1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ኢሌኒ መኩርያ ሕይወት እና ስራዎቻቸው

እሑድ፣ ሐምሌ 18 2013

"የቱንም ያህል የኑሮ ፈተና የቱንም ያህል የሕይወት ውጣ ውረድ ቢገጥመኝ አምላክ እስትንፋሴን እስኪወስዳት ፈጽሞ ተስፋ አልቆርጥም::" በአንድ ቃለ ምልልስ ይህን ያሉት አንጋፋዋና ተወዳጇ የመጀመሪያዋ እንስት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ እንዲሁም የቀድሞ የዶይቼ ቨለ "DW" ባልደረባ እሌኒ መኩሪያ ነበሩ::

https://p.dw.com/p/3y1it
Journalist Elleni Mekuria
ምስል Endalkachew Fekade/DW

የአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ኢሌኒ መኩርያ ሕይወት እና ስራዎቻቸው

"የቱንም ያህል የኑሮ ፈተና የቱንም ያህል የሕይወት ውጣ ውረድ ቢገጥመኝ አምላክ እስትንፋሴን እስኪወስዳት ፈጽሞ ተስፋ አልቆርጥም::" በአንድ ቃለ ምልልስ ይህን ያሉት አንጋፋዋና ተወዳጇ የመጀመሪያዋ እንስት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ እንዲሁም የቀድሞ የዶይቼ ቨለ "DW" ባልደረባ እሌኒ መኩሪያ ነበሩ:: በሙያ ክህሎታቸውም ሆነ በበጎ ተግባራቸው ዘውትር የሚታወሱትን እኝህ ታላቅ ኢትዮጵያዊት የመገናኛ ብዙሃን አንፀባራቂ ፈርጥ ባለፈው ረቡዕ ሀምሌ 14,2013 ዓ.ም በሞት ተነጥቀናል:: በዚህ ዝግጅታችን የባለሙያዋን ግለ-ሰብዕናና ከስድስት አስርተ ዓመታት በላይ ያበረከቷቸውን አንኳር ጉዳዮች በጥቂቱ እንዘክራለን::

 

"የሴት ልጅ ክብሯ ጓዳና ማጀቷ ነው" በሚባልበት ቆየት ያለው ዘመን 60 ዓመታት የኋልዮሽ ተሻግረን የነበረውን ታሪክ ስንፈትሽ በዚህ ዝግጅታችን ግለ-ታሪካቸውንና የሙያ ክሎታቸውን የምንዘክረው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ እሌኒ መኩሪያ ይህን ኋላቀር ባህልና አባባል ሰብረው ወደ ሙያ ስኬት ማማ ከፍ ያደረጋቸውን ለሌሎችም ታዳጊ ወጣቶች አስተማሪ የሆነውን ጥረት፣ አልበገር ባይነትና ትጋት ማስተዋል አይከብድም:: በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ 1934 ዓ.ም ከወላጅ አባታቸው አቶ መኩሪያ ወልደስላሴና ከእናታቸው ወ/ሮ ሶስና ወርቅነህ በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዘነበወርቅና በእንግሊዝ ስኩል /ሳንፎርድ/ መከታተላቸውን ግለ ታሪካቸው ያስረዳል::በልጅነትና በወጣትነት የዕድሜ ዘመናቸው ቴኒስ ጨዋታ፣ ውሃ ዋና፣ ፈረስ ግልቢያ ፣ ዳንስ ፣ ቴአትር ማየትና መተወን እንዲሁም ልዩ ልዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ማዘውተር ይበልጥ ያስደስታቸው እንደነበር ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው ይናገራሉ:: በአንድ ቃለ-ምልልስ ላይ እንደገለጹት ገና በአፍላ የታዳጊ ዘመን ዕድሜያቸው ለልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል የግንባታ ስራ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር በተዘጋጀበት ወቅት አንድ አጭር የመድረክ ቴአትር ተውነው ነበር:: አዲስ አበባ ከተማ በተቋቋመው የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር /ወሴክማ/ ውስጥም ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል:: በተፈጥሮአቸው ሳቂታ፣ ቀልድ አዋቂና በቀላሉ ከሰው ጋር ተግባቢ ነበሩ የሚባሉት እሌኒ በሳንፎርድ ትምህርትቤት ትምህርታቸውን መከታተላቸው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል:: የልጅነት ምኞታቸው ማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ የነበረ ቢሆንም በ 1951 ዓ.ም ቤሩት በሚገኘው የአሜሪካ የነርሶች ማሰልጠኛ ዩኒቨርሲቲ የነርስ ሙያ ነጻ የትምህርት ዕድል በማገኘታቸው ወደዚያው ሊያቀኑ ችለዋል::

Journalist Elleni Mekuria
ምስል Endalkachew Fekade/DW

 

ቤተሰባቸው በወቅቱ ወደ ህክምና ሙያው እንዲያዘነብሉ ግፊት ያደረጉባቸው የአያታቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ከመነጨ ጉጉት ቢሆንም ወትሮም ቢሆን የእሌኒ ፍላጎት ከህክምና ወጪ ስለነበር ከጥቂት ቆይታ በኋላ ትምህርቱን ሳይገፉበት አቋርጠው ወደ ትውልድ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ:: እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ዘመናዊ የህክምና ታሪክ የመጀመሪያው ሀኪም የሚባሉት ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ የአንጋፋዋ ጋዜጠኛ እሌኒ ወላጅ እናት ወይዘሮ ሶስና አባት ሲሆኑ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በልዩ ልዩ ሀገራት በሙያቸው ከማገልገላቸውም በላይ በዛሬዋ ማያንማር /በርማ/ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ተሹመው እንደነበር ይጠቀሳል:: በኢጣልያ ወረራ ወቅትም በስደት ላይ ከነበሩት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጋር በታላቋ ብሪታንያ የኢትዮጵያ ጉዳይ ፈጻሚ ወኪል ሆነው በእንግሊዝ ጋዜጦች የሀገሪቱን ተጨባጭና ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ የሚሰጡ ነበሩ:: ከድል በኋላም በንጉሱ ትዕዛዝ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ስለምትገነባው ግድብ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር እንዲደራደሩ ተወክለው ተልከዋል:: "በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ላይ ደማቅ አሻራ አሳርፋለች" ሲሉ የቅርብ የሙያ አጋሮቻቸው የሚገልጿቸው እሌኒ መኩሪያ በ 1950ዎቹ ዓ.ም የቴሌቪዥን ሥርጭት የቴክኖሎጂ ስልጣኔ ዓለምን ባስደመመበት ወቅት የሕይወታቸውን አቅጣጫ ወዳላሰቡት መስመር የሚቀይር አንድ አስገራሚ ክስተት ተፈጠረ:: ከቤሩት መልስ የማህበራዊ አገልግሎት ሙያተኛ /ሶሻል ወርከር/ በመሆን ሕብረተሰቡን የማገልገል ውጥንን ሰንቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ትምህርታቸውን የቀጠሉት ባለሙያዋ ብዙም ሳይቆዩ የቀድሞው የኢትዮጵያ ራዲዮ ዓለማቀፍ አገልግሎት ወይም ብስራተ-ወንጌል ይባል የነበረው የራዲዮ ጣቢያ የእንግሊዘኛ ፕሮግራም ለመጀመር ጋዜጠኞችን አወዳድሮ መቅጠር እንደሚፈልግ የሚገልጽ ማስታወቂያ በመስማታቸውና ትኩረታቸውንም በመሳቡ ተወዳድረው ፈተናውን ካለፉ በኋላ ዛሬ ከፍ ወዳለ የስኬት ማማ ያወጣቸውንና "የመጀመሪያዋ እንስት

ኢትዮጵያዊት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ" ያሰኛቸውን ሙያ አንድ ብለው መጀመራቸውን ከአራት ዓመታት በፊት ለታላላቅቅ የሙያ ስኬት የበቁ እንስት ኢትዮጵያውያትን የእውቅና ሽልማት በመስጠት የሚያበረታታው ኤዩብ ኢትዮጵያ /AWiB WoE/ የተሰኘው ድርጅት የ 2017 ዓ.ም አሸናፊ መሆናቸውን ካበሰረ በኋላ ስሜታቸውን እንዲገልጹ ባቀረበላቸው አጠር ያለ ቃለ-ምልልስ ላይ ተናግረዋል::

Journalist Elleni Mekuria
ምስል Endalkachew Fekade/DW

 

ዕውቋ ጋዜጠኛ እሌኒ መኩሪያ በጋዜጠኝነት ሙያ ከተሰማሩ በኋላ ቀደም ሲል እንደገለጹት በወቅቱ በአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት /ዩኤስ ኤድ/ በተልዕኮ ትምህርት የሚሰጠውን የጋዜጠኝነት ሙያ መሰረታዊ ሥልጠና ተከታትለዋል:: የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክህሎታቸው በአለቆቻቸው ዘንድ አድናቆትና ዕውቅና ስላተረፈላቸው ብዙም ሳይቆዩ ከዓለማቀፉ የራድዮ ጣቢያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ራድዮ ብሔራዊ አገልግሎትም በተመሳሳይ ቋንቋ ዜና አንባቢነት፣ የሙዚቃና የመዝናኛ ፕሮግራሞች አዘጋጅነትና የቃለ መጠይቅ ዝግጅቶችንም ደርበው እንዲሰሩ በር ከፍቶላቸዋል:: ከውጭ በቀሰሙት የሙያ ልምድም የኢትዮጵያ ራዲዮን የድምጽ ክምችት መዘክር ክፍልን /ኣርካይቭ/ በዘመናዊ መልክ በማደራጀት ቆየት ያሉ በሸክላ የተቀረጹ ድምጾች፣ሪል ቴፖች፣ ካሴቶችና የሲዲ ማቴሪያሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ታሪካዊ የጽሁፍ መዛግብትን በዓይነት እና በዘመናቸው በካታሎግ ሥርዓት ለይቶ በማደራጀት ጋዜጠኞችና የምርምር ባለሙያዎች በፈለጉት ጊዜና በቀላሉ እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን አሰራር ዘርግተዋል::

 

ግንቦት 18, 1955 ዓ.ም የቀድሞ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት የአሁኑ የአፍሪቃ ህብረት ቻርተር በአፍሪቃ መሪዎች መካከል አዲስ አበባ ውስጥ ሲፈረም የ 21 ዓመቷ ወጣት ጋዜጠኛ እሌኒ መኩሪያ የስብሰባውን ሂደት ተከታትላ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመዘገብ ቀዳሚዋ ሴት ጋዜጠኛ ሆናለች:: ከዛም በኋላ በ 1957 ዓ.ም የአፍሪቃ ህብረት ኦፊሴሊያዊ ምስረታን አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ የምስረታውን ሂደት ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማስተላለፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲቋቋም በአፍሪቃ ህብረት አዳራሽ ተገኝታ የድርጅቱን ምስረታና የስብሰባውን ሂደት በእንግሊዘኛ ቋንቋ በቴሌቪዥን በመዘገብ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት እንስት የቴሌቪዥን አንባቢ ሆነው በታሪክ ተመዝግበዋል:: ወዳጆቻቸው እና የሙያ አፍቃሪዎቻቸው "የሰው ልክ" እያሉ የሚያወድሷቸው ጋዜጠኛዋ ከኢትዮጵያ ራድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሌላ እንደ ቢቢሲ ላሉ ዓለማቀፍ የሚድያ ተቋማት የዜና ወኪል ሆኖ በመስራት ከፍተኛ የሙያ ልምድን አካብተዋል:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2001 ዓ.ም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም በግጭቱ የተፈናቀሉ በመጠለያ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ /አንሚ/ አማካኝነት ለተነደፈው በአማርኛ ትግርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የሚተላለፍ የራዲዮ ሥርጭት ለአምስት ዓመታት በፕሮግራም አስተባባሪነት አገልግለዋል:: በጋዜጠኝነት፣ በሕዝብ ግንኙነት ሙያና በበጎ አድራጎት ተግባራቸው የሚታወቁት ወ/ሮ እሌኒ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲመሰረት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሳሙኤል ፈረንጅና እንደ ልዑል ሰገድ ኩምሳ፣ታቦቱ ወልደሚካ ኤል፣ላዕከማርያም ደምሴና ሌሎችም የሙያ ባልደረቦቻቸው ለደረሱበት ከፍተኛ ስኬት ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው በተለያዩ መድረኮች ገልፀዋል:: በብስራተ ወንጌል፣ በኢትዮጵያ ራድዮና ፕሬስ ፣ በቪ.ኦ.ኤ የእንግሊዘኛ ፕሮግራም የዜና ወኪልነት፣ በቢቢሲ ፣በራድዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናልና ቻናል አፍሪቃ የመገናኛ ብዙኃን ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው ታዋቂው ጋዜጠኛ ላዕከማርያም ወይዘሮ እሌኒ የቅርብ የሙያ አጋሩ ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰባዊ ቅርበትም እንዳላቸው ፍልቅልቅ፣ ትሁት፣ ጨዋታ አዋቂ፣ ሙያቸውን አፍቃሪና ከስራ

ባልደረቦቻቸውም ጋር ተግባቢና ቅን ሰው እንደነበሩ ለዶይቼ ቨለ ገልጿል:: ለቢቢሲ የእንግሊዘኛ ዘጋቢ በነበሩባቸው ከ 8 የሚልቁ ዓመታት በተለይም ደግሞ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ፈታኝ ወቅት የግንባር ዘገባዎችን ከባለሙያዋ ጋር ተቀራርበው በሙያ እየተደጋገፉ መስራታቸውንም ያስታውሳል:: የሳቸውን አሻራና የሙያ ፈለግ ተከትላ በአሁኑ ወቅት ሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ 102.1 ላይ ለአፍሪቃውያን የሚዘጋጅ የሙዚቃ ፕሮግራም የምታቀርበው ልጃቸው ቀፀላ ሰይፉም እናቴን በአንድ ቃል ብገልጻት "ፍፁም ፍቅር ነበረች" ስትል የእምባ ሳግ እየተናነቃት ነግራናለች:: "እንኳን ለሰው ልጅ ለእንሳሳና እጽዋት ጭምር አዛኝ ፣ረዳት፣ ቸርና ለጋስ የሆነች ጎዳና የወደቀን አንስታ የምትረዳ ድንቅ እናት ነበረችም" ብላለች ቀፀላ::

"ሴቶች በእራስ የመተማመን ችሎታን በማዳበርና የባህል ተጽዕኖ በመቋቋም በዕውቀት፣ በትምህርትና በጥረት ከወንዶች እኩል አልያም የላቀ አስተዋጽዖ ማበርከት ይችላሉ" የሚል ጠንካራ ዕምነት የነበራቸው ጋዜጠኛ እሌኒ መኩሪያ በሴቶች ጉዳይ በተለይም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሴት ታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን አካላዊና የመንፈስ ጥቃት በተጓዳኝም ያለ እድሜ ጋብቻን በተመለከተ ግንዛቤን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ዶክመንተሪ

ፊልሞችን አዘጋጅተው በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረው ለሕብረተሰቡ በማሳየት ከፍተኛ የግንዛቤና የማንቃት ስራ አከናውነዋል::እነዚህ ፊልሞች በለንደኑ ቻናል-4 በአሜሪካና አውስትራሊያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከመተላለፋቸውም ሌላ ፊልሙ ዓለማቀፍ አድናቆት በማግኘቱ የምርጥ ስራ ስኬት የሙያ አርበኛ በሚል እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2001 ዓ.ም ከለንደኑ አልትሩሳ ኢንተርናሽናል ድርጅት ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል:: በመሰረተ ትምህርት ዘመቻ፣በኢትዮጵያ የሴቶች ድጋፍ ሰጪ ማህበር፣ በማህበራዊ ግልጋሎት ድርጅትና በሌሎችም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ የሴቶችን ችግር ለመፍታትና የሙያ ብቃታቸውን ለማጎልበት ለረጅም ዓመታት ነጻ የበጎ አገልግሎት ተግባር ላይ ተሰማርተው የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል:: ለታሪክ ከፍተኛ ፍቅርና አትኩሮት የነበራቸው ጋዜጠኛ እሌኒ የጡረታ ጊዜያቸውን በማንበብና በምርምር ስራ ማሳለፋቸውን ወዳጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ:: ሁልጊዜ ለምለምና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለማየት የሚናፍቁትና ተፈጥሮን የማድነቅ ዝንባሌ የነበራቸው ባለሙያዋ ስለሃገራችን ዛፎችና ዕጽዋት የሚያስተዋውቅ በምስል የተደገፈ መጽሐፍ አዘጋጅተው ለንባብ አብቅተዋል::

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኝነት ታሪክ ስማቸው እንዲህ በጉልህ የሚጠቀሰው እሌኒ መኩሪያ የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞችን ማህበር እንዲመሰረትና እንዲጠናከር ካደረጉ ግንባር ቀደም ሙያተኞች አንዷ ሲሆኑ በአመራርነትም አገልግለዋል:: የአፍሪቃ ሴቶች የሚድያ ኮሚቴ የአማካሪዎች የቦርድ አባልም ነበሩ::

በ 1959 ዓ.ም ከባለቤታቸው ኢንጂነር ሰይፉ ለማ ጋር ትዳር መስርተው 3 ሴት ልጆችን ያፈሩት ጋዜጠኛ እሌኒ መኩሪያ ባደረባቸው ህመም በሀገር ውስጥና በውጭ በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ የማይሞት ታሪካዊ አሻራቸውን ለተተኪው ትውልድ ትተው ባለፈው ረቡዕ ሀምሌ 14,2013 ዓ.ም በተወለዱ በ 79 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል:: ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቻቸው፣በርካታ አድናቂዎቻቸውና ወዳጆቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል:: ዶይቼ ቨለ በአንጋፋዋና ተወዳጇ እንዲሁም በመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በሙሉ መጽናናትን ይመኛል::

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

እንዳልካቸው ፈቃደ

ታምራት ዲንሳ