1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ሁለት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

ቅዳሜ፣ ጥር 7 2014

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ እና በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው። ዲፕሎማቶቹ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የአየር ድብደባዎችን እና ግጭቶችን በማቆም፣ የተኩስ አቁም በመደራደር ለሰላም የተፈጠረውን ዕልድ እንዲጠቀሙበት እንደሚያበረታቱ አሜሪካ አስታውቃለች

https://p.dw.com/p/45ZmD
Libanon - US David Satterfield mit Libanesischem Außenminister Bassil
ምስል picture alliance/AP Photo/B. Hussein

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ እና አዲሱ በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው። ሁለቱ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ከሰኞ ጥር 9 እስከ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚያደርጉት ጉብኝት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ሱዳን እና ሳዑዲ አረቢያ እንደሚጓዙ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።

የቀድሞውን የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን የተኩት ዴቪድ ሳተርፊልድ አዲሱን ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ወደ አዲስ አበባም ሆነ ወደ ኻርቱም ሲያቀኑ ይኸ የመጀመሪያቸው ነው። 

ሁለቱ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት በጉዟቸው መጨረሻ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ ይጠቁማል። በመግለጫው መሠረት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ እና ዴቪድ ሳተርፊልድ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በስልክ በተነጋገሩባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር በኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ባሰፈሩት አጭር መልዕክት "ሁለታችንም ትብብራችንን በጋራ መግባባት ላይ በተመሠረተ ገንቢ ውይይት ማጠናከር ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተስማምተናል" ቢሉም ዝርዝር ጉዳዮችን አላነሱም። 

ዋይት ሐውስ በአንጻሩ ሁለቱ መሪዎች በኢትዮጵያ ባለው ግጭት እና ሰላም እና እርቅ ለማስፈን በተፈጠሩ ዕድሎች ላይ መነጋገራቸውን በዕለቱ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። በመግለጫው መሠረት በድርድር የተኩስ አቁም ላይ በአፋጣኝ ስለሚደረስባቸው መንገዶች፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ጉዳይ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ ሰዎች እና የሰብዓዊ መብት ይዞታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የተወያዩባቸው ናቸው። ባይደን የአየር ድብደባዎችን ጨምሮ በመካሔድ ላይ ባለው ግጭት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እና መሰቃየታቸው እንደሚያሳስባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸውን ዋይት ሐውስ አስታውቋል። 

ሞሊ ፊ እና ዴቪድ ሳተርፊልድ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ "የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የአየር ድብደባዎችን እና ሌሎች ግጭቶችን በማቆም፣ የተኩስ አቁም በመደራደር፣ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት ለሰላም የተፈጠረውን ዕድል እንዲጠቀሙበት" እንደሚያበረታቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ዲፕሎማቶቹ  ዘላቂ የሰብዓዊ አቅርቦት መንገድ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እና ለአካታች ብሔራዊ ውይይት መሠረት እንዲጣል ግፊት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ ይጠቁማል። 

የአሜሪካ ሁለቱ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የጉዟቸው የመጀመሪያ መዳረሻ በሆነችው ሳዑዲ አረቢያ "የሱዳን ወዳጆች" በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ። ስብሰባው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሱዳንን በሲቪል አስተዳደር ወደ ሚመራ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር የጀመረውን ጥረት ለመደገፍ የታለመ ነው።

ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኻርቱም በማቅናት ሁለቱ ዲፕሎማቶች በሱዳን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሠረት ከሚወተውቱ የለውጥ አራማጆች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከጦሩ አመራሮች እና የፖለቲካ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። 

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ