1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ብሔራዊ ክልል ም/ቤት ሹም ሽር

ማክሰኞ፣ የካቲት 10 2012

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባዔ የ8 ቢሮ ኃላፊዎችን ሹመት አጸደቀ፤ ወደ ፌደራል መንግሥት በተዛወሩ የክልሉ አመራሮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ተቃውሞ ቀርቧል። ዛሬ የተጠራው የአማራ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባዔ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሹሟል።

https://p.dw.com/p/3Xw2N
Äthiopien Landesregionalrat in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

በአስቸኳይ ጉባዔው የ8 ቢሮ ኃላፊዎችን ሹመት ጸድቋል

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ባቀረቧቸው ዶ/ር ፋንታ ማንደፈሮ ሹመት ላይ ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት አድርጓል። አንዳንድ የምክር ቤት አባላት እንዳሉት ግለሰቡ እውቀትና ልምድ ቢኖራቸውም አሁን ክልሉ ያለበትን ችግር ለመፍታት ለአዲስ አመራር ፈተና ይሆናል ብለዋል። ሌሎቹ ደግሞ ሹመቱ አስፈላጊ ቢሆን እንኳ የክልሉን ችግር ከስር መሰረቱ የሚያውቁ አመራሮችን ወደፌደራል ከመላክ ይልቅ አዲሶቹን በፌደራል መንግስቱ እንዲመደቡ ማድረግ ተገቢ ይሆን እንደነበር ተከራክረዋል።

በመጨረሻም የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ሹመት በ3 ተቃዎሞ፣ በ48 ተዐቅቦና በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል። 
ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ አንዲት ሴት ሹመታቸው ጸድቋል። ዶ/ር ሙሉነሽ አለበቸው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው ተሸመዋል።

ዶ/ር የሺመቤት ደምሴ፣ የአማራ ክልል ኦዲተር ጀነራል፣ ዶ/ር ሰኢድ ኑሩ በምክትል ርእስ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት፣ ቤቶች ኮንስትራክሽን ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ሲሳይ ዳምጤ፣ የአማራ ክልል ሠላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ፣ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ አብዬ ካሳሁን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዚደንት፣ አቶ ኃለየሱስ ተስፋማሪያም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕረዚደንት በመሆን ቃለ ማሐላ ፈፅመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ 4 ክፍተኛ የክልሉ አመራሮች ወደ ፌደራል መንግስቱ መዛወራቸውን በርከት ያሉ የምክር ቤት አባላት ተቃውመውታል። አንዳንዶቹ እንዲያውም ክልሉን ለማዳከም የተደረገ ሴራ ነው በማለት በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በቁርጠኝነት የክልሉን ሰላምና ያለውን የከረረ የብሔር ጥላቻን የሚጋፈጡ አመራሮችን ማዛወር ተገቢ አይደለም ያሉት ደግሞ ሌላዋ የምክር ቤት አባል ናቸው። የአመራሮቹን ወደ ፌደራል መዛወር የደገፉም የምክር ቤት አባላት አስተያየት ሰጥተዋል።

የክልሉ ሠላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው መሾማቸውን የአማራ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ለዶይቼ ቬለ ገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው አመራሮቹ ራሳቸው ወደ ፌደራል የመዛወር ጥየቄ እንደነበራቸው ግን ደግሞ እርሳቸውም በክልሉ እንዲሰሩ ጥረት አድርገው እንደነበርም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። ወደ ፌደራል መንግስቱ የተዛወሩት አመራር በዛሬው ስብሰባ ላይ አልተገኙም። 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ