1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአርቲስት ሃጫሉ ሕልፈት እና የወጣቶች ምልከታ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2012

ትናንት ሐሙስ በትውልድ መንደሩ የአምቦ ከተማ የቀብር ስነስረዓቱ ተፈጽሟል። የሐጫሉ ሞት እንዲሁ ተራ ሞት ላለመሆኑ ሞቱ የቀሰቀሰው ቁጣና ያሳጣው የሰው ህይወት ፤ የተከተው የንብረት ውድመት ምናልባትም ሃገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባትን ያለመረጋጋት አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/3ekPw
Äthiopien | Sänger und Aktivist Haacaaluu Hundeessaa
ምስል Reuters/T. Negeri

የአርቲስት ሃጫሉ ሕልፈት እና የወጣቶች ምልከታ

ኢትዮጵያ በተሰማሩበት የስራ መስክ ደማቅ ታሪክ ጽፈው ያለፉ ፣ ጀብድ የፈጸሙ፤ ለህዝብ ኑረው ለህዝብ ያለፉ ልጆች አፍርታለች ። ስጋቸውን ቀብሮ የያዘው መቃብር ደማቅ ታሪካቸውን መቅበር አልተቻለውም። ሕያው ስራ ከመቃብር በላይ ነውና። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች ከዶይቸ ቬለ የዕለቱን የወጣቶች አለም መሰናዷችንን ይዘን ቀርበናል። በዝግጅቱ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በተለይ ከወጣቶች አንጻር እንቃኛለን ታምራት ዲንሳ ነኝ አብራችሁን ቆዩ።
 ሰኔ 22 ሰኞ ምሽት በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱን ያጣው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመቃብር በላይ ህያው ታሪክ አስቀርተው ካለፉቱ አንዱ ሆኗል። ትናንት ሐሙስ በትውልድ መንደሩ የአምቦ ከተማ የቀብር ስነስረዓቱ ተፈጽሟል። የሐጫሉ ሞት እንዲሁ ተራ ሞት ላለመሆኑ ሞቱ የቀሰቀሰው ቁጣና ያሳጣው የሰው ህይወት ፤ የተከተው የንብረት ውድመት ምናልባትም ሃገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባትን ያለመረጋጋት አስከትሏል። አርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳ  ድምጻዊ ፣ አክቲቪስት፣ ፖለቲከኛ እና ሌላም ሌላም ነበር ቢባል በተለይ ተወልዶ ላደገበት የኦሮሞ ማህበረሰብ በሕይወቱም ሆነ በሞቱ አንጸባራቂ ኮከብ ሆኖ ታይቷል»ይላሉ ሁኔታዎችን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች። ወጣት ሆኖ በወጣትነት ዘመኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ያንኑ በህይወት እያለ ያደረገውን በሞቱም ቀጥሎ ሲታይ በእርግጥም ተጽዕኖ ፈጣሪ ነበር ያስብላል። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ገና በማለዳ የመጀመርያው ስራው በርካቶችን መማረክ የቻለ ነበር የሚለው ወጣት አለማየሁ ፈቃዱ በስደት ከሚኖርበት እንደሚለው ሃጫሉን የሚያውቀው ገና ሙዚቃን አንድ ብሎ ባሳተመው የበኩር ስራው ነው ይላል። 
በቻይና የ Forein affairs University politics & international relation post gradute ተማሪ የሆነው ጆህን አህመድም እንደ አለማየሁ ሁሉ ሀጫሉን የሚያውቀው በመጀመርያ ሙዚቃው ነው። ጊቤ ገመን ጃለዴ ሰኚ ሞቲ የወጣት ጆን የትውልድ መንደሩን እና አካባቢውን ባህል እና ወግ ከማንጸባረቅ ያለፈ ኦሮሚያን ባንድ ያስተሳሰረ ፣ ከዳር ዳር ያዋደደ ነበር» ይላል።ጊቤ ገመን ጃለዴ ።በሰሯቸው የሙዚቃ ስራዎች ከተወለዱበት ብሔር ውጪ ቋንቋውን ማድመጥ በማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ጭምር ተወዳጅነት ካተረፉ ኢትዮጵያውያን ድምጻውያን መካከል «አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አንዱ ነው » የሚሉ በርካቶች ናቸው ። በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ ድምጻውያን የፍቅር እና የፖለቲካ ቅስቀሳ ዘፈኖችን በማቀንቀን ወጥተዋል፤ ስም እና ዝናም አትርፈዋል። በዚህ ሂደትም ጥቂት የማይባሉት ተገፍተዋል፤ ከፊሉ ሀገር ጥለው ተሰደዋል፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተገደሉ እንዳሉም መረጃዎች ያመለክታሉ። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላመነበት አመለካከት ፊት ለፍት ይጋፈጥ የነበረው ግን ምናልባትም ከሌሎች ይለየዋል ፤ ለህልፈቱም ምክንያት ሆኗል ይላሉ ወጣት ጆህን እና አለማየሁ
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በኢትዮጵያ ከሁለት አመት በፊት በመጣው ለውጥ ቀላል የማይባል ሚና ተጫውቶ እንደነበር ምስክረነታቸውን የሚሰጡ ጥቂቶች አይደሉም ። በተለይ በወርሃ ጥር 2010 ዓ/ም ከሚሊኒየም አዳራሽ በቀጥታ በተላለፈ የቴሌቪዥን ስርጭት በሽለላ የተሞላው የመድረክ ዝግጅቱ ቀስቃሽ መልዕክቶችን ያንጸባረቀ እና በለውጡ ሂደት  ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራ መስራቱን በተለያዩ መድረኮች ስሙ በስፋት ይነሳል።በመድረኩ ላይ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ያቀረበው ሙዚቃ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ለመለካት በወቅቱ የነበረው የሃገሪቱ የብሮድካስት ባለስልጣን ጥር 12/2012 ዓ/ም የሚዲያ አመራሮችን ጠርቶ በገመገመበት መድረክ ላይ ትኩረት ማግኘቱ አንዱ ማሳያ ነበር።በሰሯቸው ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎች ዛሬም ድረስ የሚዘከሩ አንጋፋ እና ቀደምት የሙዚቃ ሰዎች አሉ። ሁሉም በየራሳቸው መንገድ አርአያ ሆነዋል ። በዕድሚያቸው የተጎናጸፏቸው ስኬቶች ከራሳቸው ባሻገር ለተከታዮቻቸው እና በዕዴሚያቸው ለሚገኙ አርአያ ከመሆን ባሻገር ትውልድ ተሻጋሪነታቸውን አረጋግጠዋል። ሃጫሉ ሁንዴሳም በዚሁ መንገድ  አልፏል ይላሉ አስተያየታቸውን የሰጡን ወጣቶቹ።
ለዓላማቸው ጸንተው ፣ ፍቅርን አትርፈው በህይወታቸው ብቻም ሳይሆን በሞታቸው ገዝፈው ከታዩቱ አንዱን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን የዘከርንበት የዛሬው የወጣቶች አለም መሰናዷችን ይህን ይመስል ነበር በዝግጅቱ ሃሳባቸውን ሊያካፍሉን ፈቃደኛ የሆኑትን ወጣት አለማየሁ ፈቃዱ እና ወጣት ጆህን አህመድ አባ ሚልኪን በዝግጅታችን ተከታታዮች ስም እጅጉን አመሰግናለሁ ጤና ይስጥልኝ።