1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ምክር ቤት በዩክሬን ጦርነት የደረሰ ጉዳት ሊመዘግብ ነው

ሐሙስ፣ ግንቦት 10 2015

የአውሮፓ ምክር ቤት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ምዝገባ በይፋ ሊጀምር ነው ። በ18 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰየመው ምክር ቤቱ የጦርነቱን ጉዳት መዝግቦ ማስቀመጥ የሚያስችል ውሳኔ ሲያሳልፍ ቱርክን ጨምሮ ስድስት አባል ሀገራት ግን ለጊዜው ከውሳኔው ራሳቸውን አግልለዋል።

https://p.dw.com/p/4RXm3
Themenpaket - Ukraine - Zerstörung - Minenräumung - Europa-Rat Gipfel in Reykjavik
ምስል Alastair Grant/AP/picture alliance

የአውሮፓ  ምክር ቤት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ምዝገባ በይፋ ሊጀመር ነው ። በ18 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰየመው ምክር ቤቱ የጦርነቱን ጉዳት መዝግቦ ማስቀመጥ የሚያስችል ውሳኔ ሲያሳልፍ ቱርክን ጨምሮ ስድስት አባል ሀገራት ግን ለጊዜው ከውሳኔው ራሳቸውን አግልለዋል። አባል ሀገራቱ በውሳኔያቸው ለዩክሬን ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ፣ ከሩስያ አንጻር በአንድነት መቆማቸውን፣  ብሎም ሩስያ በጦርነቱ ዩክሬን ላይ ላደረሰችው ውድመት ተጠያቂ እንድትሆን ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል። በምዝገባው  ዩክሬን ለደረሰባት ውድመት ካሳ ማግኘት የምትችልበትን መንገድ ከማመቻቸት በተጨማሪ ሃሳቡን ወደ መንግታቱ ድርጅት በመውሰድ የውሳኔ ሃሳብ ሆኖ እንዲቀርብ ማስቻል እንደሚገኝበትም  ጉባኤው በሪክያቪክ አይስላንድ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ሲጠናቀቅ ይፋ ተደርጓል። ምክር ቤቱ በበላይነት የሚመራው  የጦርነት ጉዳት መዝጋቢ መቀመጫውን ዘሄግ ኔዘርላንድስ በማድረግ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ የደረሱ ውድመቶች ፣ ሞት እና የአካል ጉዳትን ለይቶ እንደሚመዘግብ ተገልጿል። 
ጉባኤውን ያስተናገደችው ሀገር  አይስላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ካተሪን ያኮብስዶቲር አብዛናው ጉባኤተኛው ለውሳኔው ጽኑ አቋም መያዙ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። 
«ሁሉም አባል ሀገራት አለመፈረማቸው አላስገረመኝም ። ነገር ግን አብዛኛው የምክር ቤቱ አባል ሀገር የውድመት ምዝገባውን ተቀብለው በመፈረማቸው ተደስቻለሁ»
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በጉባኤው ላይ ይህንኑ የዋና ጸሐፊዋን ንግግር ባጠናከረ ንግግራቸው  ሩስያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ እና ላደረሰችው «ጭካኔ» የተሞላ ጥፋት ተጠያቂ እንድትሆን አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።

«የአውሮጳ ምክር ቤት  ጥረት በዩክሬን እየተደረገ ባለው ጦርነት ያስከተለውን አስከፊ ውድመት ለመመዝገብ እና ሩስያ ላደረሰችው በጭካኔ የተሞላ ድርጊት በዓለምአቀፍ ደረጃ ተጠያቂ እንድትሆን ለማድረግ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው። »

ኦላፍ ሾልስ በዚሁ ጊዜ ለሶስት ዓመት ይቆያል ለተባለው የምክር ቤቱ የምዝገባ ስራ የሚውል ሀገራቸው የ10 ሚሊዮን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዴኔሽ ሚካኤል የጦርነት ጉዳት ምዝገባው በዩክሬን ለደረሰው ጥፋት ፍትህ ለማንገስ የማዕዘን መሰረት ነው ብለዋል። 
ቱርክ ሃንጋሪ እና ሰርቢያ በበኩላቸው በምዝገባው እንደማይሳተፉ በመግለጽ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል። 
ምክርቤቱ በጦርነት ጉዳት ምዝገባው በሩስያ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ስለመመዝገብ አለመመዝገቡ ያለው ነገር የለም።
ዩክሬን በጎርጎርሳውያኑ 1995 ነበር የምክር ቤቱ አባል የሆነችው ። የምክር ቤቱ አባል የነበረችው ሩስያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ስትታገድ፤ ሌላዋ የሩስያ አጋር ቤላሩስ ደግሞ በምክር ቤቱ የታዛቢነት ሚና ተወስና እንድትቀር መደረጉን የጀርመን ዜና ምንጭ ዘገባ ያመለክታል። 
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከምክር ቤቱ ጉባኤ ጎን ለጎን ሃገራቱ ለዩክሬን የጦር አውሮፕላኖች ማቅረብ በሚያስችል ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል። በዚህም ብሪታኒያ እና ኔዘርላንድስ ለዩክሬን የጦር አውሮፕላን እንዲቀርብ ዓለማቀፍ ጥምረት ለመፍጠር ጥረት ጀምረዋል። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ የዴሞክራሲ ጠንቅ እና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያደርጉ ባሏቸው ሃገራት ላይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ በገለጹበት ንግግራቸው  ። 
«እንደኛ ያለ ዴሞክራሲያዊ ተቋም እንዳይገነባ እና እንቅስቃሴያችንን ለመግታት ብሎም አለመረጋጋት እንዲሰፍን የሚያደርጉ አካላትን መታገል እንድንችል ልንጸና ይገባል። »
ከዩክሬን እና ሩስያ ጋር በተያያዘ ዜና የአውሮጳ ምክር ቤት አባል ሃገራት ስብብሰባቸው እያካሄዱ ባለበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው ምክር ቤት ሩስያ እና ዩክሬንን የሚመለከት ችሎት እንደሚሰይም አስታውቋል።  ሩስያ በጎርጎርሳውያኑ 2014 በኃይል በያዘቻት የክሬሚያ ግዛት በአናሳ ጎሳዎች ላይ አድልዎ ትፈጽማለች፤ በግዛቲቱ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ትደግፋለች ስትል ዩክሬን ትከሳለች። 
ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ