1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የሰባት ክፍለ ከተሞች ሥራ አስፈፃሚዎች ተሻሩ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2013

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከህውሓት ጋር በተፈጠረው ልዩነት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መነሳታቸውን ተናግረዋል። ከሁለት አመት በላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ አበበች ነጋሽ "ከአፈ-ጉባኤነት ብነሳም የምክር ቤት አባል ነኝ። በምክር ቤቱ አንድም ቀን ሳላጓድል እየተገኘሁ እንደትናንቱ ነገም አብሪያችሁ እሰራለሁ" ብለዋል

https://p.dw.com/p/3kEGC
Video Still TV Magazin The 77 Percent
ምስል DW

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የሰባት ክፍለ ከተሞች ሥራ አስፈፃሚዎች ተሻሩ፤ሌሎች ተሾሙ። የአዲስ አበባ ክፍለ-ከተሞች ባዲስ መንገድ ተዋቅረዉ ከ10 ወደ 11 ከፍ ብለዋል። በትናንትናው ዕለት የተሰበሰበው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴን አፈ-ጉባኤ አድርጎ ሾሟል። ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ከዚህ ቀደም በዚያው ምክር ቤት ያገለገሉ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው መሆናቸው በስብሰባው ተገልጿል።

በምክር ቤቱ የህወሓት አባላት እንደሚገኙ የተናገሩት የከተማው ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ሕዝባችንን ለማገልገል ከሌሎች መሳሳቦች፣አጠቃላይ ሀገራዊ ኹኔታዎችን ከማፋለስ እና ወደ ችግር ከመውሰድ እንደ ሕዝብ ተመራጭ በጋራ ሆነን፤ ህዝብን ማዕከል አድርገን ማገልገል እንዳለብን በሥልጠናዎቻችን፤ በኮንፍረንሶቻችን በተለያዩ የዝግጅት ምዕራፎቻችን ዋና ርዕስ አድርገን ስንነጋገር ነው የቆየንው። ህወሓትን ከወከሉ አባላት ጋር በዚህ ሒደት አብረን ማለፍ አልቻልንም። አመራር ማዘጋጀት አለብን። አመራር በስልጠናዎች ማለፍ አለበት" ብለዋል። 

ምክትል ከንቲባዋ አክለዉም፣ "በጋራ አስተሳሰብ እና በጋራ ተግባር ወጥ የሆነ አመራር ለመስጠት አስቸጋሪ ኹኔታዎች በሚያጋጥሙበት ሰዓት እንደ አመራር እየተተካካን፤ ከወይዘሮ አበበች ጋራም በደንብ ተነጋግረናል። አብረን እንሰራለን ቁርጠኝነታቸውን እናውቃለን። በጣም ነው የምናከብራቸው ነገር ግን ቅድም ባልኩት ማዕቀፍ ውስጥ ከማለፍ ጋራ አጠቃላይ የጋራ አመራር ላይ ክፍተቶች እየፈጠርን ሄዶ ጉዳቱ ሕዝብ ላይ ከሚያርፍ ሁላችንም ማገልገል በምንችልበት ሁኔታ መሔዱ መልካም ስለሆነ" የቀድሞዋ አፈ-ጉባኤ እንደተቀየሩ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። 

ወይዘሮ አበበች "ምንም እንኳ ከአፈ-ጉባኤነት ብነሳም የምክር ቤት አባል ነኝ። የምክር ቤት አባል ስለሆንኩኝ ፤ በምክር ቤቱ አንድም ቀን ሳላጓድል እየተገኘሁ፤ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን እያቀረብኩ ወደ ታች ወርጄ ሕዝቤን እየደገፍኩ እንደትናንቱ ነገም አብሪያችሁ እንደምሰራ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ" የሚል ንግግር አሰምተዋል። 

የአዲሷ አፈ-ጉባኤ ሹመት በ76 ድጋፍ በሰባት ድምጸ ተዓቅቦ፣ ያለምንም ተቃውሞ ጸድቋል። በዚሁ የምክር ቤቱ ስብሰባ የቀድሞው የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ «የከተማው ስራ አስኪያጅ" ሆነው ተሾመዋል። የቤቶች ልማት፣ የኮንስትራክሽን፣ የፕላን ኮሚሽን፣ የመሬት ልማት አስተዳደር፣ የኢንዱስትሪ፣ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ እና የገቢዎች ቢሮዎች ሹመቶችም ጸድቀዋል።  

የልደታ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ አራዳ እና የካ ክፍለ ከተሞች ሥራ አስፈፃሚዎች ከኃላፊነታቸው ተነስተው በአዲስ ተተክተዋል። የአዲስ ከተማ፣ የቂርቆስ እና የቦሌ ክፍለ ከተሞች ሥራ አስፈፃሚዎች በያዙት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ተወስኗል። 11ኛ ክፍለ ከተማ ሆኖ አዲስ የተቋቋመው የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማም ሥራ አስፈፃሚ ተሾሞለታል። 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሰራጨው መረጃ እንደሚጠቁመው ለሚ ኩራ  ከነባሮቹ ቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ተቀንሶ የተዋቀረ ነው።