1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝክረ ተክሌ የኋላ፦ ከ45 ዓመታት ጋዜጠኝነቱ፣ ከአባትነት እና ጓደኝነቱ በጥቂቱ የተጨለፈ

ዓርብ፣ ነሐሴ 6 2014

ለ45 ዓመታት በጋዜጠኝነት የሰራው የተክሌ የኋላ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ረቡዕ በጀርመኗ ኮሎኝ ከተማ ተፈጸመ። በዶይቼ ቬለ ባገለገለባቸው 39 ዓመታት ካጠናቀራቸው ዘገባዎች እጅግ ጥቂቱን በማካተት፣ ልጁን፣ የሥራ ባልደረቦቹን፣ አድናቂዎቹን እና ወዳጆቹን በማነጋገር ተክሌ የኋላን እንዘክራለን።

https://p.dw.com/p/4FNl5
Funeral service for former DW Journalist Tekle Yehwal held in Cologne, Germany
ምስል Lidet Abebe/DW

ዝክረ ተክሌ የኋላ፦ ከ45 ዓመታት ጋዜጠኝነቱ፣ ከአባትነቱ እና ጓደኝነቱ በጥቂቱ የተጨለፈ

የጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በምዕራብ ጀርመን በምትገኘው የኮሎኝ ከተማ ተፈጸመ። በኮሎኝ ከተማ በተካሔደው ሥርዓተ ቀብር ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹ እና ወዳጆቹ ተገኝተዋል።

የዶይቸ ቬለ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር ተክሌ የራዲዮ ጣቢያው ሥርጭት የሚተላለፍበት ቋንቋ በጽሁፍም ሆነ በንግግር ከፍተኛውን ደረጃ የጠበቀ እንዲሆን ላቅ ያለ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።

ተክሌ "ኢ-መደበኛ ቃላት የሚጠቀሙ ባልደረቦቹን እንደ ዘበት አያልፍም" ያሉት ሉድገር ሻዶምስኪ "በአማርኛ ዘገባቸው ውስጥ የእንግሊዘኛ ቃላት ጉራማይሌ መጠቀምን በፍጹም አይቀበልም" ሲሉ ለቋንቋ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

የተክሌ የኋላ ህልፈት ከተሰማ በኋላ ለ25 ዓመታት የሚያውቀው የዶይቸ ቬለ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ምክትል ኃላፊ እና ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ "ጥሩ አድማጭ" እንደነበር አስታውሷል።

"የተናጋሪው ሐሳብ ይጣመው አይጣመው ረጅም ጊዜ ወስዶ በትዕግስት ያደምጣል።  ታጋሽም ነበር" ያለው ነጋሽ "በየጊዜው የኢትዮጵያን ጉዳይ፣ በየአጋጣሚው ቢያነሳ አይጠግብም፤ አገር ወዳድ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አኗኗር በጣም የሚስበው ይመስለኛል። በተደጋጋሚ ያነሳዋል" በማለት የቀድሞ ባልደረባው ተክሌ ለአገሩ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር ገልጿል።  

ተክሌን "አገር አላማጄ" የምትለው ሸዋዬ ለገሰ እንደ በርካታ የሥራ ባልደረቦቹ የቋንቋ ክኅሎቱ እና ጥንቃቄው ከፍተኛ እንደነበር ከሚናገሩ መካከል ነች። "በአማርኛ ውስጥ እንግሊዘኛ ወይም ጀርመንኛ እንድትከት አይፈልግም። በእንግሊዘኛም ሲያወራ አማርኛ አይቀይጥም" ስትል ሸዋዬ ለቋንቋ ያደርግ የነበረውን ከፍተኛ ጥንቃቄ ትገልጻለች።

ለዓመታት አብራው የሰራችው ኂሩት መለሰ "ተክሌ ለራዲዮ የተፈጠረ ጋዜጠኛ" ስትል ትገልጸዋለች። "ከድምጹ ብትጀምር በጣም ማራኪ ድምጽ አለው። ከዚያ ቀጥሎ አነባበቡ በጣም ሳቢ ነው። ፕሮግራሙን የሚያቀርብበት መንገድ አድማጮችን መያዝ የሚችል ነው" የምትለው ኂሩት የቃላት አጠቃቀሙ እና የአረፍተ ነገር አወቃቀሩ "ሁሉ የተለየ" እንደነበር ታስታውሳለች።

ተክሌ የኋላ ኢትዮጵያ "ትክክለኛ የፖለቲካ አቅጣጫ ይዛ ስትጓዝ ማየት እና ሕዝቦቿም የሚፈጸምባቸው በደል እንዲቆም የሚመኝ" ጋዜጠኛ እንደነበር ትናገራለች። ኂሩት እንደምትለው ተክሌ "ሁልጊዜ በኢትዮጵያ ፍትኃዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ታላቅ ምኞት ነበረው።"

Köln Beisetzung Ex-DW Journalist Tekle Yehwal
የተክሌ የኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሐምሌ 4 ቀን 2014 በኮሎኝ ከተማ ተፈጽሟል።ምስል Eshete Bekele/DW

ተክሌ የኋላ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበር። ይኸ ለአገሩ የነበረው ፍቅር ታዲያ ለልጆቹ ያወረሰው ጭምር ነው። የወንድ ልጁን ስም ያወጣው በአድዋው ጀግና አሉላ አባነጋ ስም ነው። አሉላ አባቱን ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር በቤተሰብ ሰውነቱ ያስታውሰዋል፤ በተጫዋችነቱ። አሉላ ተክሌ ስለ አባቱ ሲያስታውስ "ብዙ ጊዜ እኔ እና እህቴ ስለ አገራችን ታሪክ በተወሰነም ስለ ፖለቲካ እንድናውቅ ምኞት ነበረው" ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።  አሉላ እንደሚለው ተክሌ ልጆቹ "ተንኮለኛ፣ መጥፎ እና ሆዳም" ሰው እንዳይሆኑ አበክሮ ይመክራቸው ነበር።  

ከአራት አስር ዓመታት በላይ በዘለቀ የጋዜጠኝነት ሙያው የተንጸባረቀው፣ ወደ ልጆቹ ያሻገረው፣ በሥራ ባልደረቦቹ የሚመሰከርለት አገር መውደድ ግን በዚህ አላበቃም። ከ1997 የኢትዮጵያ ምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰ ኹከት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ አምባገነን መንግሥትን "ጠብመንጃ ያልያዘ ሰው ድንጋይ ይዞ መጋፈጥ እንደማያዋጣ" የሚጠቁም እና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ሲዘጋጅ ተክሌ የኋላ በሙያው ተሳትፎ አድርጓል።

የተክሌ የኋላ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አቶ ኤልያስ ወንድሙ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ባቋቋሙት የኢትዮጵያ የነውጥ አልባ ትምህርት እና የሰላም ጥናት ማዕከል በኩል የተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም በስድስት አገራት የነበሩ የፖለቲካ እና የነጻነት ትግል ታሪኮችን የሰነደ ነው። ተክሌ የኋላ የተረከው ይኸው ዘጋቢ ፊልም ከደቡብ አፍሪካ የእነ ኔልሰን ማንዴላ የመጨረሻ ሰዓት፣ ከአሜሪካ የማርቲን ሉተርኪንግ፣ ከሕንድ የማሕተመ ጋንዲ የትግል ታሪኮች እና ስልቶችን ያቀርባል።

Deutsche Welle 50 Jahre amharische Redaktion
ተክሌ የኋላ በዶይቼ ቬለ የአማርኛ ክፍል ለ39 ዓመታት ሰርቷልምስል DW/Lambertin

ዘጋቢ ፊልሙን የተረከው ተክሌ "በወርቃማ ድምጹ፣ በሚያረጋጋ ድምጹ የብዙ ሰዎችን ቀልብ ለመውሰድ ችሏል" የሚሉት የጸሀይ አሳታሚ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ "ታሪኩን የበለጠ እንድንሰማው፣ የበለጠ እንዲገባን፣ የበለጠ እንድናምነው አድርጎልናል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ተክሌ ሙዚቃ በተለይ ጊታር ይሞካክር ነበር። ልጁ አሉላ እንደሚለው ስፖርት ይወዳል። እግር ኳስም ይጫወት ነበር። በተለይ ደግሞ የፔሌ አድናቂ ነው። ለስድስት አመታት በኢትዮጵያ፤ ለ39 አመታት በአውሮፓ በተለይም በጀርመን ውስጥ በአጠቃላይ ለ45 ዓመታት በጋዜጠኝነት ሰርቷል። በ72 ዓመቱ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ተክሌ የኋላ ከወደዳት፣ ከተቆረቆረላት፣ በጎ በጎውን ከተመኘላት ኢትዮጵያ ርቆ ይቺን ዓለም ተሰናበተ። ሥርዓተ ቀብሩ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ እና የሥራ ባልደረቦቹ በተገኙበት ዛሬ ሐምሌ 04 ቀን 2014 በኮሎኝ ከተማ ተፈጸመ።

እሸቴ በቀለ