1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ዝግጅት

ሰኞ፣ መጋቢት 20 2013

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ መጪው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሁሉም የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች ነፃ ሆኖ እንዲካሄድ እሰራለሁ አለ። በምርጫው ለክልልና ለፌደራል ፓርላማ ከሚወዳደሩ 432 እጩዎች መካከል አብዛኛዎቹ እጩዎቹ አዲስ እንደሆኑም አመልክቷል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3rKyj
Äthiopien Bahir Dar | Wahlkampf Wohlstandspartei
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ መጪው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሁሉም የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች ነፃ ሆኖ እንዲካሄድ እሠራለሁ አለ። በምርጫው ለክልልና ለፌደራል ፓርላማ ከሚወዳደሩ 432 እጩዎች መካከል አብዛኛዎቹ እጩዎቹ አዲስ እንደሆኑም አመልክቷል፡፡ 
የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ትናንት ፖሊሲውን ለህዝብ ባስተዋወቀበት ወቅት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብራሐም አለኸኝ «ምርጫው አንድነታችንን የምናጠብቅበት ወሳኝ ምርጫ የምርጫዎች ሁሉ ቁንጮ ነው» ብለውታል፡፡ 
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባልና በአገር ደረጃ የብልፅግና ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው ፓርቲያቸው ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የትኛውንም ሀሳብ ይዞ የመጣ ፓርቲ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ብልፅግና ይሰራል ያሉት አቶ ብናልፍ፣ ህዝቡ በጥንቃቄ መርምሮና ተገንዝቦ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል የሚለውን እጩ እንዲመርጥም አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ ቤት ኃላፊው አቶ አብረሐም እንደሚሉት ደግሞ በምርጫው ሁሉም የፖለቲካ አባላትና ደጋፊዎች ከስሜታዊነትና ከስርዓት አልበኝነት መራቅ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡ 
የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የነበረንም ያልነበረንንም ቁርሾ በማንሳት ለመለያየት መቀስቀስ እንደማይገባ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው፡፡ 
አቶ አብረሐም እንደገለፁት ብልፅግና ፓርቲ በአማራ ክልል ለክልል ምክር ቤት 294 ለፌደራል ፓርላማ ደግሞ 138 እጩዎች ለምርጫው ያቀረበ ሲሆን ለፌደራል ፓርላማ ከቀረቡት መካከል 137ቱ አዲሶች ናቸው። ለክልል ምክር ቤት ከቀረቡት 294ቱ ደግሞ 95 ከመቶ የሚሆኑት አዲስ እጩዎች መሆናቸውን እንዲሁ አቶ አብረሐም ተናግረዋል፡፡ ለሁለቱም ምክር ቤቶች ከቀረቡት እጩዎች መካከል 36 , 5 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ 27 ከመቶዎቹ ደግሞ ወጣቶች እንደሆኑ አቶ አብረሐም አብራርተዋል፡፡ አርሶ አደሩም በምርጫው ተገቢና በቂ የእጩዎች ውክልና እንዳለው ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ 
ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ