1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአካባቢ ምርጫ ጉዳይ በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10 2014

በቀጣዩ ዐመት እንደሚደረግ ከሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫ አስቀድሞ ጠቅላላ ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች ያልተደረጉ ምርጫዎች እንዲደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ።

https://p.dw.com/p/4FapY
 Ethiopian political parties joint council
ምስል Solomon Much/DW

«የፀጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ምርጫ አናደርግም» 

በቀጣዩ ዐመት እንደሚደረግ ከሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫ አስቀድሞ ጠቅላላ ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች ያልተደረጉ ምርጫዎች እንዲደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአካባቢ ምርጫው ከመደረጉ በፊት የሕዝብ እና ቤት ቆጠራው መካሄድ እንዳለበት አቋም መያዙንም ከዚህ በፊት ዐሳውቆ ነበር። 44 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይሳተፍበታል የሚል ግምት የተሰጠውን የአካባቢ ምርጫ ሥራ ለማስፈፀም 6 ቢሊዮን ብር በጀት ጠይቆ 212 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደተመደበለት የገለፀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ «የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫ አናደርግም» ማለቱ ተዘግቧል። ቦርዱ ስለ ሥጋት፣ ግጭት እና ሌሎችን ችግሮችን ስለመፍታትም ይሁን ስለ ብሔራዊ ምክክር እየተነጋገርን የአካባቢ ምርጫን እናደርጋለን ብሏል። 

Äthiopien Wahl Auszählung in Addis Ababa
ምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ዓመት በየክልሎቹ የአካባቢ ምርጫን የማስፈፀም እቅድ ተይዞ እንደነበር ገልጿል። ቦርዱ ለዚህ የአካባቢ ምርጫ አፈፃፀም መሳካት ስለ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ልምዶችን እና ኢትዮጵያን የመሰለሉ አገሮች ይህንን ሥራ እንዴት ይከውኑታል የሚለውን አስጠንቶ ውይይት አድርጓል።

የአካባቢ ምርጫ የክልል መንግሥታት የሥልጣን ማእቀፍ ውስጥ የሚወድቅ ሲሆን በአንድ በኩል የዜጎችን የመወከል እድል የሚያሰፋ በሌላ ጎኑ ደግሞ ውድድርን የሚያመጣ የዴሞክራሲ ልምምድ ነው ተብሏል። ይሁንና በእድገት ረገድ ወደ ኋላ የተጎተቱ እና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብሔርተኝነት በተካረረባቸው ሀገሮች ውስጥ ፓርቲዎች ከብሔራዊ አጀንዳዎች ይልቅ ጎሳን ፣ ግለሰቦችንና ሌሎች መስፈርቶችን ወደፊት ይዘው የሚቀርቡ በመሆኑ የአካባቢ ምርጫ ለውድድር ሳቢነት የማይኖረውና ውጤቱም መሠረታዊ የሚባል የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያመጣ ነው ማለት እንደማይቻል ለውይይት በቀረበው ጽሑፍ ላይ ተነግሯል።

የብሔራዊ ምርጫ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ፦ «የአካባቢ ምርጫ ከአጠቃላይ ምርጫ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ ግን እስካሁን ከዚህ አንፃር የተሳካልን ሂደት አድርገናል ማለት አይቻልም» ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ ዶክተር ራሄል ባፌ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ባለፉት ዐመታት «ካድሬዎች ይሾማሉ በዚያ መንገድ ነው ሕዝቡ ሲተዳደር የነበረው።» ፓርቲዎችን ያቀፈው ምክር ቤታቸው የሕዝብና ቤት ቆጠራን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ማስቀመጡንም አብራርተዋል።

Äthiopien Birtukan Mideksa UDJ Partei
ምስል Yohannes Geberegziabher/DW

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፀጥታ መጓደል ምክንያት ጠቅላላ ምርጫ ያላከናወነባቸው ስፍራዎች ብዙ ናቸው። ቦርዱ ይህንን ሥራ ለማስፈፀም 6 ቢሊዮን ብር በጀት ጠይቆ ነበር። ሆኖም የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የበጀት ድልድል 212 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደተመደበለት ተገልጿል።

ለምርጫ ቦርድ «መንግሥት የበጀተው በጀት ይበቃል የሚል እምነት የለንም» ያሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ «መንግስት ጉዳዩን ዳግም ይመለከተዋል» የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ክልሎችን ባለቤት እና ባለቤት ያልሆኑ ብለው በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኅዳጣን ዜጎችን ተወካይ መምረጥ እንዳይችሉ የሚያደርጉ የክልል ሕገ መንግሥታት በሥራ ላይ እያሉ ይህ የዴሞክራሲ ልምምድ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል ብለን ጠይቀናቸዋል። እሳቸው ምርጫውን በተመለከተ መቅደም ያለበት እንዲቀድም ምላሽ መስጠቱ ላይ አተኩረዋል።
በመርህ ደረጃ ለአካባቢ ምርጫ ትኩረት አለመንፈግ ይገባል፣ ለአካባቢ ነዋሪዎችም የማስተዳደር ስልጣንን ከማእከላዊ መንግሥት ክትትል ሳይለየው ስልጣን መስጠት መሠረታዊ ጉዳይ ነው የሚለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚመለከታቸው ጋር ሲመክርበት ተደጋግሞ ተገልጿል። 

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ «የፀጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ምርጫ አናደርግም» ብለዋል። በሕዝብ ተወካዮች እና በክልል ምክር ቤቶች ሕዝብን ወክለው የሚገቡ ተመራጭ ሰዎች ከአብዛኛው ሕዝብ የእለት ተእለት የሥራ እና የግንኙነት መስመር የራቁ ሲሆኑ በአካባቢ ምርጫ የሚመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ግን ከይዘትም ሆነ በዓይነት በወካይና ተወካዩ መካከል ያለውን ርቀት የሚያጠብ፣  አገልግሎትን በተሻለ ቅርበት ለማግኘትና ቁጥጥርም ለማድረግ የተሻለ ምቹነት የሚፈጥር ሥርዓት ነው። 

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ