1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጉባኤ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 15 2012

መጀመሪያ ላይ ለመሪዎቹ የቀረበውን የ500 ቢሊዮን ዩሮ  እርዳታ ምክረ ሃሳብ የሰሜን አውሮጳዎቹ ሃገራት ኔዘርላንድስ ኦስትሪያ ስዊድን ዴንማርክና ፊንላንድ በመቃወማቸው ወደ 390 ቢሊዮን ዩሮ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። አምስቱ  ባለጸጋ ሃገራት ብሩ በዛ ሲሉ ለማስቀነስ በልዩ ጉባኤው ላይ ብዙ ተሟግተዋል። 

https://p.dw.com/p/3ferg
Belgien PK Abschluss EU-Gipfel
ምስል Reuters/J. Thys

የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጉባኤ ፍጻሜ 

 ዛሬ ማለዳ ያበቃው የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ልዩ ጉባኤ ከእስከዛሬዎቹ ረዥም ጉባኤዎች አንዱ ነው። በአጠቃላይ 90 ሰዓታት የወሰደው ይኽው አወዛጋቢ ጉባኤ በስምምነት ነው የተጠናቀቀው።መሪዎቹ በኮቪድ 19 ክፉኛ ለተጎዱት ሃገራት ግዙፍ የእርዳታና የብድር ማዕቀፍ ላይ ነው የተስማሙት። ለበጀትና የኮሮና ተህዋሲ ላደረሰው ጉዳት ማገገሚያ የሚውል 1.8 ትሪሊዮን ዩሮ ወይም 2.1 ትሪልዮን ዶላር አጽድቀዋል።ከዚህ ውስጥ 750 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 858 ቢሊዮን ዶላር በኮሮና ተህዋሲ ለተጎዱ ሃገራት የኤኮኖሚ ማገገሚያ የሚከፋፈል ሲሆን ቀሪው ገንዘብ ደግሞ የህብረቱ የሰባት ዓመት በጀት ነው።ይሁንና መሪዎቹ አግባቢ ስምምነት ላይ የደረሱት ለሁለት ቀናት የታሰበው ጉባኤ በሁለት ቀናት ተገፍቶ ምናልባትም ክልተስማሙ ለሌላ ጊዜ ይተላለፋል ከተባለም በኋላ ነበር ።በዙር የሚደርሰው የወቅቱ የአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አግባቢ ሃሳብ ላይ መድረሱ ቀናት ቢወስድም ዋናው ነገር መስማማታችን ነው ሲሉ ውጤቱን አወድሰዋል።
አራት ቀንና ሌት የተካሄደው ጉባኤ«በዚህ ስምምነት ለሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት የአውሮጳ ህብረትን የገንዘብ ድርጅቶች መንገድ ጠርገናል፤ከዚሁ ጋርም ከአውሮጳ ህብረት ምሥረታ በኋላ ለገጠመን ታላቅ ቀውስ ፣በመልሶ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ መልክ ፣መልስ ሰጥተናል።ይህ ቀላል አልነበረም።ብዙ ቀናትም መውሰዱም የሚያሳየው ከተለያዩ አቅጣጫዎች መምጣታችንን ነው ።ሆኖም ለኔ ዋናው ነገር በስተመጨረሻ አንድ መሆናችንና ሁላችንም አንድ ነገር መሥራት እንዳለብን አምነን መስማማታችን ነው።»
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮም በጉባኤው ውጤት ረክተዋል።ስምምነቱንም ታሪካዊ ብለውታል።
«የጋራ የእርዳታና የብድር መርሃ ግብር ስናዘጋጅ እና በአንድ ላይም ዋስትን ስንሰጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።አንዳችን በሌላችን ላይ እጅግ አድርገን መተማመናችንም በታሪክ ልዩ ቦታ የሚይዝ ነው።ሃያ ሰባታችንም በአንድ ጠረጴዛ ላይ የጋራ ቤታችንን ፈጥረናል።በየትኛው የዓለም ፖለቲካ ነው ይህ እውን ማድረግ የሚቻለው ?በየትኛውም!»
የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሻርልስ ሚሼል በበኩላቸው ስምምነቱን ለአውሮጳ ትክክለኛውና በትክክለኛው ጊዜ የተፈጸመ ሲሉ ገልጸውታል።
«እርግጥ ነው ድርድሩ ለሁሉም አውሮጳውያን በጣም አስቸጋሪ ነበር።የተካሄደውም በጣም አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ላይ ነበር።በጥድፍያ የተካሄደ ግን ለ27 ቱም አባል ሃገራት የተሳካ ውጤት ያስገኘ ጥሩ ስምምነት ጠንካራም ውል ነው።ከምን በላይ ደግሞ ትክክለኛ እና በትክክለኛውም ጊዜ የተከወነ ስምምነት ነው።»
ባለፈው ታህሳስ በቻይና ተከስቶ በፍጥነት ዓለምን ባዳረሰው በኮሮና ወረርሽኝ ከ14.7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተይዟል።የሞተው ደግሞ ከ610 ሺህ በላይ ነው። በሽታው ክፉኛ ካጠቃቸው ክፍለ ዓለማት የ500 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነችው አውሮጳ አንዷ ናት።በክፍለ ዓለሙ በኮቪድ 19 ሕይወቱ የተነጠቀው ቁጥር 135 ሺህ ነው።በሽታውን ለመቆጣጠር በተወሰዱ የመከላከያ እርምጃዎች ሰበብ አገልግሎት መስጠት ያቋረጡ በርካታ ድርጅቶች ከስረዋል።በርሳቸው ይተዳደሩ የነበሩ ሠራተኞችም ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል።ኮሮና ላደረሰው ለዚህ የኤኮኖሚ ጉዳት ማገገሚያ ከተመደበው 750 ቢሊዮን ዩሮ  ውስጥ 390 ቢሊዮን ዩሮው የማይከፈል እርዳታ ነው። መጀመሪያ ላይ ለመሪዎቹ የቀረበውን የ500 ቢሊዮን ዩሮ  እርዳታ ምክረ ሃሳብ የሰሜን አውሮጳዎቹ ሃገራት ኔዘርላንድስ ኦስትሪያ ስዊድን ዴንማርክና ፊንላንድ በመቃወማቸው ወደ 390 ቢሊዮን ዩሮ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው መሪዎቹ አግባቢ ስምምነት ላይ የደረሱት እንዲህ በቀላሉ አልነበረም።አምስቱ  ባለጸጋ ሃገራት ብሩ በዛ ሲሉ ለማስቀነስ በልዩ ጉባኤው ላይ ብዙ ተሟግተዋል። 
ኮቪድ 19 ያደቀቀው የአውሮጳ ኤኮኖሚ እንዲያንሰራራ ከታቀደው ከዚህ የእርዳታና የብድር መርሃ ግብር ዋነኛ ተጠቃሚዎች ኮሮና በርካታ ዜጎቻቸውን የገደለባቸውና ኤኮኖሚያቸውንም ያሽመደመደባቸው ስፓኝና ኢጣልያ ናቸው።ስፓኝ 140 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 160.17 ቢሊዮን ዶላር እርዳታና ብድር ጸድቆላታል።ከዚህ ውስጥ 72.7 ቢሊዮን ዩሮው እርዳታ የተቀረው ደግሞ የሚከፈል ብድር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ዛሬ ተናግረዋል።ሳንቼዝ ለአውሮጳም ለሃገራቸው ለስፓኝም ታላቅ ያሉትን ስምምነት  አውሮጳ ነገን ከእይታ ሳታስወጣ ለኮቪድ 19 ቀውስ መሠረታዊ ምላሽ ያስቀመጠችበት ብለውታል። ሌላው የእርዳታው ተጠቃሚ ብዙ ዜጎቿን ኮቪድ የገደለባት ኢጣልያም 150 ቢሊዮን ዩሮ ታገኛለች።ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጁሴፔ ኮንቴ ገንዘቡን ኢጣልያን ወደ ቀደመው ሁኔታ ለመመለስ ይውላል ብለዋል።
«አሁን ታላቅ ሃላፊነት አለብን። 150 ቢሊዮን ዩሮውን ኢጣልያን ጠንካራ ለማድረግና ወደነበረችበት ለመመለስ እንጠቀምበታለን»
ፈረንሳይ ለኤኮኖሚ ማነቃቂያ ከታቀደው እርዳታ 40 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 45.81 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ የገንዘብ ሚኒስትሯ ብሩኖ ለማሪ አስታውቀዋል።ብሩኖ መንግሥታቸው የኤኮኖሚ መነቃቂያውን ዝርዝር ጉዳዮች ከአንድ ወር በኋላ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።ለየሃገራቱ እንደ የችግራቸው ስፋትና መጠን ታስቦ ይከፋፈላል የተባለው እርዳታና ብድር አሰጣጥ እንዴት ነው?የብድሩ አከፋፈልስ ገበያው 
መሪዎቹ ዛሬ የተስማሙበት ይህ የእርዳታና የብድር መርሃ ግብር ሥራ ላይ እንዲውል በአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ፓርላማ መጽደቅ ይኖርበታል።27ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች በጋራው ብድርና እርዳታ ላይ በሁለት ቀናት መስማማት ተስኗቸው ለተጨማሪ ሁለት ቀናት ከተወያዩ በኋላ ለሁሉም የሚበጅ አግባቢ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ብዙ አስተምህሮት አለው

Belgien Abschluss EU-Gipfel
ምስል Reuters/S. Lecocq
EU-Gipfel Coronavirus | Angela Merkel
ምስል Reuters/F. Lenoir
Belgien I EU-Gipfel in Brüssel
ምስል Reuters/Pool/J. Thys

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ