1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረት በናይል ወንዝ ላይ የያዘው አቋምና ኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2014

በናይል ውኃ አጠቃቀም የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ የታዛቢነት ሚና ያለው የአውሮፓ ሕብረት የወንዙን የውኃ አጠቃቀም በተመለከተ ከሰሞኑ ለግብጽ ያደላ አቋም ማራመዱን ኢትዮጵያ አጣጣለች። ከሰሞኑ ውይይት ያደረጉት የአውሮፓ ሕብረት እና ግብጽ የናይል ውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ባወጡት የጋራ መግለጫ ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ማራመዳቸው ታዉቋል።

https://p.dw.com/p/4D8vG
Äthiopien Hawassa | Ambassador Dina Mufti
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫ

 
በናይል ውኃ አጠቃቀም የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ የታዛቢነት ሚና ያለው የአውሮፓ ሕብረት የወንዙን የውኃ አጠቃቀም በተመለከተ ከሰሞኑ ለግብጽ ያደላ አቋም ማራመዱን ኢትዮጵያ አጣጣለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሳምንታዊ መግለጫው እንዳስታወቀው ከሰሞኑ ውይይት ያደረጉት የአውሮፓ ሕብረት እና ግብጽ የናይል ውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ባወጡት የጋራ መግለጫ ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ማራመዳቸውን ከቃል አቀባይነት ኃላፊነታቸው የተነሱት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።
የአውሮፓ ሕብረት "የግብጽ የውኃ ደህንነት በፍፁም መነካት የለበትም ፣ አይነኬ ነው በሚል ወደ አንድ ወገን ያጋደለ የገለልተኝነት ሥሜት የሌለው መግለጫ አውጥቷል" ሲሉ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም የታችኞቹን የተፋሰሱን አገሮች ያለመጉዳት ፖሊሲዋን አጥብቃ እንደምትከተልና ከተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብር መሥራቷን ትቀጥላለችም ብለዋል።
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻሉን ጠቅሰው በጥሬ ገንዘብና በነዳጅ እጥረት ምክንያት ለተጎጅዎች ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ ስለመሆኑ መናገራቸውን የተጠየቁት ዲና " ለትግራይ ሕዝብ ከ እኛ የበለጠ የሚቀርበው የለም። ለዚህ ሕዝብ ሰቆቃና ችግሩ መድረስ የመጀመርያ የሞራልም፣ የፖለቲካም ፣ የሁሉ ኃላፊነት ያለው እኛ ጋር ነው በሚል ሒሳብ እየተሠራ ነው" ብለዋል።
ቻይና ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ የመመደባቸውን መነሻ እና ፍላጎት በተመለከተ ሲመልሱ " ጉዳዩ ነው የሳባቸው። በቀጣናው ካለው ችግር እና ለቀጣናው ከሚሰጡት ግምት አንፃር ነው" ብለዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል ዐቀባይ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው ላለፉት ሁለት ዐመታት ያገለገሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይህንን ኃላፊነታቸውን በቅርቡ በኬንያ የአምባሳደርነት አገልግሎታቸውን አጠናወው ለተመለሱትና ለዚሁ ሥራ የበላይ ኃላፊ ሆነው ለተሾሙት አምባዳደር መለስ አለም ያስረከቡ ሲሆን እሳቸው በዚያው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው መሾማቸውንም ጋዜጠኞችን ለነበራቸው መልካም የሥራ ግንኙነት አመስግነው በተሰናበቱበት የመጨረሻው የዛሬው መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።


ሰለለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ