1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአካል ጉዳተኞች ብርቱ ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ኅዳር 29 2015

በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን መሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል። በጦርነት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች እንክብካቤ የሚያገኙበት የተሐድሶ እና ስልጠና ማእከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመንግስት መቅረቡም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Kf77
Äthiopien  World Disability day celebration in Dire Dawa
ምስል Mesay Tekilu/DW

ኢትዮጵያ «ሃያ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይታመናል»

በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን መሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል። በእርግጥም በመንገድ ላይ የቁም እና የወለል ምልክቶች እጦት፤ ወደ ሕንጻዎች አካል ጉዳተኞችን የሚደግፉ መወጣጫዎች እጦት፤ ተመጣጣኝ መጸዳጃ አገልግሎቶች አለመኖር፤ በመጓጓዣ አገልግሎቶች ዘርፍ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት አለመደረጉ ችግሮቹን የሚያባብሱ ጉዳዮች መሆኑንም የአካል ጉዳተኞች በተደጋጋሚ ጊዜያት በምሬት ሲናገሩ ይደመጣል። በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እጅግ አነስተኛ እንደነበረም  ተገልጧል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ለዘርፉ ችግር መፍትኄ ለማምጣት ይረዳሉ ያላቸውን የአደረጃጀት እና ሕግ የማውጣት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ዐስታውቋል። በጦርነት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች እንክብካቤ የሚያገኙበት የተሐድሶ እና ስልጠና ማእከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመንግስት መቅረቡም ተገልጿል። 

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ መንግስት የብዙሀኑን የአካል ጉዳተኞች የመብት ጥሰት ለመከላከል እና እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲቻል የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ ረቂቅ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጠዋል።

ሚንስትሯ የኢትዮጵያ ጀግኖች የጦር አካል ጉዳተኞች ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችል የተሐድሶ እና ስልጠና ማእከል ማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለመንግስት መቅረቡን ተናግረዋል። የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፊት ለፊት ብሩህ ተስፋ ያለ ቢሆንም ቀሪው ሥራ ሰፊ በመሆኑ ለበለጠ ጥረት መዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል። 

በጤናው መስክ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትን ያስረዱት የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተለይ በቅርቡ አካል ጉዳተኞች በጤና የትምህርት መስክ ያላቸውን ተሳትፎ በሚመለከት የገጠመውን ችግር በማንሳት መፍትሄ ለማስቀመጥ እየሰራን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወይንሸት ሙሉሰው በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው ለረጅም ዓመታት የቆየ መሆኑን በማንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት እና በተለያዩ አካላት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ማሳየታቸውን አንስተዋል። የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ ከቀናት በፊት መከበሩ ይታወሳል።

Äthiopien  World Disability day celebration in Dire Dawa | Woineshet Mulusew,
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወይንሸት ሙሉሰውምስል Mesay Tekilu/DW

አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ «ሃያ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይታመናል» ብለዋል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ።

በጎጂ ልማድ እና በተዛባ አመለካከት እንዲሁም በሕግጋት ክፍተት እና በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ በአካል ጉዳተኞች ላይ ወድቆ የቆየው ችግር ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ነበር ተብሏል። በዚህም ምክንያት ዘርፈ ብዙ ለሆኑ ችግሮች ሰለባ ሆነው መቆየታቸው ገልፀዋል።

መንግስት በለውጡ ማዕቀፍ ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ከአካል ጉዳተኛ ማኅበራት እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ተጨባጭና ውጤታማ ስራዎችን እየሰራ ነው ተብሏል።

የአካል ጉዳተኞች የማኅበረሰቡ አካል ናቸዉ

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር በሚንስቴሩ ተቋማዊ መዋቅር ውስጥ ካሉ «በጣም ጥቂት» የሥራ ክፍሎች የአካል ጉዳተኞች የሥራ ክፍል አንዱ ሆኖ በዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲመራ መደረጉን የትኩረቱ ማሳያ መሆኑን ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተናግረዋል።

መንግስት ባለፉት ጊዜያት በብሔራዊ ማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን፣ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች የድርጊት መርኃ ግብር ፣ የአካላዊ ተሐድሶ ስትራቴጂ፣ ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ የማስገባት መመርያ እንዲወጣ በማድረግ በርካታ አካል ጉዳተኞችን ተጠቅሚ ሲያደርግ እንደቆየም ተገልጿል።

በጤናው ዘርፍ በተመሳሳይ የተለያዩ ስራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸው ተጠቅሷል። የጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሁሉን አቀፍ ጥራት ያለው አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት እና የተሐድሶ ህክምና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

Äthiopien  World Disability day celebration in Dire Dawa | Dr. Liya Tadesse,
የጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ምስል Mesay Tekilu/DW

በተለይ የተሐድሶ ሕክምናን ከማስፋት አንፃር ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ስትራቴጂ በመቅረፅ ጥረቶች ተደርገዋል። ሚንስትሯ «የአካል ተሐድሶ ማዕከላት (Physical Rehabilitation Center) የምንላቸው በአሁን ሰዓት እንደ ሀገር ሃያ አራት ተቋማት ይገኛሉ» ብለዋል ። ከእነዚህም ውስጥ አስራ አራት በግል እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አስሩ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ የመንግስት ተቋማት የሚገኙ ናቸው።

ተቋማትን ከማደራጀት ባለፈ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ተብሏል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወይንሸት ሙሉሰው በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው ለረጅም ዓመታት የቆየ መሆኑን በማንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት እና በተለያዩ አካላት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ማሳየታቸውን አንስተዋል።

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ