1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአረብ አብዮት 10ኛ ዓመት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2013

ወራት ያስቆጠሩት የማዕድን ሠራተኞቹና የገበሬዎች አድማ፣ ተቃዉሞና አመፅ የመላዉ ቱኒዚያን ሕዝብ ቀልብ ለመሳብ ወይም በፓሪሶች ጠመንጃ፣ዲፕሎማሲና ፖለቲካ የሚረዳዉን የዘይን ኤል አቢዲኒ ቤን ዓሊን አገዛዝ ለመነቅነቅ የተከሩት ነገር የለም።አድማ፣ ተቃዉሞዉ መደፍለቁ ወጣቱን አትክልት ቸርቻሪ ተስፋ ለማስቆረጥ በቂ ነበር

https://p.dw.com/p/3n1Xw
Tunesien Sidi Bouzid Jahrestag Ausschreitungen Arabischer Frühling
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Dridi)

የአረብ ሕዝባዊ አብዮት ዉጤትና አስተጋብኦቱ


የሱዳን ሕዝብ በ30 ዓመት ገዢዉ ላይ ያመፀበትን ሁለተኛ ዓመት፣ የቱኒዚያ ሕዝብ፣ ያ ወጣት ጀግናዉ እራሱ ላይ በለኮሰዉ እሳት፣ ሕዝባዊ ዓመፅ ያቀጣጠለበትን 10ኛ ዓመት ባለፈዉ ሳምንት ዘከሩ።እኩል በተዘከረዉ የሁለቱ ሐገራት አመፅ መካከል የስምንት ዓመት ልዩነት አለ።የስምንት ዓመቱ ልዩነት ከአልጄሪያ እስከ ሊባኖስ፣ ከባሕሬን እስከ የመን፣ ከሶሪያ እስከ ኢትዮጵያ፣ ከግብፅ እስከ ሴኔጋል፣ ከሊቢያ እስከ ቡሪኪና ፋሶ፣ የሁለቱ ሲደመር  የ12ት ሐገራት ሕዝብ  የአመፅ፣አድማ፣ ሠልፍና ዉጤቱ አለ።የ10 ዓመት ያመፅ፣የለዉጥ ታሪክ።10ኛ ዓመቱ መነሻ፣በጎ-መጥፎ ዉጤቱ ማጣቃሻ፣ አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
 የብሪታኒያ ቅኝ ገዢዎች ግብፅ ላይ እግራቸዉን ከተከሉበት ከ1882 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ፣ ያን ሰፊ፣ በረሐማ፤ የአረብ-ሙስሊሞችን ግዛት ከዑስማን ቱርክ ገዢዎች ለመቀማት ያልሞከሩ፣ ያላሴሩ፣ ያልሻጠሩበት ጊዜ፣ያልሞከሩት ደባ አልነበረም።
የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች እንደ ጥሩ ስልት ገቢር ካደረጉት ሴራ፣ በቱርኮች አገዛዝ የተከፉ የአረብ ባለባቶችን አባብለዉ በቱርኮች ላይ ማሳመፅ አንዱና ለዉጤት የበቃላቸዉም ነበር።
የመካዉ ሸሪፍና የሒጃዙ አሚር ሁሴይን ቢን ዓሊ አል-ሐሺሚ ከነብዩ መሐመድ ደም፣ ዘር የሚወርሱ 37ኛዉ ትዉልድ በመሆናቸዉ የቱርኮች አገዛዝ ቢወገድ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ የድፍን አረብ ኸሊፋነትን ይመኛሉ።
የቆስጠንጥኒያ፣ የበርሊንና የተከታዮቻቸዉን ሐገራት ገዢዎችን ባንድ ጎራ፣ የለንደን፣ ፓሪስ፤ዋሽግተንና ደጋፊዎቻቸዉን በተቃራኒዉ ያሰለፈዉ የመጀመሪያዉና «የዓለም» የተባለዉ ጦርነት የፈነዳዉ፣አል-ሐሺሚ ለረጅም ጊዜ ምኞታቸዉ ስኬት፣ በካይሮ የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች የለንደን አለቆቻቸዉን ለማስደሰት በሚደራደሩበት መሐል ነበር።1914።
ጦርነቱ በተጀመረ ባመቱ የብሪታንያ የጦር መሳሪያ፤ወታደራዊ አማካሪና ገንዘብ ወደ ሒጃዝ ይጎርፍ ገባ።ለ600 ዘመን የፀናዉን የቱርክን አገዛዝ ከመካከለኛዉ ምስራቅ ነቅሎ ለብሪታንያ በማስረከቡ ሴራና ዉጊያ ስም-ዝና ያተረፉት ብሪታንያዉ የጦር መኮንንና ሐገር አሳሽ ቶማስ ኤድዋርድ ሎሬንስ (የአረቢያዉ ሎሬንስ) አረብ መስለዉ፣ ከአረብ ጎን ተሰልፈዉ ቱርክን ለመዉጋት አረቢያ የገቡትም ያኔ ነበር። 
ሰኔ 5፣ 1916 የአል-ሐሺሚ ሁለት ወንድ ልጆች በቱርክ አገዛዝ ላይ ማመፃቸዉን በመዲና የቱርክ የበላይ ገዢ ለነበሩት ለጄኔራል ፈቅሪ ፓሻ በግልፅ አስታወቁ።በአምስተኛዉ ቀን አል ሐሺሚ ራሳቸዉ ታላቁ የአረብ አመፅ ያሉትን ዉጊያ በይፋ አወጁ።
አረብ ለአመፅ እንግዳ አይደልም።ከብሪታንያና ከፈረንሳይ ጋር ያበረዉ የአረብ ጦር የቱርክን ጦር  በ1918 ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ጠራርጎ አስወጣ።በጦርነቱ በትንሽ ግምት ሰላሺ የሚገመት አረብ አልቋል።ከቱርክ የተማረከዉን የአረብ ግዛት ግን ብሪታንያና ፈረንሳይ ለሁለት ተቀራምተዉu ተቆጣጠሩት እንጂ አረቦች አልገዙትም።
አል ሐሺሚም «አሚር» የሚለዉን ማዕረግ ንጉስ በሚል ከመቀየር ባለፍ ለከሊፋነት አልበቁም።ንጉሥነቱንም፣ ብሪታንያዎች አዲስ ባፈሩት ጠንካራ ታማኝ ወዳጃቸዉ በቢን ሳዑድ  በ1924 ተቀምተዉ ከነምኞታቸዉ------አረብ እንደሚለዉ «መዓሠላማ።»
አረብ ለዓመፅ እንግዳ አይደለም።በ1920 የኢራቅ፣ በ1936 የፍልስጤም ሕዝብ የብሪታንያ አገዛዝን በመቃወም አምፀዉ ነበር።የሁለቱም ሕዝብ በየዘመኑ በነበረዉ የብሪታንያ ጨካኝ ጦር ተጨፈጨፈ።አመፁምጨርሶ ባይጠፋ ተዳፈነ። ኢራቅ ዛሬ ወድማለች።ፍልስጤም ዛሬም ያምፃል።አረብ ለዓመፅ እንግዳ አይደለም።ጭቆናና ግፍ እስካለ አመፅ፣ አረብ ይሁን አፍሪቃ ወይ ሌላ ሥፍራ ሊቆም አይችልም-ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን።
                                        
ታሪክ ኤል ጠይብ መሐመድ ቡአዚዚ ጥንት ከመዲና እስከ ባግዳድ፣ከደማስቆ እስከ እየሩሳሌም ለነፃነት የተደረጉ አመፅ-ተቃዉሞዎችን ወይም ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ካይሮ፣ ሰነዓ፣ ባግዳድ፣ ደማስቆ፣ ካርቱም ትሪፖሊና ሌሎች ሥፍራዎች ጨቋኝ አገዛዞችን በመቃወም የተደረጉ ትግሎችን ወይም መፈንቅለ መንግስቶችን ለማስተንተን ፖለቲካዊ-አካዳሚያዊ ዕዉቀት ብቃት-ምቾቱም በርግጥ የለዉም።
ይሁንና በ2008 እዚያዉ ቱኒዚያ የጋፍሳ  ማዕድን ሠራተኞች የመቱትን አድማ፣ በ2010 የሲዲ ቡዚድ ግዛት ገበሬዎች ያደረጉትን ተቃዉሞ ሰልፍና የመንግስትን የጭካኔ ርምጃ በቅርብ ተከታትሏል።እንዲያዉም የቅርብ ጓደኞቹን የሚጠቅሱ ተንታኞች ያ አትክልት ቸርቻሪ ወጣት ተስፋ የቆረጠዉ በገበሬዎቹ ሠልፍና ተቃዉሞ ከተሳተፈ በኋላ ነዉ ይላሉ።
ተሳተፈተም አልተሳተፉ ወራት ያስቆጠሩት የማዕድን ሠራተኞቹና የገበሬዎች አድማ፣ ተቃዉሞና አመፅ የመላዉ ቱኒዚያን ሕዝብ ቀልብ ለመሳብ ወይም በፓሪሶች ጠመንጃ፣ዲፕሎማሲና ፖለቲካ የሚረዳዉን የዘይን ኤል አቢዲኒ ቤን ዓሊን አገዛዝ ለመነቅነቅ የተከሩት ነገር የለም።አድማ፣ ተቃዉሞዉ መደፍለቁ ወጣቱን አትክልት ቸርቻሪ ተስፋ ለማስቆረጥ በቂ ነበር።በዚያ ላይ ፖሊስ  ጉቦ ካልከፈልክ ብሎ የአትክልት ማዞሪያ ጋሪዉን ሲቀማዉ ደግሞ ብቻዉን ማድረግ የሚችለዉን ግን ከባድ እርምጃ ለመዉሰድ ወሰነ።እራሱን በእሳት አጋየ።ታሕሳስ 17፣ 2010።
 መሐመድ ቡአዚዚ እራሱ ላይ የለኮሰዉ እሳት የወጣቱን ሕይወቱን ሲያጠፋ፣ የቱኒዚያ፣ የግብፅ፣ የሊቢያ የየመን እያለ የድፍን አረብን ሕዝብ በተለይም የወጣቱን አመፅ አቀጣጠለ።ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ 10ኛ ዓመቱ።በ10 ዓመት 12 የአረብና የአፍሪቃ ሐገራትን ባዳረሰዉ ሕዝባዊ አመፅ ሺዎች ተገድለዋል።ብዙዎች ቆስለዋል።አመፁ ባሕሬን ላይ በታንክ፣ ዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌትና ሞሮኮ ላይ በገንዘብና ሚኒስትሮችን በመቀያየር ተደፍልቋል።
ሊቢያ፣ ሶሪያና የመንን ደግሞ ከሉዓላዊ ሐገርነት ወደ ጉልበተኞች መፈንጪያነት አዉርዷል።ከሞት፣ ስደት፣ስቃይ ለተረፈዉ ለየሐገሩ ሕዝብ ሠላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ እኩልነት፣ የምጣኔ ሐብት ትሩፋት ማስገኝት-አለማስገኘቱም እንደየተመልካቹ የሚበየን ሆኗል።
ግብፃዊቱ ደራሲ አሕዳፍ ሶይፍ እንደሚከራከሩት ግን ስለ ሕዝባዊዉ አብዮት በጎ መጥፎ ዉጤት ለመናገር ጊዜዉ አጭር ነዉ።ለዉጡም ገና በሒደት ላይ ነዉ።«ከሁሉም በላይ»፣ ይላሉ ደራሲዋ ሕዝቡ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በኖረበት መንገድ መኖር እንደማይችል፣በጨቋኝ ገዢዎች ላይ ማመፁን መግታት እንደማይቻልም ያመለከተ፣ ወደፊትም የሚቀጥል ነዉ።አቶ ዩሱፍ ያሲንም በዚሕ ይስማማሉ።
 አቶ ዩሱፍ አክለዉ እንዳሉት የነመሐመድ ቡአዚዚ ጥያቄና ምኞት ለዉጤት አልበቃ ይሆናል።ጨቋኝ ገዢዎች ግን እንደ ከዚሕ ቀደሙ በመፈንቅለ መንግስትና በአማፂያን ዉጊያ ሳይሆን በሕዝብ አመፅ መወገዳቸዉ አያጠያይቅም።
 የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የሰበአዊ መብትና የመናገር ነፃነት ጥያቄን ያነሳዉ ከአረቦቹ ቀደም ብሎ በ1990ዎቹ ነበር።ይሁንና በ1990ዎቹ በየሐገሩ በተደረጉ ንቅናቄዎችና በማስመሰያ ምርጫዎች ሥልጣን የያዙ ኃይላት ራሳቸዉ ከቀዳሚዎቻቸዉ ብዙም የማይሻሉ አንዳዱጋም የባሱ በመሆናቸዉ የሕዝቡ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ አላገኘም።ጥያቄ ትግሉም አልተቋረጠም።
የአረቦች ሕዝባዊ አመፅ፣ ጀርመናዊዉ የአፍሪቃ ፖለቲካ  አጥኚ ሮበርት ካፔል እንደሚያምኑት ከሰሐራ በረሐ በታች ያሉ የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብምን ለማነቃቃት ጠቅሟል።
                                         
«አፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ዉስጥ፣ለተሻለ ዴሞክራሲ፣ለመናገር ነፃነት፣ ለበለጠ ተሳትፎ የተደረጉና  የሚደረጉ ንቅናቄዎች ሰሜን አፍሪቃና መካከለኛዉ ምሥራቅ በተደረጉ ተመሳሳይ ንቅናቄዎች የተነቃቁ ወይም የተጠናከሩ ይመስለኛል።(እንቅስቃሴዎቹ) የአፍሪቃ  አምገነን ገዢዎችን፣ ጭቆናን፣የፕሬስ  አፈናን፣ ሰብአዊ መብትን  ለማስወገድ የሚደረገዉ ትግል  አካልና ሒደት ናቸዉ።የዐረቡ ሕዝባዊ አመፅ የአፍሪቃዉያንን የትግል ሒደትና እንቅስቃሴ አጠናክሯል።»
ሱዳንን ከአረብ ቀይጠን፣ ከቡርኪና ፋሶ እስከ ዚምባቡዌ፣ ከሴናጋል እስከ ኢትዮጵያ የታዩ ሕዝባዊ አመፅና ለዉጦች፣ ተንታኞች እንደሚሉት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ከአረቦቹ ሕዝባዊ አብዮቶች ጋር የሚመሳሰሉ ምናልባትም የአረቦቹን አስተምሕሮ የተከተሉ ናቸዉ።የዋጋዱጉ፣ የዳካር፣ የአዲስ አበባና የሐራሬን ገዢዎች  ነቅሎ የጣለዉ ሕዝባዊ አመፅ የየሐገሩን ሕዝብ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት፣ የምጣኔ ሐብት ተጠቃሚነት ፍላጎቱን ማሟላት-አለማሟላቱ ግን ያዉ እንደ አረቦቹ ሁሉ ሲጠየቅ፣ሲያከርክር፣ ሲያነጋግር ተጨማሪ ሕይወት፣ አካል ሐብት ሲያስገብር  ዓመታት ማስቆጠሩ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።

Skulptur Selbstverbrennung Mohammed Bouzizi Sidi Bouzid Tunesien
ምስል Reese Erlich
Militär Gewalt Ägypten
ምስል AFP/GettyImages
Ägypten arabische Frühling Frau mit Handy und Kamera
ምስል Imago
Symbolbild Arabischer Frühling Tunesien
ምስል picture-alliance/AP Photo/Salah Habibi

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ