1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአኝዋክ ስደተኞች በደቡብ ሱዳን

ዓርብ፣ ሐምሌ 6 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሚያዝያ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በወሰዷቸው ርምጃዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የታዩ ግጭቶችን አብርደዋል፤ ከጎረቤት ኤርትራም ጋር ሰላም ፈጥረዋል። ይህ ሁሉ ብዙ አድናቆት አትርፎላቸዋል። ኾኖም በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ዳግም መታየት ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/31QXt
Gorom-Flüchtlingslager im Südsudan
ምስል DW/T. Marima

የአኝዋክ ስደተኞች በጎሮም መጠለያ ጣቢያ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመንግሥቱ ፀጥታ ኃይላት ወሰደውታል በተባለው የኃይል ርምጃ ሰለባ የሆኑት እና ወደ ጎረቤት ሀገር የተሰደዱት ውሁዳኑ የአኝዋክ ጎሳ አባላት ግን አዲሱን የሀገሪቱን አመራር በጥርጣሬ እንደሚመለከቱት በደቡብ ሱዳን የአኝዋክ ጎሳ ተወላጆች የሚገኙበት አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የጎበኘችው ኒያሻ ካዳንዳራ ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መሀመድ ባለፈው ሚያዝያ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የወሰዷቸው ርምጃዎች አስገርመዋል። ሀገሪቱን ወደፊት ለማራመድ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማቲክ ተሀድሶዎች ተደርገዋል። ጠ/ሚንስትሩ የፖለቲካ ክትትል በመሸሽ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ለማነጋገር በሐምሌ ወር መጨረሻ ገደማ ወደ ዩኤስ አሜሪካ ይሄዳሉ። «ግንቡን እናፍርስ» «ድልድዩን እንገንባ » የሚሉ መፈክሮች በማንገብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሀገራቸውን ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ የወደፊት ዕድል መቀየስ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማበረታት ይሻሉ። ይህ መልካም ቢሆንም ግን፣ በጋምቤላ ከሚኖሩት ከውሁዳኑ የአኝዋክ  ጎሳ  አባላት መካከል ብዙዎቹ በዚያ የሚደርስባቸውን ክትትል እና ስቃይ በመሸሽ ከጎርጎሪዮሳዊው ታህሳስ ፣ 2003 ዓም ወዲህ ወደ ጎረቤት ሱዳን ተሰደዋል።  
ከ15 ዓመት በፊት ያኔ የሱዳን ግዛት በነበረው ደቡባዊ የሀገሪቱ አካባቢ፣ ብሎም፣ በዛሬዋ ደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ አቅራቢያ በተከፈተው የጎሮም የስደተኖች መጠለያ ጣቢያ ከሚኖሩት 2,783  መካከል አንዱ የሆኑት ኦሞት አባንግ ክዎት ለጎሳቸው ሁኔታዎች አስጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
«  ዋናው የሸሸንበት ምክንያት ስለተጨፈጨፍን ነው፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። ጭፍጨፋው የተካሄደው በኢትዮጵያ መንግሥት ሲሆን ብሎበምዕራባዊ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል የሚኖረውን የአኝዋክ ጎሳ ለማጥፋት  ። »
የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂውመን ራይትስ ዎች ከ2003 ዓም ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ፀጥታ ኃይላት ይፈጽሙታል ያለውን የመብት ጥሰት መዝቧል። በዚሁ መሰረት፣ ታህሳስ ፣ 2017 ዓም   ቢያንስ 424 ሲቭል የአኝዋክ ተወላጆች ተገድሏል፣ ወደ 16,000 የሚገመቱ ደግሞ ያኔ የሱዳን ግዛት ወደ ነበረው ደቡባዊ የሀገሪቱ አካባቢ ተሰደዋል።  ከ15 ዓመታት ወዲህ ብዙ ስደተኖች አሁንም በዚያው ጎሮም መጠለያ ጣቢያ እንደሚኖሩ ያስታወቀው ክዎት አዳዲስ ስደተኞች አሁንም ከለላ ፍለጋ ወደ መጠለያው ጣቢያ እንደሚመጡ ገልጿል። ከጋምቤላ ግድያና ክትትልን  ሸሽቶ ስደት የገባው ደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመድረስ ሁለት ዓመት የወሰደበት ኦኬሎ ኦቻንግ አንዱ ነው።
« በአካባቢያችን ውጊያ በፈነዳበት ጊዜ የመቁሰል አደጋ ሲደርስብኝ በጦሩ ተማረክሁ፣ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም በእስር ቤት ከቆየሁ በኋላ ተፈታሁ፣ ግን ገንዘብ ስላልነበረኝ ወደ መጠለያ ጣቢያው የመጣሁት በእግሬ ነው። »     
ባልተቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ወደሚኖሩበት የጎሮም መጠለያ ጣቢያ የሄደው ቻንግ በጋምቤላ ግድያው መቀጠሉን ይናገራል። ይሁንና፣ ይላል ቻንግ፣ ሰዎች በጥይት ሳይሆን በመርዝ እየተመረዙ እንደሚገደሉ አስታውቋል። በዚህም የተነሳ ለኦቻንግ ቻም አሁን በመንግሥት አመራር ላይ ለውጥ መደረጉ ያን ያህል ትርጉም የለውም። 

Gorom-Flüchtlingslager im Südsudan
ምስል DW/T. Marima

« ወደፊት ምን እንደሚሆን በርግጥ አላውቅም፣ የመንግሥቱ ስርዓት ግን አለመለወጡን አውቃለሁ። ምንም እንኳን በሀገሪቱ አዲስ ጠ/ሚንስትር ስልጣን ቢይዝም፣ ስርዓቱ አልተቀየረም።»
በጎሮም መጠለያ ጣቢያ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ የምትኖረው አክዋታ ኡሞት ኦኮክ ፣ ጋምቤላ ካሉት ዘመዶችዋ ጋ እንደምትሰማው በዚያ ሁኔታው አስጊ ነው። እናም  እሷም እንዳንዳንዶቹ የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪዎች አዲሱ የሀገሪቱ አመራር ለነርሱ ለውጥ ማምጣቱን በጥርጣሬ ነው ስለምትመለከተው ወደ ትውልድ ሀገሯ የመመለስ እቅድ እንደሌላት ነው የተናገረችው። « ከሁለት እህቶቼ ጋር ግንኙነት አለን። ለደህንነታቸው ይሰጋሉ። ለመኖር ያህል ነው የሚኖሩት። ሁኔታዎች ከተቀየሩ እመለሳለሁ፣ ካልተቀየሩ ግን አልመለስም።» 

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ