1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካፒቶል፣ የአሜሪካ ዴሞክራሲና ፈተናዉ

ሰኞ፣ ጥር 3 2013

ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ ጊዜ ጀምሮ የልዕለ ኃያሊቱን ሐገር ነባር የፖለቲካ ይትበሐል፣ሕግ-ደንብን፣ የዓለምን የጋራ ትብብር፣ ስምምነት፣ ዉልን የመነቃቀሩት ዶንልድ ትራምፕ የመረጣቸዉን ሕዝብ ከፋፈሉት። አራት ዓመት የተገዛ፣ የተከተላቸዉ ሕዝብ አንመርጥም እንቢኝ ሲላቸዉ ግን እንቢኝ አሉት።

https://p.dw.com/p/3nnQL
USA Washington | Pro-Trump Unterstützer stürmen Kapitol
ምስል Hiroshi Tajima/AP/picture alliance

ካፒቶል፤ የአሜሪካ ዴሞክራሲና ፈተናው አብነት

ቶማስ ጃፈርሰን በሮሞቹ የጁፒተር ኦምቲሙስ ማክሲሙስ ሙክራብ ስም በላቲኑ ቋንቋ ካፒቶል ብለዉ የመሰየሙበት ምክንያት ለብዙ አጥኚዎች ብዙ ነዉ።ለጥንክሬ፣ ግዝፈት፤ዉበት ማራኪነቱ ግን የፔሪ ሻርልስ ለ ኤንፋን፣የዊኪያም ቶርንቶን፣የቤንጃሚን ሔንሪ ላትሮብ እና የብዙ መሐንዲሶች የሥነ-ሕንፃ ዕዉቀት፣ብልሐት፣የብዙ ሺ ባሮች፣ደም-ላብ፣ ፈስሶበታል። የነኮንስታንቲኖ ብሪሚዲ የየጥበብ ክሒል አሽሞንሙኖታል።ጆርጆ ዋሽግተን መሠረቱን ጣሉ፣ጆን አዳምስ መረቁት።ከቴዎዶር ሴዲግዊክ እስከ ናንሲ ፖሎሲ የመሯቸዉ ሚሊዮነ-ሚሊዮናት እንደራሴዎች ሰፊ-ደሐይቱን ሐገር ከቅኝ ተገዢነት፣ ዓለምን ወደ አስገበረ ታላቅነት፣ ከዘር ታባይነት ወደ ዴሞክራሲዊ ቀንዲልነት ያንቻረራትን ሕግጋት አርቅቀዉ አፅድቀዉበታል። በ1814 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጄነራል ሮበርት ሮስ የሚያዙት የብሪታንያ ጦር በከፊል አጋየዉ። በ207ኛዉ ዓመት ዘንድሮ ትራምፕ አስወረሩት። ሕይወት፣ ሐብት ንብረት አስጠፉበት። ካፒቶል። የአሜሪካ ዴሞክራሲና ፈተናዉ አብነት። 

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ባለፈዉ ሮብ ካፒቶል ሕንፃን መዉረር፣ ሕይወት፣ ሐብት ንብረት፣ ሰነድ ማጥፋቸዉን የዓለም፣ በጣሙን ከአትላንቲካ ባሕር ማዶ-ለማዶ የሚገኙ የአዉሮጳና የአሜሪካ ፖለቲከኞች የፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ቋንቋ በሚፈቅደዉ ልክ ተቃወሙ፣አወገዙትም።የአፍሪቃ፣ የእስያ፣ የደቡብ አሜሪካ ተራ ዜጋ በየሐገሩ ማአለት-ወሌት ከሚያዉ ጭቆና ፣ ማጭበርበር  ሁከት ጋር እመሳሰለዉ። የሴኔጋሉ ተማሪ ቡበከር ዳዊ አንዱ ነዉ።

                        

«አሜሪካ የሆነዉ፣ እዚሕ አፍሪቃ ዉስጥ በየጊዜዉ የሚፈፀም ነዉ።ሥልጣን ላይ የሚገኙ ፕሬዝደንቶች በምርጫ፣ በተቀናቃኞቻቸዉ  መሸነፋቸዉን አይቀበሉም።አፍሪቃ ዉስጥ በየጊዜዉ የሚታይ ነዉ። አሜሪካ የዴሞክራሲ ሐገር እንደሆነች በየጊዜዉ ይነገራል። አሁን ግን ዴሞክራሲ የኛም ጭምር ለአደጋ መጋለጡን አየን።»እርግጥ ነዉ የትራምፕዋ አሜሪካ-የድፍን አሜሪካ ሁለንተናዊ ነፀብራቅ እንደሆነች የሚያምኑ፣ የሚከራከሩ፣ የሮቡ ወረራ ለየእምነት መከራከሪያቸዉ ማረጋገጪያ እንደሆነ ያስታወቁ፣ ያላገጡም ብዙ ናቸዉ። የአሜሪካን ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ ሥርዓትን የሚመኘዉ ደግሞ ከእንግዲሕ፣ አፍሪቃዊዉ ወጣት እንዳለዉ «ምንቀረን» ዓይነት ይል ገባ።

USA | Trump-Supporter Richard Barnett
ምስል Saul Loeb/AFP/Getty Images

                        

«ዩናይትድ ስቴትስ የዕድገትና የዴሞክራሲ ናሙና ነበረች።ከእንግዲሕ ግን የዴሞክራሲ ምሳሌ ልትሆን አትችልም።»

የአሜሪካ የምጣኔ ሐብት ዕድገት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓቷ መሠረት ሕገ-መንግስቷ ነዉ። ዓለም በቅጡ የደረጀ፣ በምዕራፍ-አንቀጾች የተከፋፈለ፣ በወጉ የተሠነደ ሕገ መንግሥት ያወቀችዉ በ1789 ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥና ከዩናይትድ ስቴትስ ነዉ።እነ ጀምስ ሜድሰን ትንሹ ለዚያች ሰፊ፣ቅኝ ተገዢ፣ የቅይጦች ሐገር ያበረከቱት ሠነድ «We the People (እኛ ሕዝቡ ብንለዉ ያስኬዳል) በሚሉት ሶስት ቃላት ይጀምራል።

 

የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) እንደሚበይነዉ ሶስቱ ቃላት «የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የቆየመዉ ሕዝቡን ለማገልገል መሆኑን ያረጋግጣሉ።ለሕዝብ የቆመዉ ሕገ-መንግስት ከዘመኑ ሒደት፣ ከአሜሪካኖች ዕዉቀት፣ ዕድገት፣ ከሁሉም በላይ ከየዘመኑ ሕዝብ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም 27 ጊዜ ተሻሽሏል።

የመጀመሪያዎቹ ሶስት ቃላት ግን ዛሬም እዚያዉ ናቸዉ። ሕገ-መንግስቱ መጀመሪያ ሲፀድቅ ከነበሩት ሰባት ምዕራፎች የመጀመሪያዉ፣ የሁለቱን ምክር ቤቶች (የሕግ መመሪያና መወሰኛዉ) ኃላፊነቶችና ምግባርን ይደነግጋል።

የሁለቱ ምክር ቤቶች እንደራሴዎች ከ1800 ጀምሮ፣ በዚያ ሕገ-መንግስት ላይ ተመስርተዉ ሌሎች ሕግና ደንቦችን የሚያረቁ፣የሚያፀድቁ፣ ሹመት፣ሽረትን፣ በጀት፣ሥራ ማስኬጂያን የሚያፀድቁት እዚያ ሕንፃ ዉስጥ  ነዉ። ቶማስ ጃፈርሰን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን ካፒቶል እንዲባል የተሟገቱለት፣ ያ ዋሽግተን ዲሲ ኮረብታላይ የተሰደረዉ ሕንፃ የሁለቱን ምክር ቤቶች ተጣማሪ ጉባኤ ሕዳር 17 1800 ካስተናገደ ወዲሕ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ሥርዓት ማዕከል፣ ለአብዛኛዉ ዓለም አብነት ተደርጎ ይታያል።

BdTD USA | Demonstranten im Kapitol | Polizei mit Blendgranaten
ምስል Leah Millis/REUTERS

 

በ1814 የቀድሞዋ የአሜሪካ ቅኝ ገዢ የብሪታንያ ጦር የአዲሲቱን የአሜሪካ አዲስ ጦርን ድል አድርጎ ያን ግዙፍ ሕንፃ በከፊል አጋይቶት ነበር።ከስኮትላንድ-ብሪታንያ እናት የሚወለዱት ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ በ207ኛዉ ዓመት ዘንድሮ አስባበሩት፣ አስወረሩት፣ አስመዘበሩትም። «ወደፈለጋችሁበት እንጓዛለን።እኔ እንደሚሰለኝ ግን አሁን ወደ ካፒቶል እንሔዳለን። ጀግና ሴናተሮችንና የምክር ቤት አባላትን እናበረታታለን።»

USA Sturm gegen US-Capitol | Gegenproteste
ምስል Essdras M. Suarez/ZUMA Wire/picture alliance

ደጋፊዎቻቸዉም ጨፈሩ፣ዘመሩ፣ እንደ አሜሪካኖቹ ደንብ እስከ ደም ጠብታ ሊፋለሙ ፎከሩም።«በጥርስ ጥፍራችን እንፋለማለን።ባይደን በዓለ ሲመታቸዉን ቢያከብሩ እንኳ ይሕ የመጨረሻዉ አይደለም። መፋለማችንን አናቆምም።ማንንም ይሹሙ፣ ማንን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ፕሬዝደንታችን ትራምፕ ናቸዉ።»

ከፖለቲካዉ ጡቃንጡቅ፣ ከረቂቁ ሕግ ትርጓሜ፣ ከገቢራዊነቱ እንዴትነት ይልቅ ዶላር የማጋበስ፣ የማትረፍ፣ መክበርን ንግድ የተካኑበት ትራፕ በ2016 የተመረጡት እንደ አሜሪካ ወግ፣ እንደ ሕገ-መንግስቷ ድንጋጌ በሕዝብ ድምፅ ነበር።

ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ ጊዜ ጀምሮ የልዕለ ኃያሊቱን ሐገር ነባር የፖለቲካ ይትበሐል፣ሕግ-ደንብን፣ የዓለምን የጋራ ትብብር፣ ስምምነት፣ ዉልን የመነቃቀሩት ዶንልድ ትራምፕ የመረጣቸዉን ሕዝብ ከፋፈሉት።አራት ዓመት የተገዛ፣ የተከተላቸዉ ሕዝብ አንመርጥም እንቢኝ ሲላቸዉ ግን እንቢኝ አሉት።

                      

«እጅ አንሰጥም።አንቀበልም።ሊሆን አይችልም።ስርቆት ሲቀየጥበት አትቀበሉትም።»አራት ዓመት የከፋፈሉትን ሕዝብ ከሕዳሩ ምርጫ በፊት ጀምሮ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ቀሰቀሱት። ሲሸነፉ ለአደባባይ ሰልፍ ጠሩት፣ ከደላላነት ወደ ፕሬዝደትነት በተመነደጉበት የአሜሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት አብነት ላይ አዘመቱት። ዳጋፊያቸዉም ፎክሮ አልቀረም።የጆርጅ ዋሽግተንን ቅርስ፣ የጆን አዳምስን መታሰቢያ፣ የቶማስ ጃፈርሰንን ስጦታ፣የአብረሕም ሊንከንን መለያ ረመረመዉ።ሮብ።

Washington | Sturm auf Kapitol
ምስል Stephanie Keith/REUTERS

ኦስትሪያዊዉ-አሜሪካዊዉ ዕዉቅ የፊልም ተዋኝና የቀድሞ የካሊፎርኒያ አገረገዢ አርኖልድ ሽቫርሰኔገር እንደ ትራምፕ ሁሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል ነዉ። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ማግስት በ1947 የተወለደዉ ሽቫርሰኔገር የሮቡን ወረራና ጥፋት ከፖለቲከኝነቱ ይልቅ እንደተዋኝነቱ ገለፀዉ።

                       

«ያደግኩት ኦስትሪያ ነዉ። ስለ ክርስታል-ናኽት ወይም ስለ መስተዋት መሰባበሪያ ሌሊት በደንብ አዉቃለሁ። በ1938 ካሁኖቹ «ኩሩ ልጆች» ጋር የሚመሳሰሉት ናዚዎች የአይሁድን ንብረት የሰባበሩበት ሌሊት ነዉ። ሮብም፣እዚሕ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ መስተዋት የተሰባበረበት ቀን ነዉ።»

የትራም ደጋፊዎች የሰባበሩት በር፣ መስኮት፣ መስተዋት ብቻ አይደለም።» እያለ ቀጠለ የተርምኔተሩ ተዋኝ።«መስተዋት የመሰባበሩ ጥቃት የደረሰዉ በዩናይትድ ስቴትሱ ካፒቶል ላይ ነዉ። ይሁንና መንጋዉ፣ የካፒቶል መስኮቶችን ብቻ አይደለም የሰባበሩት።ያጠፉት፣ በእርግጠኝነት የምናምንባቸዉን አስተሳሰቦች ጭምር ነዉ። የሰባበሩት የአሜሪካን ዴሞክራሲ የሚያስተናግደዉን ሕንፃ በሮች ብቻ አይደለም፣ ሐገራችን የተመሠረተችበትን መርሆዎች ጭምር ነዉ የመነቃቀሩት።»

 

በጥቃቱ አምስት ሰዎች ተገድለዋል። ብዙ ቆስለዋል። የጠፋዉ ሐብት-ንብረት ሰነድ መጠን በዉል አልታወቀም። ፖሊስ እስካሁን ድረስ ከ50 በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን አስታዉቋል። የጥቃት ጥፋቱ ቀስቃሽ፣ የአጥፊዎቹ አደራጅ፣ አዝማች፣ ምናልባትም በገንዘብ ደጋፊዉ ዶናልድ ትራምፕን ለመክሰስ   የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት እየገፋፉ ነዉ። የኒዮርኩ ከንቲባ ቢል ደ ብላሶ አንዱ ናቸዉ።

                       

«ዶናልድ ትራምፕ አሁኑኑ መሰናበት አለባቸዉ።እንዲሕ ዓይነት ከሐዲ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ እንዲሕ አይነት ሁከት እስከ መቀስቀስ ድረስ አቅሉን የሳተ ሰዉ በኑክሌር ቁልፎች ላይ ጣቱን ሊያሳርፍ አይገባዉም።»

ይበሉጂ ሰዉዬዉ ዛሬም 6 ሺሕ የኑክሌር ቦምብን ጨምሮ ዓለምን የሚያንቀጠቅጠዉ የአሜሪካ ምርጥ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ናቸዉ።የብቸኛዋ ልዕለ ኃያል ሐገር ፕሬዝደንት ናቸዉ። ዶናልድ ጆን ትራምፕ። የብሪታንያ ጦር በ1814 ካፒቶልና ዋይት ሐዉስ ላይ የለኮሰዉ እሳት በሰዓታት ልዩነት ዉስጥ በጣለዉ ዶፍ ዝናብ ጠፍቷል። የትራምፕ ደጋፊዎች ሽቫርሰኔገር እንዳለዉ በዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ የተቃጣዉን ጥቃት ለማጥፋት የተፈጥሮ ነጎድጓድን እንጠብቅ ይሆን?

US-Capitol | Wiederaufnahme der Sitzung | Nancy Pelosi
ምስል Jim Lo Scalzo/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ