1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንጎላዋ "ልዕልት" ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ምስጢሮች

ረቡዕ፣ ጥር 13 2012

የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ልጅ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ በ40 አገሮች በ400 ኩባንያዎች ግዙፍ የንግድ መረብ ዘርግታ በሥራ ፈጣሪነቷ ስትደነቅ ቆይታለች። ሰሞኑን ይፋ የሆኑ ሰነዶች የኢዛቤል ኩባንያዎች በአባቷ ውሳኔ በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ የማማከር ሥራዎች፣ ብድሮች፣ ግዙፍ የመንግሥት የግንባታ ሥራዎችና የንግድ ፈቃዶች እንደተሰጣቸው አጋልጠዋል

https://p.dw.com/p/3WeMq
Angola l Isabel dos Santos - Gericht zieht Vermögen
ምስል picture alliance/dpa/TASS/M. Metzel

የአንጎላዋ "ልዕልት" ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ምስጢሮች

ከአስራ ስምንት አመታት በፊት የአንጎላ አማፂያን መሪ የነበሩት ዮናስ ሳቪምቢ ሲገደሉ በሆሴ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶስ የሚመራው መንግሥት የአንጎላ አልማዝ የሚመረትባቸውን ጉድጓዶች ሙሉ በሙሉ ከእጁ ገቡ። ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን ሐብት ለማስተዳደር አስኮርፕ (ASCORP) የተባለ ኮርፖሬሽን አቋቋሙ። ከኩባንያው 24.5 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ትራንስ አፍሪካ ኢንቨስትመንት ሰርቪስስ ለተባለ በጂብራልታር ለተመዘገበ ኩባንያ ሰጡ። የዚህ ኩባንያ ባለቤቶች ማንነት ለረዥም ጊዜ ሳይታወቅ ቢቆይም የኋላ ኋላ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ እና እናቷ መሆናቸው ተረጋገጠ። 

ለአመታት አንጎላ ትከተለው የነበረውን ፖሊሲ በመቀየር ፕሬዝዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶስ ዩኒቴል የተባለ ኩባንያ በአንጎላ ገበያ በቴሌኮም አገልግሎት እንዲሰማራ ከአስራ ዘጠኝ አመታት በፊት ፈቀዱ። የዩኒቴል 25 በመቶ ባለቤት ቪዳቴል የተባለ በብሪቲሽ ቨርጅን ደሴቶች የተመዘገበ ድብቅ ኩባንያ ሲሆን የዚህም ባለቤት የፕሬዝዳንቱ ልጅ ኢዛቤል ሆና ተገኘች።

አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ

ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሐብቷ ላቧን ጠፍ አድርጋ ያፈራችው የልፋቷ ውጤት እንደሆነ ዓለምን ለማሳመን በብርቱ ለፍታለች። ከሁለት አመት በፊት ሶናንጎል የተባለው የአንጎላ መንግሥት የነዳጅ ንግድ ኩባንያ ኃላፊ ሳለች ለናጠጡ የዓለም ሐብታሞች እና ሥመ-ጥር የነዳጅ ነጋዴዎች በስሟ ያስመዘገበቻቸውን ኩባንያዎች ከስኬት ማማ ለማድረስ ያለፈችባቸውን ውጣ ውረዶች ተናግራ ነበር። 

Präsidentschaftskandidat Jose Eduardo dos Santos Angola
የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶስ ባሳለፏቸው መንግሥታዊ ውሳኔዎች የልጃቸው ኩባንያዎች ግዙፍ የመንግሥት ውሎች ተቀብለዋልምስል picture-alliance/dpa

“ኩባንያዎችን ከትንሽነታቸው ጀምሮ ስኬታማ እስኪሆኑ ድረስ በእያንዳንዱ እርከን እየተከታተልኩ ለረዥም አመታት መርቻለሁ” ብላ ነበር። ወይዘሮዋ ከታሪኳ የዘለለችው አንድ ጉዳይ ነበር። የአንጎላ የድፍድፍ ነዳጅ ምርት እና ግብይት በብቸኝነት የተቆጣጠረውን ሶናንጎል ግሩፕ የተባለ የመንግሥት ኩባንያ በኃላፊነት ለመምራት የተሾመችው በአባቷ መሆኑን ለመናገር አልፈለገችም። 

የሉዋንዳ ሰነዶች

ዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ኅብረት ከ36 የብዙኃን መገናኛ አጋሮቹ ጋር በመተባበር ይፋ ያደረጓቸው ሰነዶች ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት አባቷ ሥልጣን ላይ ሳሉ እንዴት ሐብት እንዳካበተች አጋልጠዋል። ማኅበሩ ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች ከ715,000 በላይ ናቸው። የኢ-ሜይል መልዕክቶች፤ የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባዎች ቃለ-ጉባኤዎች፤ ቪዲዮዎች፤ የብድር ሥምምነቶች፤ የክፍያ ሰነዶች፤ የሥራ ውሎች፤ ደረሰኞች፤ የግብር ማወራረጃዎች ከሰነዶቹ መካከል ይገኙበታል። 
እነዚህ ሰነዶች ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ፤ ባለቤቷ እና ተባባሪዎቻቸው በ40 አገሮች በ400 ኩባንያዎች የገነቡትን ግዙፍ እና ውስብስብ የንግድ ኢምፓየር አሳይተዋል።

ሥራቸውን ሲያከናውኑ ማልታ፣ ሞሪሽየስ፣ እና ሖንግ ኮንግን ጨምሮ 94 ግብር ለማሸሽ የተመቹ አገሮችን ይጠቀሙ ነበር። ኩባንያዎቹ ባለፉት አመታት በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ የማማከር ሥራዎች፣ ብድሮች፣ ግዙፍ የመንግሥት የግንባታ ሥራዎች፣ ለሌሎች የተከለከሉ የንግድ ፈቃዶች ሲያገኙ ቆይተዋል። አብዛኞቹ አባቷ በሚያስተላልፏቸው ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔዎች አማካኝነት የተሰጡ ናቸው። 

የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ እና የአባቷ ምሥጢሮች ሲጋለጡ ዓለም «ጉድ ጉድ» ቢልም ለአገሬው ዜጎች ግን ያን ያክል እንግዳ የሆኑ አይመስሉም። አንጎላዊው ጋዜጠኛ ራፋኤል ደ ሞራዬዝ የሉዋንዳ ሰነዶች የሚል ስያሜ የተሰጣቸው መረጃዎች ዝርዝር መረጃ ቢያቀርቡም ሙስናው ግን ቀድሞም የሚታወቅ ነበር ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። 
"የሉዋንዳ ሰነዶች አዲስ ነገር ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ የራሷን አገር በመዝረፍ ያንን የሙስና መረብ እንዴት እንደዘረጋች የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎች ማቅረባቸው እና የአንጎላ ጥሪት ሲዘረፍ ተባባሪ የነበሩ፤ እንዲሳካ ያመቻቹ ወገኖችን ሚና በጥልቅ ማሳየታቸው ነው። ከዚህ ባሻገር ግን አብዛኛው መረጃ ከዚህ ቀደም በተደረጉ የተለያዩ ምርመራዎች ይፋ የተደረጉ ናቸው» ብሏል። 
የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ኩባንያ በተሳተፈበት የመልሶ ማልማት ዕቅድ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሉዋንዳ ከተማ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤቶቻቸው መፈናቀላቸውን እነዚሁ ሰነዶች አጋልጠዋል። በሉዋንዳ ከተማ ደቡባዊ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት በተጀመረው ዕቅድ የኔዘርላንድስ እና የቻይና ኩባንያዎች ጭምር እጅ ነበረበት። ከመኖሪያ ቤቶቻቸው ለመልሶ ማልማት ለመነሳት የተገደዱ የሉዋንዳ ነዋሪዎች አኗኗር ቢጎሳቆልም ጉዳዩ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስን፣ ኩባንያዎቿንም ሆነ አማካሪዎቿን የሚያሳስብ አልሆነም። 
ሰነዶቹን ከመረመሩት መካከል ቬዴአር የተባለው የጀርመን የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ የሆነው አንድሪያስ ስፒርናትስ እንደሚለው ጉዳዩ የሙስናውን ውስብስብነት የሚያሳይ ነው። አንድሪያስ ስፒርናትስ «ይህ እንደ ግለሰብ ከኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ የላቀ ጉዳይ ነው። በርካታ ዓለም አቀፍ ጠበቆች፤ ኦዲተሮች፤ የሥራ ፈጣሪዎች፣ እና ፖለቲከኞች ከጀርባዋ እንደነበሩ ማሳየት ችለናል» ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። 

Isabel dos Santos of Angola
በስኬቷ ትደነቅ የነበረችው ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ሰነዶቹ የአንጎላ መንግስት በአንድ ቢሊዮን ዶላር ሙስና ከከሰሳት በኋላ ኑሮዋን በዱባይ እና በለንደን አድርጋለች። በአንጎላ ባንኮች ገንዘብ ያስቀመጠችባቸው ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል።ምስል picture-alliance/dpa/Unitel Angola

አንጎላዊው ጋዜጠኛ ራፋኤል ደ ሞራዬዝ እንደ አንድሪያስ ሁሉ የሙስናው ድርጊት ውስብስብ በመሆኑ ይስማማል። ጋዜጠኛው እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ባይ ነው።«ይኸ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ሙስና ነው። ኤዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ሌባ ሆና ሳለ በአንጎላ ስኬታማዋ የንግድ ሰው እያለ ሲያሞካሻት የነበረው ዓለም ነው። ለአንጎላ ያበደሩት ገንዘብ ለኢዛቤል መክበሪያ የዋለባቸው እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች ለምን ብለው መጠየቅ አለባቸው። አንጌላ ሜርክል በቅርቡ አንጎላን ሲጎበኙ ጀርመን ለአንጎላ ያበደረችው ገንዘብ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ እንዴት የእሷ መክበሪያ ሆነ? ብለው መጠየቅ አለባቸው» ሲል አሳስቧል። 

ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ማነች? 

በትውልድ አገሯ የከበረ ስም ባይኖራትም ከሊዝበን እስከ ዱባይ፤ ከፓሪስ እስከ ለንደን የሉዋንዳዋ ልዕልት በሚል ቅፅል ስሟ ትታወቃለች። የአንጎላ መንግሥት ሥራዎቿን እና ኩባንያዎቹን መመርመር በመጀመሩ ሳቢያ ከአገሯ ከወጣች ከአንድ አመት በላይ ሆኗታል። ኑሯዋን በዱባይ እና በለንደን አድርጋለች።  በቅርቡ ለአንጎላ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላት የገለጸችው የ46 አመቷ ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ የሶስት ልጆች እናት ነች። በለንደን እና በሊዝበን የቅንጡ መኖሪያ ቤቶች አሏት። 

Bildergalerie Angola Rohstoffe
ለ38 አመታት አንጎላን የመሩት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶስ የመንግሥቱን ሕግ አውጪ፣ አስፈፃሚ እና ተርጓሚ ቅርንጫፎች ተቆጣጠረው እንደቆዩ ይነገራል።ምስል DW/R. Krieger

ከአባቷ ባላት ጥብቅ ግንኙነት ከተዋወቀቻቸው አሜሪኮ አሞሪየም የተባሉ ፖርቹጋላዊ ባለጸጋ በመጣመር በአንጎላ ባንኮ ቢአይሲ የተባለ ባንክ (Banco BIC SA) አቋቁማለች። ይኸ ባንክ በአሁኑ ወቅት 4.2 ቢሊዮን ዶላር ሐብት ያለው የአንጎላ ቀዳሚ የፋይናንስ ተቋም ነው። ኢዛቤል እና አሞሪየም ከባንክ ባሻገር የስሚንቶ አምራች እና አከፋፋይ፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ንግድ የሚያከናውኑባቸው ኃይል የሚያመነጩባቸው ተቋማትም በጥምረት መስርተዋል። 

አባቷ ሆሴ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶስ በተፈጥሮ ሐብት የናጠጠችውን አገር ለ40 ገደማ አመታት ጸጥ ለጥ አድርገው ገዝተዋል። የአንጎላ ባለስልጣናት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለልጃቸው የሰጧቸው የሥራ ውሎች በአንድ ቢሊዮን ዶላር የተጋነኑ መሆናቸውን ጠቅሰው በአገሪቱ ባንኮች የሚገኝ ጥሪቷን እንዳታንቀሳቅስ አግደዋል። ከዶሽ ሳንቶስ ቤተሰብ የአንጎላን ጥሪት በመመዝበር የተከሰሰች ግን ኢዛቤል ብቻ አይደለችም። የ41 አመቱ ወንድሟ ጆሴ ፊሎሜኖ ዶሽ ሳንቶስ ከአንጎላ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አሽሽቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል። ጋዜጠኛው ራፋኤል ደ ሞራዬዝ እንደሚለው የቀድሞው ፕሬዝዳንት አንጎላን ለልጆቻቸው ሸጠዋታል። «ፕሬዝዳንት ዶሽ ሳንቶስ 38 አመታት በሥልጣን ሲቆዩ አገሪቱን በአብዛኛው ለልጆቻቸው እና ለዘመዶቻቸው ሸጠዋታል። ይኸ ሙስና አንጎላን ገድሏታል። ዜጎች የግል ንፅህናቸውን እና ጤንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል ኤኮኖሚያዊ አቅም የላቸውም። ይኸ የሆነው በፕሬዝዳንቱ ቤተሰቦች ስግብግብነት ነው»

Bildergalerie Angola Rohstoffe
የአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ለኑሮ ውድ ከሆኑ የዓለም ከተሞች አንዷ ናት። በአንድ አፓርታማ ላይ የሚገኝ የመኖሪያ ቤት ኪራይ እስከ 5,000 ዶላር ይደርሳል።ምስል DW/R. Krieger

የኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስ ባለቤት ሲንዲካ ዶኮሎ ውድ የጥበብ ሥራዎች እና ቅንጡ ተሽከርካሪዎች በመሰብሰብ የሚታወቅ የኮንጎ ዜጋ ነው። አሁን ይፋ የሆኑት ሰነዶች እንደሚጠቁሙት ዶኮሎ በባለቤቱ የንግድ ሥራዎች እና የገንዘብ ዝውውሮች ቁልፍ ሚና ያለው ሰው ነው። 

ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶስም ሆነች ጠበቆቿ ከማልታ እስከ ሉዋንዳ፤ ከዱባይ እስከ ሊዝበን በተዘረጋው የንግድ እንቅስቃሴ አንዳች ጥፋት አልተፈጸመም ሲሉ ክደዋል። «ዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ኅብረት ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች በሙሉ የውሸት ናቸው» ያለችው ኢዛቤል «ማን ያምነዋል?» ስትል ጉዳዩን ልታጣጥል ሞክራለች። 
«ይኸ በአንጎላ ሕዝቦች ንቅናቄ ለነፃነት የውስጥ ፖለቲካ ላይ ጫና ለማሳደር፤ የሌሎች እጩዎች ድምፅ እንዳይሰማ፤ በፓርቲው ውስጥ ሊኖር የሚችል ሌላ ቡድን እንዳይነሳ የሚደረግ ጥረት ነው» ስትል ክሶቹ ከፖለቲካ ቅራኔ የመነጩ መሆናቸውን ገልጻለች።  

የሐብታም ደሐ - አንጎላ

Angola Rohstoffe
በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙት አንጎላውያን ያገራቸው ሐብት እንዴት ወዴት እንደሔደ የሚያስረዳ መረጃ አግኝተዋልምስል DW/Renate Krieger

በደቡብ የአፍሪካ ቀጠና የምትገኘው አንጎላ በነዳጅ ዘይት እና በአልማዝ የናጠጠች የሐብታም ደሐ ነች። የአገሪቱ ጥቂት ልሒቃን አንጡራ ሐብቷን ለብቻቸው ሲቀራመቱ ግፋ ሲልም ወደናጠጡት የአውሮፓ አገራት እያሸሹ ኑሯቸውን ሲያደላድሉ ኖረዋል። ፕሬዝዳንት ጁዋዎ ሎሬንዞ የሚመሩት መንግሥት አንጎላን የልጆቻቸው እና ቤተ-ዘመዶቻቸው ጓዳ ያደረጉትን የቀድሞ መሪ ከፍትኅ ፊት ማቅረብ ስለመቻሉ በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው። ደ ሞራዬዝ ግን «ፕሬዝዳንቱ ያለመከሰስ መብታቸው በ2022 ዓ.ም. ያበቃል። ከዚያ በኋላ በሥልጣን ላይ ሳሉ ላጠፉት ጥፋት እና ለፈጸሙት ወንጀል ከችሎት ቆመው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙ እና ሥልጣናቸውን በለቀቁ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ በርካታ ምርመራዎች ተጀምረዋል። የጦር ጄኔራሎች እና የምክር ቤት አባላ ትን ጨምሮ አንዳንዶቹ ክስ ተመስርቶባቸዋል። በርካቶችም ታስረዋል። መንግሥት የሕግ አስፈፃሚው እስከሚችለው ድረስ በርካታ ጉዳዮችን ለፍርድ እያቀረበ ነው። በእርግጥ ትክክለኛው አካሔድ ይኸ አይደለም። ምክንያቱም አብዛኞቹ ዳኞች እና ዐቃብያነ-ህግጋት በጆዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶስ በራሳቸው የተሾሙ ናቸው» ሲል አስረድቷል። 

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ