1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት የስደተኞች መርህ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 19 2010

የእሁዱ ጉባኤ ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እጅግ አስፈላጊ ነበር። የፓርቲያቸው « የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት»፣ እህት ፓርቲ «የክርስቲያን ሶሻል ህብረት» ሜርክል ለችግሩ የጋራ መፍትሄ ማምጣት ካልቻሉ የጊዜ ገደብ ሰጥተው ከዚያ በኋላ የተናጠል እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ የፓርቲው ሊቀ መንበር ኽርስት ዜሆፈር ዝተዋል።

https://p.dw.com/p/30L5i
EU-Minigipfel
ምስል picture alliance/AP Photo/Y. Herman

የአውሮጳ ህብረት የስደተኞች መርህ

የአውሮጳ ህብረት በስደተኞች ጉዳይ ላይ በአባል ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ እየጣረ ነው። በዚህ ሳምንት ሐሙስ ብራሰልስ ቤልጅየም የሚካሄደው የአባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ ከሚነጋገርባቸው ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛው ይኽው የስደተኞች ጉዳይ ነው።  ከዚህ ጉባኤ አስቀድሞ  16 አባል ሀገራት ባለፈው እሁድ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደዋል። 

የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ስደተኞች ከሰሜን አፍሪቃ እና ከቱርክ በተለያዩ ጀልባዎች በብዛት ወደ አውሮጳ መሰደድ ከጀመሩበት ከዛሬ ሦስት ዓመት ወዲህ ጥልቅ መከፋፈል ውስጥ ነው የሚገኙት። በስደተኞች የተጨናነቁት ኢጣልያ ግሪክ እና ማልታን የመሳሰሉት የህብረቱ ደቡባዊ ድንበር ሀገራት ሸክማችንን ተጋሩን ሲሉ ለአባል ሀገራት ጥሪ ቢያቀርቡም ምላሹ አዝጋሚ እና ተሰፋ አስቆራጭ ሆኖ ነበር የቆየው። የአውሮጳ ህብረት ችግሩን ያቃልላል በሚል አባል ሀገራት በርካታ ስደተኞች ይገኙባቸው ከነበሩት ከነዚህ ሀገራት ሊወስዱ ይገባቸዋል ያለውን የስደተኞች ቁጥር የመደበበትን የኮታ ስርዓት አውጥቶ ነበር። ይህን ተግባራዊ ያደረጉት ግን ጥቂት ብቻ ናቸው። የኮታ ስርዓቱን የተቃወሙት በተለይ ሀንጋሪ ፣ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ስሎቫክያን የመሳሰሉ ሀገራት እስካሁንም በዚሁ አቋማቸው እንደጸኑ ነው። አሁን ደግሞ ኢጣልያ እና ማልታን የመሳሰሉ ሀገራት በፈንታቸው የጀልባ  ስደተኞች አናስገባም ማለት ጀምረዋል። አንድ የግብረ ሰናይ ድርጅት የህይወት አድን መርከብ የታደጋቸውን ስደተኞች የጫነች መርከብ በኢጣልያ እና በማልታ እምቢተኝነት እና ፉክክር ለቀናት በሜዴትራንያን ባህር ላይ እንድትቆይ መደረጓ አንዱ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው። የአውሮጳ ህብረት በወቅቱ ሁለቱም ሀገራት የሰዎችን ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ እንዲሰጡ ቢጠይቅም ጥሪው ሰሚ አላገኘም ነበር። ችግሩ ግን በስተመጨረሻ ስፓኝ ስደተኞቹን ለማስገባት ፈቃደኛ በመሆንዋ ተፈቷል። እነዚህ እና ሌሎችንም የህብረቱን አባል ሀገራት የማያስማሟቸው ጉዳዮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እያሰፋ ሄዷል።  ጀርመንን በመሳሰሉ  መንግሥታትም ላይ ጫና እያሳደረ ነው። ይህ መነሻ ሆኖም የፊታችን ሐሙስ እና አርብ ከሚካሄደው የአባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ ባለፈው እሁድ  አነስተኛ ጉባኤ ተካሂዷል። በስደተኞች ጉዳይ በእህት ፓርቲያቸው አጣብቂኝ ውስጥ በገቡት በጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አሳሳቢነት የህብረቱ ኮሚሽን የጠራው እና 16 አባል ሀገራት የተሳተፉበት ይህ ጉባኤ ሜርክል እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት ያስችላሉ በተባሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምቷል።

Belgien Brüssel - Angela Merkel und Jean-Claude Juncker
ምስል Reuters/Y. Herman

«ሁላችንም ህገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ፣ ድንበሮቻችንን ለመጠበቅ እንደምንፈልግ ተስማምተናል።  ሁላችንም ለሁሉም ጉዳዮች ሃላፊነት እንወስዳለን። አንዳንዱ የመጀመሪያው የስደት ጉዳይ ተጋላጭ ሌሎች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የችግሩ ተጋሪ መሆን የለባቸውም። ለሁሉም ነገር ሁሉም ሃላፊነት መውሰድ አለበት። በሚቻለው ቦታ ሁሉ አውሮጳዊ መፍትሄ እንሻለን። በማይቻልበት ጊዜ ደግሞ ፈቃደኛ የሆኑትን በአንድ ላይ አሰባስበን የጋራ የድጋፍ ማዕቀፍ እንፈልጋለን።»   

Horst Seehofer, Angela Merkel
ምስል picture alliance/dpa/P.Kneffel

የእሁዱ ጉባኤ ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እጅግ አስፈላጊ ነበር። የእሁዱ ጉባኤ ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እጅግ አስፈላጊ ነበር። የፓርቲያቸው « የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት»፣ እህት ፓርቲ «የክርስቲያን ሶሻል ህብረት» ሜርክል በስደተኞች ጉዳይ ላይ አንድ የጋራ መፍትሄ ማምጣት ካልቻሉ የጊዜ ገደብ ሰጥተው ከዚያ በኋላ የተናጠል እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ የፓርቲው ሊቀ መንበር ኽርስት ዜሆፈር ዝተው ነበር።  የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም የሆኑት ዜሆፈር ፣ሜርክል የተባሉትን ካላደረጉ ሥልጣናቸውን በመጠቀም በሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት የስደት ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ወይም ከዚህ ቀደም ተገን እንዲሰጣቸው ጠይቀው የተከለከሉ ስደተኞች ወደ ጀርመን እንዳይገቡ ያወጡትን እቅድ ተግባራዊ አደርጋለሁ ሲሉ  ነበር ያስፈራሩት። ሜርክል ችግሩ በአጠቃላይ በአውሮጳ አቀፍ ደረጃ መፈታት አለበት የሚል አቋም ነው ያላቸው። እንደ ሜርክል አውሮጳ አቀፍ የስደተኞች ፖሊሲ ሲነደፍ ነው የጀርመንም ችግር የሚወገደው። ሂደቱን በቅርብ የሚከታተለው የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው የእሁዱ ጉባኤ የአውሮጳ ህብረት ተጨማሪ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ የሚከላከል በጀርመንም የሰፈነው ውጥረት እንዲረግብ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ጉባኤውም በጥቅሉ በልዩነት አንድነትን ይዞ የመቀጠል ስምምነት ላይ ነው የደረሰው

ስደተኞችን ከሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት አንወስድም በሚለው አቋማቸው የፀኑት  ሀንጋሪ ፣ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ስሎቫክያን የመሳሰሉ ሀገራት በጉባኤው ላይ አልተገኙም። እናም አባል ሀገራት በሙሉ የሚስማሙበትን የጋራ የስደተኞች መርህ ማምጣት እንዳልተቻለ በእሁዱ ጉባኤ ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል። ይህን እና ሌሎች አገራትም የሚያሳዩትን የተናጠል እርምጃ የመውሰድ አዝማሚያ ለማስቀረት ከሚስማሙት ጋር በሚስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ነው ግንዛቤ የተወሰደው እንደ ገበያው።

EU-Sondertreffen in Brüssel
ምስል picture alliance/dpa/G. Van den Wijngaert

ከእሁዱ ጉባኤ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሜርክልና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮም በርሊን ውስጥ በጉዳዩ ላይ መክረው ነበር። ማክሮ ሥልጣን እንደያዙ ያቀረቡትን የጋራ የስደተኞች ማዕከል የማቋቋም ሀሳብ በዚሁ ወቅት አንስተው ነበር። የብዙዎች ድጋፍ ያለው የሚመስለው ይሄ ሃሳብም ሆነ  ሀገሪቱ ያወጣችው አዲስ የስደተኞች ጉዳይ ህግ በተለይ ለስደተኞች ተስፋ የሚሰጥ አይደለም  ትላለች የፓሪስዋ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ። ሃይማኖት እንደምትለው የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መንግሥታት ከሀገር ውስጥ የሚደርሱባቸው የተለያዩ ተጽእኖዎች አቋማቸውን እንዲቀያይሩ ምክንያት እየሆኑም ነው።

የአውሮጳ ህብረትን ለሁለት የከፈለ የሚመስለው የህብረቱ የስደተኞች መርህ በወደፊቱ ጉዞው  ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ያም ሆኖ በገበያው እምነት የህብረቱን አንድነት ያፈርሳል የሚል ስጋት የለም ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ