1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንበጣ ወረርሽኝ በምስራቅ አፍሪቃ

ዓርብ፣ ጥር 22 2012

በቅርቡ የተከሰተዉን የአንበጣ መንጋ በጊዜ መከላከል ካልተቻለ በምስራቅ አፍሪቃ የምግብ ችግር ሊያጋጥም ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል። እንደ ድርጅቱ 76 ሚሊዮን ዶላር  የአንበጣ መንጋዉን ለመግታት የሚያስፈልግ ቢሆንም እስካሁን የተገኘዉ ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ ሁኔታዉ ሚሊዮኖችን ለምግብ ዋስትና ችግር ይዳርጋል ።

https://p.dw.com/p/3X6WO
Global Ideas Kenia Heuschreckenplage
ምስል picture-alliance/AP Images/B. Curtis

«ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ሊዳርግ ይችላል»


በምስራቅ አፍሪቃ እየተስፋፋ የመጣዉ የአንበጣ መንጋ አፍሪቃ  ላለፉት 70 ዓመታት አይታ የማታዉቀዉ ነዉ።ይህንን ለመከላከል እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 76 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል ።ነገር ግን እስካሁን የተሰበሰበዉ  15 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ። ይህም ቀድሞዉንም የረሃብና የድህነት ስጋት ላለባቸዉ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገሮች የአንበጣዉ ወረርሽኝ በጊዜ ካልተገታ ሚሊዮኖችን የባሰ ችግር ላይ ሊጥልና የምግብ ዋስትና ሊያሳጣ ይችላል ሲል  የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ገልጿል።የድርጅቱ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ዶምኒኩ ቡርገን እንደሚሉት ኢትዮጵያ በዋናነት ከተጠቁ ሀገራት መካከል አንዷ ነች።
«በአሁኑ ጊዜ ኬንያ ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በቢሊዮን በሚቆጠሩ የበረሃ አንበጣ ከተጠቁ ሀገራት መካከል ዋነኛዎቹ ናቸዉ። ነገር ግን ሌሎች ሀገሮችም አሉ።በተለይ ደቡብ ሱዳን ዩጋንዳና ኤርትራ በበረሃ አንበጣ  ከተጠቁት ሀገሮች ዉስጥ ናቸዉ።»
ያም ሆኖ በኢትዮጵያ ችግሩ የምግብ ዋስትና ስጋትን አይፈጥርም ሲሉ በግብርና ምንስቴር የዕፅዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር አቶ ወልደ ሃዋሪያት አሰፋ ቀደም ሲል ለዶቼቬለ ገልጸዉ ነበር። 
ዶቼ ቤለ ያነጋገራቸዉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴም መስሪያ ቤታቸዉ በዚህ ጉዳይ እየሰራ ባይሆንም ሀሳቡን ይጋሩታል። 
 የአንበጣ መንጋ ከዝናቡ  መጣልና  ከአዳዲስ  ዕፅዋት ማቆጥቆጥ ጋር ተያይዞ በዚህ ሳምንትም በደቡብ ሱዳንና በዩጋንዳ ሊስፋፋ ይችላል ተብሏል።ይህ ወረርሽኝ ደረቁ የሰኔ ወር እስኪመጣ ድረስ ስርጭቱን በቀላሉ መቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑም ነዉ በዘገባዉ ተገለጿል። እናም በጊዜ መላ ሊበጅለት ይገባል ይላሉ ዶምኒኩ ቡርገን ከፋኦ ።
«ከ 11 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ባለበት ክልል ውስጥ ነን ። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቱን የከፋ ችግር  ለማስወገድ  በተቻለ መጠን ጥረት ማድረግ አለብን ። እንደምናየዉ እነዚህ አንበጣዎች በእህል ብቻ ሳይሆን የግጦሽ መሬትም ጭምር እያወደሙ በመሆናቸዉ  በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አኗኗር ላይ ተፅእኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እናውቃለን ።ለዚህም ብቸኛው መፍትሔ የአየር ላይ ፀረ-ተባይ ርጭት ነዉ።»
ያካልሆነ ግን  ቁጥሩ አምስት መቶ ጊዜ ሊጨምር እንደሚችል ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነዉ።ለዚህም ይመስላል የአለም አቀፉ የእርሻና የምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ኩ ዶንጉዩ የሚፈለገዉ ገንዘብ ከሚያዚያ ወር በኋላ ከመጣ ምንም ጥቅም የለዉም ሲሉ የተደመጡት።
እንደ ተባበሩት መንግስታት ዘገባ በአንድ ስኩየር ኪሎሜትር 150 ሚሊዮን አንበጣ ሊሰፍር ይችላል። ኦክስፋም የተባለዉ ድርጅት በቅርቡ ያወጣዉ ዘገባ ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን አንበጣ አንድ ቶን የሚመዝን ሲሆን አንድ ቶን አንበጣ በአንድ ቀን ሁለት መቶ ቶን ዕፅዋትን ሊያጠፉ ይችላል ። ከሰኔ አጋማሽ 2011 ጀምሮ በ57 ሺህ ስኩየር ኪሎሜትር  በኢትዮጵያ የሰፈረዉ የበረሃ አንበጣም  በአሁኑ ወቅት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሲሆን በደረሰበት አካባቢ 90 በመቶ የሚሆነዉን ምርት ማዉደሙን የፋኦ ሪፖርት ያመለክታል።ችግሩ በተለይም በሀገሪቱ ብዙ ምርት ሊሰበሰብባቸዉ በሚችሉት ሸለቋማ ቦታዎች የከፋ መሆኑ ተብራርቷል።  
በመሆኑም የአንበጣ ስርጭቱ በጊዜ ካልተገታ ከዚህ ወረርሽኝ  በፊት ከ 20 ሚሊዮን  በላይ ሰዎች በጎርፍና በድርቅ ለከፋ የረሀብ አደጋ ተጋልጠዉ የቆዩት የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት  እስከሚቀጥለዉ የምርት  ወቅት ድረስ ተመሳሳይ የምግብ ዋስትና ችግር ሊያጋጥማቸዉ  ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት አስጠንቅቋል።በጉዳዩ ላይ የግብርና ምንስቴርን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

Global Ideas Kenia Heuschreckenplage
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis
Kenia Heuschreckenplage
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ