1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ግጭትና ተፈናቃዮች

ረቡዕ፣ ጥር 24 2015

የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ ግጭቱ በተፈጠረበት በመጀመሪያዎቹ 3 ቀናት ከ300ሺህ በላይ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተፈናቅለው እንደነበር አስታውሰው፣ አንፃራዊ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ አንዳንዶቹ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Mydo
Infografik Karte Äthiopien Close E,  Shewa Robit, Senbete , Ataye, Kemise

በአማራ ክልል ግጭት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏል


በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን የተደረገዉ ግጭት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዋች ማፈናቀሉን  ባለስልጣናት አስታወቁ።ግጭቱ የተደረገባቸዉ አካባቢዎች የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ባለስልጣናት በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት በሰሜን ሽዋ ዞን 500 ቤቶች ጋይተዋል።በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደግሞ የ50ሺህ ሰዎች ቤት ንብረት ወድሟል።በግጭቱ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸዉን የዓይን ምስክሮችና ድርጅቶች ይናገራሉ።ተፈናቃዮቹ እርዳታ እንዳላገኙ አስታዉቀዋል።ባለስልጣናት  ግን  የእለት ድጋፍ እየሰጠን ነው ይላሉ።ለዝርዝሩ ዓለም መኮንን ከባሕርዳር 
ከጥር 13/2015 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታን ግድም፣ አንፆኪያ ገምዛ ወረዳዎች፣ እንዲሁም ሸዋ ሮቢትና አጣዬ ከተማ አስተዳደሮችና በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር በሚገኙ አርጡማ ፉርሲ፣ ጂሌ ጥሙጋ ወረዳዎችና ሰንበቴና ጨፋ ሮቢት ከተማ አስተዳደሮች በተፈጠረ የሰላም መደፍረስ በመቶዎች የሚቆተሩ ሰዎች ሲገደሉ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ንብረት ወድሟል ርካታዎችም ተፈናቅለዋል፡፡
በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ ግጭቱ በተፈጠረበት በመጀመሪያዎቹ 3 ቀናት ከ300ሺህ በላይ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተፈናቅለው እንደነበር አስታውሰው፣ አንፃራዊ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ አንዳንዶቹ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡
“አሁን መረጃውን እያጠራን ነው፣ በሰዓቱ  ወደ 303ሺህ በሶስቱ ቀናት ተፈናቅሎ ነበር፣ አሁን ሰው እየተመለሰ ነው፣ ብዙ ቤቶች የተቃጠሉ ስላሉ፣ ሰውም እንዲመለስ እያደረግን ነው፣ የቤት መቃጠል አለ፣ ዘረፋ አለ፣ የመንግስት ተቋማት መቃጠል አለ፣ ትምህርት ቤት መቃጠል አለ፣ እነሱ እነሱን እንዴት እናስጀምር? እያልን ስለሆነ ያው የተፈናቃይ ቁጥርም እየቀነሰ ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ መሐመድ ይማም በበኩላቸው በወቅቱ በነበረው ግጭት 200ሺህ ሰው ተፈናቅሎ እንደነበር አስታውሰው 100 ሺህ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ነው ያሉት፡፡ ቀሪዎቹ በተለያዩ ትምህርት ቤቶችና በየዘመድ የተጠለሉ ሲሆን 50ሺህ የሚሆኑት ቤታቸው የተቃጠለባቸው እንደሆነ አመልክተዋል፤ የምግብና የመጠለያ ችግር ቢኖርም አልባሳት እንዲደርሳቸው መደረጉንም ገልጠዋል፡፡
“ሰዎች (ተፈናቃዮች) በተለያዩ ቦታዎች ነው ያሉት፣ ሁለት የገጠር ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች፣ ላይ ነው ግጭቱ የተፈጠረው፣ …እስካሁን ድረስ ተፈናቅለው ነው ያሉት፣ በእጃችን አልባሳት ነበሩ እሱን ሰጥተናል፣ አሁን የመጠለያና የምግብ ፍላጎት ያስፈልጋል፣ እሱን ለሚመለከተው አካል መረጃ ተሰጥቷል፣ መጀመሪያ የተፈናቀለው ቁጥር ወደ 200ሺህ የሚጠጋ ነበር፣ አሁን ሌሎች ተመልሰው የቀሩት ወደ 202 ሺህ ናቸው፣ እኝህ ደግሞ መጠለያ የሚያስፈልጋቸው ቤታቸው የተቃጠለባቸው ወደ 51ሺህ ናቸው፣”
ቤታቸው በግጭቱ ከተቃጠለባቸው መካከል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰንበቴ ከተማ ነዋረ አቶ ሰኢድ አህመድ ኢማም፣ መንግስት ያደረገው ድጋፍ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
“የደረሰብን በወቅቱ የቆላ ስንዴ ዘር ለስራ ዘመቻ ወጥተን ነበረ፣ 4 ሰዓት ላይ በድሽቃ (ተተኮሰብን) ከብትም፣ ልጅም ማውጣት አልቻልንም ልጅም ከብትም አለቀብን ሳር ቤት ነበረ ቤት ያሉ ንብረቶች ሁሉ አጠቃላይ ከስሯል፣ ውድም ነው ያለው፡፡ ከመንግስት ያገኘነው ነገር የለም፣ የምንበላው ህብረተሰቡ አውጣጥቶ ሩዝም፣ እንጀራም ዱቄትም እህልም ግማሾቻችንም ከዘመድ ጋር ተዳብለን ነው ያለነው፣ ሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው ያለነው የሁለት ቀበሌ ነዋሪ (የአርቡአዩና ጃራዋካ) ከ1000 በላይ በአባወራ ብቻ ይኖርበታል፡፡ ”
ሌላው በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣየ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘመናይ ለገሰ በግጭቱ ምክንያት ቤትና ንብረታቸው መውደሙን አመልክተዋል፡፡ እርዳታም አልደረሳቸው፡፡
“ቤታችንን እንዳለ ሙሉ ለሙሉ ሱቅም ቤትም አወደሙት፣ ከመንግስት የምንጠብቀው ብዙ ነገር ነበር ምንም አላደረገልንም፣ ልጆቻችን ተበትነዋል፣ ልብስ እንኳን መቀየሪያ የላቸውም፣ ሌሊት  የሚለብሱት ሳይዙ ነው ወደ ገጠር የወጡት፣ ከዘመድ ጋር ናቸው፡፡” 
የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊው አቶ አበባው መለሰ ግን እርዳታ ለተጎዱ ሰዎች እየደረሰ መሆኑና ይህም ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡
“ከ500 በላይ ነው (ቤት) የተቃጠለው፣ አንፀኪያ ገምዛና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች፣ አጣዬና ሸዋ ሮቢት ከተሞች፣ …(እርዳታ) ወዲያውኑ ነው ማስገባት የጀመርነው … የጭነት መኪኖችን በማነጋገርና በማስገደድ ጭምር (እርዳታ) አንዲጓጓዝ  ነው ያደረግነው፣ ያጓጓዝነው በትክክል ደርሷል ወይ? የሚለውን ደግሞ ትናንትናና ዛሬ አረጋግጠናል፣ ደርሷል፣ ተሰራጭቷል፡፡”
ሰሞኑን በአካባቢዎቹ በተፈጠረው ግጭት የፀጥታ ኃሎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁለቱም ወገን መገደላቸውን የተለያዩ ብዙሐን መገናኛ ተቋማት መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ