የኖቤል ሽልማት፤ የአፍሪቃ የሰላም መልእክተኞች
ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ከአፍሪቃውያን የዓለም የሰለም ኖቤል ተሸላሚዎች ወጣቱ ናቸው። በቁጥር ደግሞ ዐሥረኛው። ለሰላም ባደረጉት ጥረት ነው የተሸለሙት። የመጀመሪያው የዓለም የሰለም ኖቤል ሽልማት አፍሪቃ የገባዉ በ1960 (ዘመኑ በሙሉ እ.ጎ.አ.ነው) ነበር።
ከአቦሸማኔ ቆባቸው ጋር ወደ ሽልማቱ
አልበርት ሊቱሉ በደቡብ አፍሪቃ የነበረውን የዘር መድልዎ ሥርዓት በመቃወም ላደረጉት ሰላማዊ ትግል በ1960 የዓለም የሰለም ኖቤል ሽልማት ሲሰጣቸው የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ነበሩ። አልበርት ሊቱሉ እንደ (ANC) ፕሬዚደንትነታቸው ተሸላሚ በነበሩበት ወቅት የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ መንግሥት የነጻነት ንቅናቄውን አግዶ ስለነበር ከአገር እንዳይወጡ ተከልክለዋል። ሽልማታቸውን መቀበል የቻሉት ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር፤ የጉዞ እገዳው ለዐሥር ቀን ሲነሳላቸውም አልበርት ሉቱሊ ወደ ዖስሎ ማቅናት ችለዋል።
መንፈሳውያኑ በጋራ ኾነው
አቡነ ዴዝሞንድ ቱቱ የደቡብ አፍሪቃ የስነ-ምግባር ተምሳሌት ተደርገው ይቆጠራሉ፤ በሰብአዊ መብቶች አቀንቃኝነታቸው እና ጸረ መድልዎ ታጋይነታቸው ይታወቃሉ። «የቀስተደመና ሀገር ነን» የሚለው አባባል ምንጩ ዴዝሞንድ ቱቱ ናቸው። በ1984ም የፕሮቴስታንት መንፈሳዊው አቡን ዖስሎ ውስጥ ተሸልመዋል። ለዛ የተሞሉት የዓለም የኖቤል የሰላም ተሸላሚው የማንዴላ ኹነኛ ወዳጅ ብቻ ሳይኾኑ በዓለም ዙሪያም እንደ ዳላይ ላማ ያሉ ወዳጆች አሏቸው።
አማንዳ! በስተመጨረሻ ከእስር ነጻ!
ይኽ ፎቶ በዓለም ዙሪያ ተዳርሷል። የጸረ አፓርታይድ ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በ1990 ዓ.ም ከ27 ዓመታት እስር ቆይታ በኋላ ከወህኒ የተለቀቁ ጊዜ፤ ደቡብ አፍሪቃ ትንፋሿ ቀጥ ያለበት ታሪካዊ ዕለት። በአልበገሬነት የዘለቁበት ትግል ደቡብ አፍሪቃ በ1994 ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና እንድትገባ መንገዱን ጠርጓል። ከዚያ አንድ ዓመት በፊት ኔልሰን ማንዴላ ርእሰ-ብሔር ከነበሩት ፍሬድሪክ ቪሌም ደ ክላርክ ጋር የዓለም የኖቤል ተሸላሚ ኾነዋል።
ኹለት ባላንጦች በሰላም ተጣመሩ
ቆራጥነት፤ ትእግስት እና ጽናት ወደ ግባቸው መርቷቸዋል። የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ እና የደቡብ አፍሪቃ የቀድሞው ርእሰ-ብሔር ፍሬድሪክ ቪሌም ደ ክላርክ በ1993 በጋራ ለዓለም የሰላም የኖቤል ተሸላሚነት ክብር በቅተዋል። ያም ኔልሰን ማንዴላ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት ከመኾናቸው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነው። ሰላማዊ አብዮቱ ስኬቱን መትቶ ነበር፤ ኾኖም የሰላም ሒደቱ በዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃ ገና ሥር አልሰደደም ነበር።
በሰላም ተልእኮ በዓለም ዙሪያ
ኮፊ አናን የሰላም አምባሳደር የሚለው መለያቸው ነው። ጋናዊው ዲፕሎማት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ «በተሻለ ለተቀናጀች እና ሰላማዊ ለኾነች ዓለም ተግባራቸው» ከድርጅታቸው ጋር ለዓለም የኖቤል ሽልማት በቅተዋል። ገጽታቸውን መገንባት ቢችሉም ጥቁር ጠባሳ ግን አርፎባቸዋል። በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ የተባበሩት መንግሥታት እንዳላየ ችላ ብሏል በሚል በብርቱ ይወቀሳሉ። ኮፊ አናን ቆይቶም ቢኾን ስህተቱን አምነው ተቀብለዋል።
ማማ ሚቲ፦ የዛፎች እናት
በ2004 ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ወይዘሮ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸልመዋል። እኚህ ሴት ዋንጋሪ ማታይ ናቸው። ኬኒያዊቷ ፕሮፌሰር ለሴቶች መብት እና በሀገራቸው ድህነትን ተፋልመዋል። የአካባቢ ጥበቃ ምክትል ሚንሥትሯ «ለአረንጓዴ ቀበቶ ንቅናቄያቸው» ይበልጥ በሚታወቁበት «የዛፎች እናት» ስያሜ ተሸልመዋል። ሽልማታቸውንም በራሳቸው መንገድ ነው ያከበሩት። «አንድ ችግኝ እተክላለሁ» በሚል ርእስ ግለ-ታሪካቸውን ጽፈዋል።
ሴቶች ተሸላሚዎች፦ ለሦስት ሴቶች ዕውቅና
በ2011 ሦስት ሴቶች በጋራ ተሸልመዋል። የላይቤሪያዋ ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሲርሌፍ (በስተቀኝ) እና የሀገራቸው ልጅ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቿ ሌይማኅ ግቦዊ (ከመሐል) እናም ጋዜጠኛ ታዋኩል ካርማን ከየመን። የምዕራብ አፍሪቃዋ ላይቤሪያ ኹለቱም ሴቶች ሀገራቸውን ከእርስ በእርስ ጦርነት በመታደጋቸው ነው ለሽልማት የበቁት።
ሰዎች ትንግርተኛው ሐኪም ሲሉ ይጠሯቸዋል
ኮንጎዋዊው ሐኪም እና የሰብአዊ መብቶች ተሟቹ ዴኒስ ሙክዌጌ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የኾኑ ሴቶችን በመርዳት ላበረከቱት የሕይወት ዘመን አገልግሎት ተሸልመዋል። ቡካቩ ውስጥ በ1999 ራሳቸው ባቋቋሙት ፓንዚ ሐኪም ቤት ውስጥ የማኅጸን ክፍል ዋና ቀዶ ጠጋኝ ኾነው ለረዥም ዘመን አገልግለዋል። ለመምተኞቻቸው ተስፋ በማሰነቅ እና ቆራጥ እንዲኾኑ በማበረታት ብዙ ለፍተዋል። ለዚያም አገልግሎታቸው በ2008 ከኩርድኛ ተናጋሪ ይዚዳዊቷ ናዲያ ሙራድ ጋር በጋራ ተሸልመዋል።
ወጣቱ አብዮተኛ ከፊት
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ቢደሰቱ ምክንያት አላቸው። ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽዖ ዘንድሮ ተሸላሚ ኾነዋል። ምንም እንኳን መንገዱ ገና አባጣ ጎርባጣ ቢኾንም ቅሉ፤ በገዛ ሀገራቸው እርቀ-ሰላም እንዲወርድ መንገድ እየጠረጉ በመኾናቸው አድናቆት ተችሯቸዋል። ባልተረጋጋችው የበርካታ ብሔሮች ሀገር ኢትዮጵያ ያስጀመሩት ቆራጥ የለውጥ ሒደት አድናቆት አስገንቶላቸዋል። ዐቢይ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን ዖስሎ ውስጥ በተደረገ የሽልማት ስነስርዓት ወስደዋል።