1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል አዲስ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሾመ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24 2011

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የአንድ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የዘጠኝ ቢሮ ኃላፊዎችን ሹመቶች አጸደቀ። አቶ ላቀ አያሌው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተደርገው የተሾሙ ሲሆን በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊነትን ስልጣን ተረክበዋል።

https://p.dw.com/p/37cWf
Äthiopien Amhara Ratssitzung in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

የአማራ ክልል አዲስ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሾመ

የአማራ  ክልል ምክር ቤት በዛሬው ጉባኤው ያደጸቀው ሹመት የ10 ኃላፊዎችን ነው። ምክር ቤቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል ከቀረቡለት ተሿሚዎች መካከል የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትን ሲመሩ የቆዩት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ይገኙበታል። አቶ ንጉሱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሰይመዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ በሚገኘው አዳራሽ ከትላንት ጀምሮ ሲመክር የሰነበተው የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ነባር ቢሮዎችን እንደገና ለማዋቀር የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ላይም ተወያይቶ አጽድቋል። በውሳኔው መሰረትም የክልሉ የሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ መቋቁሙ ተነግሯል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባዔው በጫት አጠቃቀም ላይ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብም በከፊል አጽድቋል። ጫት በዋና ዋና መንገዶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲሁም በሆቴሎች እንዳይቃም በሚል በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ ደግፏል፡፡ ቢሆንም ግን የቀረቡት ስምንት የውሳኔ ሀሳቦች በሙሉ ወዲያው ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ተናግሯል። ጫት ለሚሸጡ፣ ለሚያዘዋውሩና ለሚያከፋፍሉ ወጣቶችም መንግስት ሌላ የስራ መስክ እንዲያመቻችላቸው ጠይቋል፡፡

ሂደቱን በአንዴ ማስቆም አስቸጋሪ በመሆኑ ጫት አደገኛነቱ በምክር ቤት አባላት በአቋም ተይዞ በሂደት የውሳኔ ሀሳቦች ተግባራዊ እንደሚሆን ምክር ቤቱ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የውሳኔ ሀሳቡ በአስገዳጅ አዋጅ ሊደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ጫት ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ በጉባኤው ተገልጿል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ