1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ማዕቀብ

ሰኞ፣ ግንቦት 16 2013

ብሊንከን «ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ» ያሉት ወገን የሚያደርገዉን አናወቅም መንግስታቸዉ ግን በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት ባለስልጣናት፣በጦር አዛዦች፣ «መደበኛ ያልሆነ» ባሉት የአማራ ኃይል አዛዦችና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይል አዛዦችና አባላት እንዲሁም በየቅርብ ቤተሰቦቻቸዉ ላይ የመግቢያ ፍቃድ ወይም የቪዛ እገዳ ጥሏል።

https://p.dw.com/p/3tt0g
Äthiopien - Besuch des Präsidenten Isayas Afewerki aus Eritrea
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Ayene

ዩናይትድ ስቴትስ የጣለችዉ ማዕቀብ


ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነፃ የወጣችበትን ወይም የተገነጠለችበትን 30ኛ ዓመት ዛሬ አክብራለች።ኢትዮጵያ ደግሞ ያኔ የአስመራና የአዲስ አበባ አብያተ-መንግስታትን በተቆጣጠሩት ኃይላት አገላለፅ «ከደረገ-ኢሠፓ» አገዛዝ «ነፃ የወጣችበትን» 30ኛ ዓመት  የፊታችን አርብ ታስባለች።ለኤርትራና ለኢትዮጵያ «ነፃነት» ላሉት መከፋፈልና ለደርግ ሥርዓት መዉደቅ የጋራ ግንባር ፈጥረዉ በትንሽ ግምት ለ17 ዓመታት የተዋጉት ኃይላት ባድመ ላይ ሌላ ጦርነት ከገጠሙ 21ኛ ዓመት ደፈኑ።ሁሉም የሆነዉ ግንቦት ነበር።ደርግን ከማዳከም ኤርትራን እስከ መገንጠሉ፣ ከየጦርነት-ግጭቱ እስከ ዕርቅ-ድርድሩ የኢትዮ-ኤርትራን ፖለቲከኞች ስትረዳ-ስትቃወም፣ ሥትደግፍ-ሥትነቅፍ ዓመታት ያስቆጠረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዘንድሮ ግንቦት በሁለቱ ሐገራት ባለስልጣናት፣ በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያና የትግራይ ገዢዎችና በአማራ የፀጥታ ኃይል አዛዦች ላይ ማዕቀብ ጣለች።ትናንት።የማዕቀቡ ምንነት፣ምክንያት፣ ፍትሐዊነቱ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።ለሁለት እንግዶቻችን አራት ጥያቄዎች እናነሳለን።ጠብቁን።
                                        
የብሊንከን ማስጠንቀቂያ፣ የኩን መልዕክት፣ የፌልትማን ዲፕሎማሲ አጉዞ አጉዞ እዚሕ ላይ ደረሰ።ማዕቀብ።ዋና ሰበቡ የትግራይ ክልልን የጎዳዉ ጦርነት ነዉ።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እንደፃፉት  ትግራይ ዉስጥ ያለዉ ቀዉስና የኢትዮጵያን ልዑላዊነት፣ ብሔራዊ አንድነትና የግዛት አንድነትን የሚያሰጉ ሌሎች አደጋዎችን ዩናይትድ ስቴትስን በጅጉ ያሳስቧታል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉን ግድያ፣ አስገድዶ  ማፈናቀል፣ የወሲብ ጥቃትን፣ ለሰላማዊ ሕዝብ አገልግሎት በሚዉሉ በዉሐ፣ በሕክምና ማዕከላትና በሆስፒታሎች ላይ የሚደርስ ጥፋትና ዘረፋን ዩናይትድ ስቴትስ ታወግዛለች።ኤርትራ ጦሯና ከኢትዮጵያ ለማስወጣት የገባችዉን ቃል እንድታከብርም ሚንስትሩ ጠይቀዋል።
ይሁንና «የትግራይ ክልልን ያወደመዉን ጦርነት «በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተፋላሚ ኃይላት የወሰዱት ሁነኛ እርምጃ» የለም-እንደሚንስትሩ።
«ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እርምጃ የሚወስድበት ወቅቱ አሁን ነዉ-ብለዋል ብሊንከን።ብሊንከን «ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ» ያሉት ወገን የሚያደርገዉን አናወቅም፣ መንግስታቸዉ ግን በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት ባለስልጣናት፣ በጦር አዛዦች፣ «መደበኛ ያልሆነ» ባሉት የአማራ ክልል ኃይል አዛዦችና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይል አዛዦችና አባላት እንዲሁም በየቅርብ ቤተሰቦቻቸዉ ላይ የመግቢያ ፍቃድ ወይም የቪዛ እገዳ ጥሏል።
ዩናይትድ ስቴትስ ምግብና መድሐኒትን ከመሰሳሰሉ የሰብአዊ ርዳታዎችና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይጠቅማሉ ከምትላቸዉ ድጋፎች ዉጪ ለኢትዮጵያ የምትሰጠዉን የምጣኔ ሐብት፣ የፀጥታና የወታደራዊ ድጋፍም አቁማለች።
ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ ሐገራት ከምትሰጠዉ ርዳታ ከፍተኛዉን የምታገኘዉ ኢትዮጵያ ነበረች።በዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል።
እርምጃዉ ተገቢ ይሆን? በኪል-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰርና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አወል ቃሲም አሎ፣ የአዉሮጳና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት ትግራይ ዉስጥ ይፈፀማል ያሉት ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም፣ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ፣ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ «ያለሰለሰ» ያሉትን ጥሪ፣ጥረትና ግፊት ሲያደርጉ መክረማቸዉን ይዘረዝራሉ።እና ርምጃዉ «ተገቢ ነዉ» ባይ ናቸዉ።
በብራስልስ-ቤልጂግ የዶቸ ቬለ ዘጋቢ ገበያዉ ንጉሴም ልክ እንደ ዶክተር አወል ሁሉ  ምዕራባዉያን መንግስታት ተከታታይ ግፊትና ጥረት ማድረጋቸዉን ይጠቅሳል።ማዕቀቡን ግን «እጅ መጠምዘዢያ» ብሎታል።
የአዉሮጳ ሕብረት ባለፈዉ መጋቢት በኤርትራ የሥለላ ወይም የደሕንነት ባለስልጣናት ላይ ተመሳሳይ ማዕቀብ ጥሎ ነበር።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» ሲሉም የአሜሪካን አቋም ቀድመዉ የሚጋሩትን የአዉሮጳ ሐገራት ማለታቸዉ እንደሁ  ለብዙዎች እንግዳ አይደለም።
ያሁኑ ማዕቀብ አዉሮጶች የጀመሩት አሜሪካኖች የደገሙት ምናልባት አዉሮጶች የሚያሰልሱት ይሆን ይሆን? ተመሳሳይ ነዉ መልሳቸዉ።ከዶክተር አወል እንጀምር።
ገበያዉም አዉሮጳና አሜሪካ ተናቦ ነዉ የሚሰራዉ ይላል።
                                   
የኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊዎች ሰሞኑን በሚያሰራጩዋቸዉ መልዕክቶች የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት የጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት ላይ ጠንካራ ግፊት ያደረገና ትናንት የወሰደዉን እርምጃ ለመዉሰድ የሚዝተዉ አስተዳደሩ በፕሬዝደንት ቢል ክሊንተንና በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዘመን ሥልጣን ላይ በነበሩ ፖለቲከኞችና ዲፕሎማቶች ስለተሞላ፣ እነዚያ ባለስልጣናት ደግሞ የሕወሓት ወዳጆች፣ የሽዕቢያ ጠላቶች ስለነበሩ ነዉ ብለዉ ይከራከራሉ።
የዶክተር አዉል አስተያየት «የአሜሪካ መርሕ በባለስልጣናት ፍላጎት ብቻ አይመራም» ዓይነት የሚል ነዉ። ገበያዉ ንጉሴ የባይደን አስተዳደር ባለስልጣናት የሕወሓት «ወዳጅ» መሆናቸዉ ከታወቀ የነሱን ፍላጎትና እምነት ለማስቀየር የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ያደረጉትን ጥረት ይጠይቃል።የጥረቱ ዉስንነት ማረጋገጪያዉ ደግሞ ገበያዉ እንደሚለዉ  የአሜሪካኖች ርምጃ ነዉ።
                                          
ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ማዕቀብ የተጣለችዉ የፍልስጤሟ ግዛት ጋዛ፣ እስራኤል ከአየር-ከምድር ካዘነበችባት እቶንና ፍላፃ ተንፈስ፣ የነዋሪዎቹ እልቂት፣ጩኸት፣ስቃይ፣ሽሽት ገለል ቀለል ባለ ሳልስት መሆኑ ነዉ።የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ  እስራኤልን ባብዛኛዉ በጓዳ ሠራሽ  ሮኬት በመምታቱ የአሜሪካንን እጅግ ዘመናይ ጦር መሳሪያ የታጠቀዉ የእስራኤል ጦር በሰላማዊ ፍልስጤሞች ላይ ሳይቀር  11 ማዓልት ወሌት ቦምብ ሚሳዬሉን ሲያጎርፍ እስራኤልን የደገፈችዉ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ጦርነትና ግጭት ይሕን ያሕል የተጨነቀችዉ፣ አሜሪካኖች ኢትዮጵያዉያንን ከፍልስጤሞች በላይ «ስለሚወዱ» ይሆን?
የኢትዮጵያ መንግስት አፀፋን እንዲነግሩን የሐገሪቱን ጠቅላይ ሚንስቴር ፅሕፈት ቤት እና የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለስልጣናትን በስልክ ለማግኘት እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ ሞክረን ነበር።እንደተለመደዉ ስልካቸዉን አያነሱም።የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፅሕፈት ቤት በፌስ ቡክ ገፁ ባሰፈረዉ ሁለት ገፅ የእንግሊዝኛ ፅሁፍ እንዳለዉ ግን  የአሜሪካኖችን እርምጃ ለኢትዮጵያ «አሳዛኝና ተቀባይነት የሌለዉ» ብሎታል።
መግለጫዉ የኢትዮጵያና የዩናይትድ ስቴትስን ግንኙነት «ታሪካዊና በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ» ይለዋል።ለዚሕ  ግንኙነትም «ኢትዮጵያ  ትልቅ ሥፍራ ትሰጣለች።» ማዕቀቡ ግን  »የሁለቱን ሃገራት የረዥም ዘመን ጠቃሚ  ግንኙነት በእጅጉ የሚጎዳና በጣም አሳዛኝም ነው» ይላል።ዩናይትድ ስቴትስ የጣለችዉ የቪዛ ማዕቀብ በቀጥታ የሚነካቸዉን ባለስልጣናትና የቤተሰቦቻቸዉን ማንነት በዝርዝር አላስታወቀችም።

US-Außenminister Blinken in Island
ምስል Saul Loeb/AFP/AP/dpa/picture alliance
Äthiopien I Konfliktregion Tigray
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ