1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የአብይ መንግሥት ያቀዳቸው እርምጃዎች ምን ይሆኑ?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 11 2010

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በያዝንው ሳምንት በእጃቸው የውጭ ምንዛሪ የሚገኝ ኢትዮጵያውያን ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ከማሳሰቢያው በኋላ በርከት ያሉ ደንበኞች ከወትሮው በተለየ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ወደ ባንኮች ማቅናት መጀመራቸው እየተሰማ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በዘመቻ ሊወስድ የሚችላቸው እርምጃዎችስ ምንድናቸው?

https://p.dw.com/p/31iUb

የዐብይ መንግሥት ያቀዳቸው እርምጃዎች ምን ይሆኑ?

በኢትዮጵያ ባንኮች የሚሰሩ ገንዘብ ከፋዮች እና ተቀባዮች ያለፉትን ጥቂት ቀናት በሥራ ገበታቸው ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ ገጥሟቸዋል። በአዲስ አበባ ካሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ውስጥ ከሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች በአንዱ የሚሰሩ ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በትናንትናው ዕለት ከዚህ ቀደም በቀን ከሚሰሩት አማካኝ የውጭ ምንዛሪ የበለጠ ወደ ብር መንዝረዋል። 

አንድ ደንበኛቸው ከያዙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 5,000 ዶላር በእርሳቸው መስኮት ወደ ብር መመንዘራውን የተናገሩት ባለሙያ ግልጋሎቱን ፈልገው ወደ ባንካቸው የሚመጡ ደንበኞች ቁጥር እና ይዘውት የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ መጠን ጭማሪ እንዳሳየ ይናገራሉ።  ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሌሎች አራት የባንክ ባለሙያዎችም በየሚሰሩባቸው ቅርንጫፎች ዶላር እና ዩሮ የመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች ወደ ብር የሚቀይሩ ሰዎች መበራከታቸውን አስተውለዋል። ለባንክ ባለሙያዎቹ ከዶላር ወደ ብር የሚደረገው የምንዛሪ ሞቅ ያለበት ምክንያት አልጠፋቸውም።  

የእግረ-መንገድ ማሳሰቢያ/ ማስጠንቀቂያ

መነሾው ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ከትናንት በስቲያ የውጭ ምንዛሪ እና የብር ክምችት እና ዝውውር ላይ የሰጡት የእግረ-መንገድ ማሳሰቢያ አሊያም ማስጠንቀቂያ ነው። "ሳይነገረን እንዳይባል" ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ጥቂትም ሆነ በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው የሚገኝ ዜጎች በአፋጣኝ ወደ ባንኮች ጎራ ብለው እንዲመነዝሩ አሳስበዋል።

የጠቅላይ ምኒስትር አብይ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት የወጪ ቅነሳን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ገቢራዊ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እንዲህ ባጭር ጊዜ እንደማይፈታ ጠቅላይ ምኒስትሩ ባደረጓቸው ንግግሮች ቢጠቁሙም ቢያንስ በባንኮች እና በጎንዮሽ ግብይቱ መካከል ያለው የነበረው የምንዛሪ ተመን ልዩነት እየጠበበ መጥቷል። ጥቁር እየተባለ በሚጠራው የጎንዮሽ ገበያ እስከ 36 ብር ከ50 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው አንድ የአሜሪካን ዶላር ሰሞኑን ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል።  እንደ ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ ያሉ የቢዝነስ ተንታኞች ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ ያላቸው አመኔታ መሻሻል ለለውጡ ምክንያት እንደሆኑ ያምናሉ። አይ-ካፒታል አፍሪካ የተባለው አማካሪ ተቋም ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ገመቹ "በውጭ ምንዛሪ እጠረት ምክንያት የተፈጠሩ አሳማኝ የሆኑ ከውጪ እቃዎችን ለማምጣት፣ ለመጓዝ እና በኤኮኖሚ አሳማኝ ለሆኑ ምክንያቶች የውጭ ምንዛሪ ከሚፈልጉ ሰዎች ባሻገር የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የፈጠረው በሰዎች ላይ የመተማመን እጥረት ነበረ። ሰው በማንኛውም ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ ለመጓዝም ይሁን ቤተሰቡን ወደ ሌላ ቦታ ለማዞር ብሎ ብሮችን ሰብስቧል። ነጋዴውም ሐብቱን ለማሸሽ ገንዘብ ይዟል። በእርግጥም በሰዎች እጅ ገንዘብ አለወይ ለሚለው በትክክል አለ። ምን ያክል የሚለውን ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።  

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ከጠቅላይ ምኒስትር አብይ መግለጫ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው የሚገኝ ኢትዮጵያውያንን ወደ ባንክ የሚያጉዙ ሁለት ምክንያቶች ይገኛሉ። የመጀመሪያው "በርከት ያለ" ያሉት እና ወደ ኢትዮጵያ ይገባል የተባለው የውጭ ምንዛሪ መጠን ሲሆን ሁለተኛው ከጥቂት ሳምንት በኋላ በተከማቸ ገንዘብ ላይ ይወሰዳል የተባለው ዘመቻ ናቸው። ለመሆኑ ኢትዮጵያውያኑን ለኪሳራ ሊዳርግ የሚችለው በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገሪቱ የሚገባው ከየት ነው? ጠቅላይ ምኒስትሩ ማብራሪያ አልሰጡም። ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝባቸው መንገዶች የሚታወቁ ናቸው የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "ተዓምር" ሊጠበቅ እንደማይገባ ይናገራሉ። "በቅርብ የምናውቀው ከዱባይ ጋር የተስማሙት አንድ ቢሊዮን ዶላር ብሔራዊ ባንክ የሚቀመጥ ነው" የሚሉት አቶ አብዱልመናን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የታቀደው ተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለመዋዕለ-ንዋይ ሥራዎች የታቀደ በመሆኑ ረዥም ጊዜ ይወስዳል ሲሉ ይናገራሉ። በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ይደረጋል የተባለው አንድ ቢሊዮን ዶላር የአገሪቱን ፍላጎት ለማሟላት በቂ አይደለም የሚሉት አቶ አብዱልመናን ጠቅላይ ምኒስትሩ "ፖለቲከኛ እንደመሆናቸው ማስጠንቀቂያ መስጠት አለባቸው። በተግባር ስናየው ግን ብዙም ለውጥ የሚያመጣ ነገር አይደለም" ሲሉ ያክላሉ።  

የባንክ ባለሙያዎቹንም ሆነ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን ቀልብ የሳበው የጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ መንግሥት በተከማቹ ገንዘቦች ላይ በጥቂት ሳምንት ውስጥ እወስዳቸዋለሁ ያላቸው ዘመቻዎች ናቸው። ዘመቻዎቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ዶክተር ገመቹ "ሰዎች መደበኛ ወደሆነው አሰራር እንዲገቡ ማበረታታት፣ ኢ-መደበኛ የሚባለው ግብይት ላይ የሚሔዱበትን ምክንያት ማሳጣት" ቀዳሚው እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ። ሁለተኛው በኢትዮጵያ ሰዎች ሊይዙት የሚችሉ የውጭ ምንዛሪን የሚወስነውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ሁለተኛው የመንግሥት አማራጭ እንደሆነ ያክላሉ።

Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሪ እጁ ከገባበት ዕለት ጀምሮ ከ30 ቀናት በላይ ይዞ መቆየት አይችልም። ከ1,000 ዶላር በላይ ይዘው ወደ አገሪቱ የሚገቡ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ለመንግሥት ሊያሳውቁ ይገባል። አቶ አብዱልመናን "የውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚካሔድባቸው አካባቢዎች ላይ ተቆጣጣሪ ኃይል አቋቁሞ ሱቆችን መዝጋት፣ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደዚሁም እጃቸው ላይ የተገኘ የውጭ ምንዛሪ መውሰድ" የመሳሰሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ተሞክረው እንደነበር ተናግረው ችግሩን ለተወሰነ ጊዜ ግብይቱን ሊያረጋጋው ቢችልም በዘላቂነት ሊፈታው እንደማይችል ግን ባለሙያው ይተቻሉ።

ከአንድ ወር ገደማ በፊት የኢትዮጵያ የፌድራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ በሁለት ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ሊወጣ ሲል መያዙን አስታውቆ ነበር። በርከት ያሉ ባለሙያዎች ሕገ-ወጥ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሲነሳ ከትናንሽ ገንዘቦች ባለፈ ትኩረት ሊያደግባቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ዶክተር ገመቹ  እከሌ እከሌ ብለው የሚጠቁሙት ባይኖርም መንግሥት ግን ማን ላይ ማተኮር እንዳለበት መረጃው እጁ ላይ ሳይኖር እንደማይቀር እምነት አላቸው።

ኢትዮጵያ ቀፍድዶ የያዛትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት አወቃቀር ማስፋት እና የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛኑን ማመጣጠን እንደሚጠበቅባት ባለሙያዎች ይመክራሉ። የጎንዮሽ ግብይቱን መቆጣጠር ጠቀሜታ ቢኖረውም ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ይስማማሉ።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ