረታችን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ጉባኤውን ማካሄድ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ መመካከርና ዘላቂ መግባባት ላይ መድረስ ነው” በማለትም በሂደቱም በህዝቦችና በመንግስት መካከል ጠንካራ መተማመን በመፍጠር ሰላም የሰፈነበት ብርቱ አገረመንግስት ለመገንባት ጽኑ መሰረት እንደሚጣል እናምናለን ብለዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

“ከዚህ ምንም ይመጣል ብለን አንጠብቅም”  (ኦፌኮ)

ኮሚሽኑ ተስፋ እንዳደረገው በምክክር ጉባኤው ሂደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮቹ ተደማምጠውና ተመካክረው አገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግራት ቁርጠኛ መግባባት ላይ ይደርሳሉ፡፡ ለዚህ ውጥን እውን መሆን ደግሞ በየደረጃው ላሉ ለሚመለከታቸው ሁሉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ይሁንና የምክክር ሂደቱ አካታችነትና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ከሂደቱ  እራሳቸውን ካገለሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነውን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)ን በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርነት የሚመሩት ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ፤ “ከዚህ ምንም ይመጣል ብለን አንጠብቅም” በማለት በሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙትን ተመሳሳይ ሃሳብ እንጂ ልዩነት የሌላቸው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የታጠቁ አካላትና ከሂደቱ ውጪ ያሉትን ስለማሳተፍ

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፤ ሀገሪቱን ከተጨማሪ መበታተን ለማዳን ብቸኛው አዋጭ መንገድ እውነተኛ እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ማካሄድ ነው የሚል ምክረሃሳብ ማስቀመጡ ይታወሳል። መሰል ውይይት በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር በጦርነት ላይ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን አካትቶ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይሎች በማሰባሰብ በድርድር ላይ ለተመሰረተ አዲስ የፖለቲካዊ ስምምንነት ፍኖተ ካርታ መሰረት መጣል በእጅጉ ያስፈልጋል ብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ ትናንት ባቀረቡት ጥሪ፤ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ያልተሳተፉ ወገኖች የምክክር ሂደቱ የመጨረሻው ወደ ሆነው ወሳኙ ምዕራፍ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ “ለዚህም ኮሚሽኑ በሩ ክፍት ነው ሲሉ” አሳስበዋል፡፡
ፖለቲከኛ ሙላቱ ለዚህም ጥሪ በሰጡት ምላሽ ግን፤ “ጥሪ አቅራቢ” ያሉት ወገኖችም ጭምር በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብለው ሳይሆን ጥሪውን ያቀረቡት “አድርገናል ለማለት ያህል ነው” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር