1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ አማራ ክልል

ዓርብ፣ ሰኔ 25 2013

በአማራ ክልል የምሥራቅ ዞን አካባቢዎች በ38 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የአንበጣ መንጋ መከሰቱን ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች አመለከቱ። የየአካባቢው የግብርና ባለሥልጣናት ደግሞ አንበጣው የከፋ ጉዳት እንዳላደረሰ ግን ደግሞ እንድንጠነቀቅ አመላካች ነው ይላሉ። ኅብረተሰቡም በባህላዊ መንገድ ለመገላከል እየሞከረ መሆኑም ተገልጿል። 

https://p.dw.com/p/3vwsA
Kenia Meru | Heuschreckenplage & Landwirtschaft
ምስል Yasuyyoshi Chiba/AFP/Getty Images

«38 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የአንበጣ መንጋ መከሰቱ»

በአማራ ክልል የምሥራቅ ዞን አካባቢዎች በ38 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የአንበጣ መንጋ መከሰቱን ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች አመለከቱ። የየአካባቢው የግብርና ባለሥልጣናት ደግሞ አንበጣው የከፋ ጉዳት እንዳላደረሰ ግን ደግሞ እንድንጠነቀቅ አመላካች ነው ይላሉ። የአንበጣ መንጋው በገብስና ማሽላ ቡቃያዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱና ኅብረተሰቡም በባህላዊ መንገድ ለመገላከል እየሞከረ መሆኑም ተገልጿል። የአንበጣ መንጋ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና ደቡብ ወሎ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቷል፡

በአማራ ክልል ወግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጋዝ ጊብላ ወረዳ የዞማሪያም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትr አቶ ጣፈጠ እሸቴ  ከሰኔ 24 /2013 ዓ ም ጀምሮ የአንበጣ መንጋ በቀበሌያቸው መከሰቱንና በባህላዊ መንገድ ከአካባቢው ለማስወጣት እተደረገ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። በዞኑ የጋዝጊብላ ወረዳ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ተፈራ ሁልዬ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው በ14 ቀበሌዎች ላይ መታየቱንና በአብዛኘው በቁጥቋጦ ቦታዎች ላይ መስፈሩን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ አንበጣውን ከአካባቢው ባህላዊ በሆነ መንገድ ከአካባቢው እያባረረው እንደሆነም ለዶይቼ ቬለ አመልክተዋል፡፡ የጋዝጊብላ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቱ እሸቴ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው በርካታ ቀበሌዎችን እያዳረሰ ቢሆንም ከአቅም በላይ ባለመሆኑ ማኅበረሰቡ እንዲከላከለው እየተደረገ ነው ይላሉ። በአማራ ክልል የኮምቦልቻ እፅዋት ጥበቃ ክሊኒክ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ይመር በአማራ ክልል 4 ዞኖች፣ 17 ወረዳዎች፣ 78 ቀበሌዎች በ37 ሺህ 993 ሄክታር መሬት ላይ የበረሀ አንበጣ መከሰቱን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ተመሳሳይ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋ በ16 ወረዳዎችና በ111 ቀበሌዎች ተከስቶ በሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ