1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖቤል ሽልማት የCNN የ2019 ጀግና

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3 2012

ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚያስጠሩ ጉልህ ክንውኖች የታዩበት ነው። የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማትና ከሽልማቱ መልስ የተደረገላቸው አቀባበል፤ እንዲሁም የጎርጎሪዮሳዊው 2019 የCNN ጀግና ወ/ሮ ፍሬወይኒ መብርሃቱ ስኬት የብዙዎች ትኩረት ስቧል። 

https://p.dw.com/p/3UmIV
Norwegen l Verleihung des Friedensnobelpreis an Abiy Ahmed in Oslo
ምስል picture alliance/AP Photo/NTB scanpix/H. M. Larsen

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኖርዌዩ የኖቤል ኮሚቴ ማክሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ,ም ለመቶኛው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሽልማቱን ሲያበረክት በርካታ ኢትዮጵያውያን ኦስሎ ከተማ በመገኘት የደስታቸው ተካፋይ መሆናቸውን አሳይተዋል። ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛነቷን ጠቅሰው በዚህ ስሌት ደግሞ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን በማለት አዳራሹን በጭብጨባ ያናጋ ደስታ የጫሩት የኖቤል ኮሚቴው ሊቀመንበር ቤሪት ራይስ አንደርሰን ወደመድረኩ የጋበዟቸው የዓለም ሎሬት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው የብዙዎችን ልብ ያሞቀ ንግግር አድርገዋል። ይህን ዜና ከተከታተሉ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች መካከል፤ ሰንትዩ ደሬሳ ሴባ በፌስቡክ፤ «ለሀገራችን ትልቅ ኩራት ነው የጠቅላያችን የኖቤል ሽልማት» ሲሉ፣ ቴዲ ጌታቸው ደግሞ፤ «በእርስዎ ትልቅ እምነት ያኖርነዉ በምክንያት ነው። ደግሞም አምንቦታለሁ አንድ ቀን ሁሉም ብሔር ተዋዶ እና ተከባብሮ በእኩልነት የሚኖርበትን ኢትዮጵያ እና  ብዙዎች የሚመኟትን ሀገር እንደሚገነቧት ተስፋ አለኝ።» ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በኦስሎ እና አዲስ አበባም ሲመለሱ ሕዝቡ ያሳያቸውን አክብሮት እና ፍቅር መሠረት ያደረገ ሃሳባቸውን በትዊተር እና በፌስቡክ አማርኛን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲህ አካፍለዋል፤ «ፍቅር እና ክብር የገባውን ሕዝብ ማገልገል ኩራትም ዕድልም ነው፤ አመሰግናለሁ! ገለቶሚ! ታንኪዪው ! » ነው ያሉት።  ጌቾ ካዎ ጌቾ ታዲያ፤ «እንወድሀለን በርታ! አንተን በመቃወም ከሚጮህ ወረኛ ይልቅ በቤቱ ተቀምጦ አንተን የሚደገፍ እና ስለ አንተ የሚጸልይ ይበልጣል። » ሲሏቸው፤ ሙሉነህ ሱጌቦ ደግሞ፤ «እንኳን ደህና ተመለሱ። አቀባበሉ ቢያንስ እንጂ የሚበዛብዎት አይደለም። ለማንኛውም ይህን ስኬት እያጣጣምን በእግዚአብሔር ፈቃድ ለበለጠ ስኬት ከጎንዎ ነን። ከሠራነው ይልቅ ያልሠራነው ይበልጣልና ቀበቶ ጠበቅ።» ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት ስር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ዘ ኮረም ክብረት የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «እኛም ደስ ብሎናል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ስሟን ከፍ ስላደረጉልን ከልብ እናመሰግናለን! በዚህ ሳምንት በዚህ ስንገረም የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ መመዝገቡ ደግሞ በነበረን ደስታ ላይ ሌላ ደስታ ጨምሮልናል፡፡ መጭው ጊዜ የኢትዮጵያ ሀገራችን ትንሳኤ ነው፡፡» ብለዋል። ኤሴቅ ድሬ በበኩላቸው፤ « የእግዚብሔር ሚዛን የዳኛ ሚዛን የመሪ ሚዛን፤ ለህዝቡ በሙሉ እኩል መሆን አለበትና፤ እይታህ ለሁሉም እኩል ከሆነ ሁላችንም፤ ከጎንህ ነን መሪ ለህዝቡ አባት ነው። »  የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል።  የሲሳይ ዘገየ አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል፤ «የሰላሙን ነገርማ ራስህ ታውቀዋለህ ብቻ እንኳን ደስ አለህ ስንቱ ወላጅ በሃዘን ቤት ተቀምጦ የሰላም ተሸላሚ መሆናችን አልዋጠኝ ብሏል።»

Symbolbild Twitter Konto
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gombert

ሌላው በዚሁ ሳምንት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠራው ወ/ሮ ፍሬወይኒ መብርሃቱ በዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን በCNN የዓመቱ ጀግና ሆና መመረጧ ነው። ወ/ሮ ፍሬወይኒ ለሴቶች የወር አበባ መቀበያ ተገቢው የንፅሕና መጠበቂያ በማይገኝባት ኢትዮጵያ ዳግም አገልግሎት መስጠት የሚችል የወር አበባ መቀበያ አዘጋጅተው ለተማሪዎች እንዲዳረስ ማስቻላቸው አድናቆትን አትርፎላቸዋል። ለወገኖቻቸው ያበረከተቱት ታላቅ አስተዋፅኦ ለክብር ያበቃቸው ወ/ሮ ፍሬወይኒን መሸለም የሰሙ ወገኖች አድናቆት ምሥጋናቸውን ያለስስት ነው የሰጧቸው። ከእነዚህ መካከልም ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሃ በትዊተር፤ «ፍሬወይኒ መብርሃቱ የየCNN የ2019 ጀግና በመባልሽ እንኳን ደስ ያለሽ! ኢትዮጵያ እና አፍሪቃ ባንቺ ኮርተዋል።» ሲሉ፤ የኢትዮጵያ የመንገዶች እና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ በበኩላው፤ «ዳግም ማገልገል የሚችል የወር አበባ መቀበያ በማዘጋጀት ወጣት ሴቶች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ለማድረግ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አግላይ ባህል እንዲገታ ጊዜሽን የሰጠሽው ፍሬወይኒ መብርሃቱ እንኳን ደስ ያለሽ። በዚህ ሥራዋ የ2019 የCNN የዓመቱ ጀግና ተባለች። ኮርቻለሁ!» ብለዋል።  አዲስ ዓለም ደስታ በበኩላቸው፤ «የ2019 የCNNን የዓመቱ ጀግና ሆነሽ በማሸነፍሽ ፍሬወይኒ መብርሃቱ እንኳን ደስ ያለሽ። ይህ አንቺንም ሆነ እያንዳንዳችንን በሌሎች ሕይወት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ለማዋጣት እንድንችል የሚያነቃቃን ይሁን።» የሚል አድናቆታቸውን በትዊተር አጋርተዋል። የሱነህ ወልዴ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «በእውነት አገርሽን  መውደድሽን  በተግባር  ያሳየሽ ምርጥ ጀግና የኢትዮጵያ ልጅ ነሽ። የዘመኑ አገርና  ሕዝብን እወዳለሁ  ለብሔሬ ቆሜያለሁ ከሚል እና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያባሉ ፖለቲከኛች ለሕዝብ መቆም ምን እንደሆነ ካንቺ መማር ይገባቸዋል።» ነው ያሉት። ኮነ ፍሰሀ በቃሉም እንዲሁ፤ «ሰው የራሱንና ለሰው ክብር ሲሰጥ በሥራውም ይከበራል እንዲህ ወቀሳና ከሰሳ ይጥፋ ከሀገራችን ይውደም የፖለቲካ ቁማራችን።» ብለዋል። ደስታ አስገደሞ አስፋው ተስፋዬም፤ «በተግባር ሰርቶ ማሳየት እንደዚህ ነው  ኢትዮጵያውያን፤  ወሬና ውሸት አይጠቅምም ። ሁላችንም ወደ ሥራ ገብተን አገርና ህዝብ የሚጠቅም  ነገር ሠርተን እንለፍ።  ከጀግና ፍረወይኒ መብራህቱ እንማር በተለይ ባለስልጣኖች ።» ሲሉ አስተያየታቸውን በፌስቡክ አስነብበዋል። ዓለሙ በበኩላቸው በትዊተር ባካፈሉት መልእክት የጎርጎሪዮሳዊው ዓመት 2019 የኢትዮጵያውያን ስኬት የተመዘገበበት እንደነበር ለእንደሚከተለው ለማሳየት ሞክረዋል፤ ኢትዮጵያውያን በ2019 ዓ,ም አሉ ታደሰ ዓለሙ፤ ዶክተር ዐቢይ አህመድ የ2019 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ፣ ፍሬወይኒ መብራሃቱ የ2019 የCNN ጀግና፤ ተወልደ ገብረ ማርያም የ2019 የዓመቱ የአየር መንገዶች ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም የ2019 የሀርቫርድ የፊዚያቲክ ኤፒዲሞሎጂ እና ባዮስታትስቲክስ ሽልማት አሸናፊ፤ ዶክተር ግርማ አረጋዊ በሰሜን ካሮላይና የ2019 የዓመቱ የህክምና ባለሙያ፤ ዶክተር ሐረገወይን አሰፋ በአሜሪካ የኬሚስትሪ ማኅበረሰብ የ2019 የኬሚስትሪ ጀግና፤ ማርታ ገበየሁ የ6ኛው የዓለም ውኃ ሽልማት የ2019 አሸናፊ፤ ሶስና ወጋየሁ በአውስትራሊያ አጠቃላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የ2019 የዓለም አቀፍ ፌር ፕሌይ ተሸላሚ» ለእሳቸው የስኬት ዝርዝር አስተያየት የሰጡት ሰለሞን ንጉሥ በበኩላቸው፤ «ብዙው አንቀላፍቷል ጥቂቶች እየገሰገሱ ነው። ዓለምም የምትለወጠው በብዙኃኑ አይደለም።» ብለዋል።

Symbolbild Facebook
ምስል Getty Images/AFP/L. Bonaventure
ፍሬወይኒ መብርሃቱ የ2019 የCNN ጀግና
ምስል Getty Images/M. Loccisano

ሌላው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ሲያነጋግር የሰነበረው ጉዳይ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፌደራል ፖሊስ ይሰማራል መባሉ ነው። የኢትዮጵያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ ግጭቶችን ለመከላከልና የተማሪዎችን ስጋት ለመቀነስ ዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑን ለዶቼ ቬለ DW ተናግረዋል። ውሳኔውም ጥበቃን በማጠናከር ዩንቨርስቲዎቹን ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ለመመለስ የሚያግዝ መሆኑንም ኃላፊዉ አብራርተዋል። ይህን በተመለከተ ማሙሽ አከለው በፌስቡክ፤ «ይሻላል ያለነው ከፈጣሪ በታች በመከላከያ እና በፊደራል ሃይል ነው፤  የአዲስ አበባ እና የክልል ፓሊስና ልዩ ሃይል ጉዳይ አሳሳቢ ነው» ሲሉ ወንደወንሰን ኃይሉ ደግሞ፣ «ምንም አዲስ ነገር የለውም።  በዘመነ ኢህአዴግ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ በበዛበት ወቅት የአጋዚ ክፍለ ጦር ወታደሮች የዪኒቨርሲቲውን ካኪ ዩኒፎርም እየለበሱ ተማሪው አመፅ እንዳያነሳ ይጠብቁ ነበር። ልዩነቱ እነዚህ የግቢው ጥበቃ አጋዥ ሲሆኑ የበፊቱ ግን ጠቅልሎ ከግቢው በማስወጣት ወደ አዲስ አበባ ፓሊስ በማዛወር ሰልጥነው እንዲቀጠሩ ተደርጓል። በጥባጭን ለመከላከል ሠላምን ለመፍጠር የሚደረግ በመሆኑ ክፋት የለውም።» ብለዋል። የዳንኤል አበበ አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል፤ «ሀገራዊ ምርጫ እስኪያልፍና ሀገሪቱ እስኪረጋጋ በዩንቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች በሙሉ ትምህርት አቁመው ወደ ቤታቸው ቢመለሱ የተሻለ ነው።  ቢመረቁ ባይመረቁም ሥራ አጥ ተብሎ መቀመጣቸው ለማይቀር ሰላም አይጡ፤ እኛንም ሰላም አያሳጡን !!!» አበራ ወልዳይ በበኩላቸው፤ « በጣም ፍትሓዊ አይደለም።መሆንም ካለበት ችግር ያለባቸው ክልሎች ብቻ እንጂ ሁሉም ክልልሎች ላይ በጅምላ ጦር መመደቡ እንደ ትግራይና አፋር የመሳሰሉ የክልሉ ህዝብ፣ መንግስትና የክልሉ የፀጥታ ኣካላት ጥረት እውቅና የሚነፍግ ነው።» ሲሉ፤ ዊዝ ክብረአብ ደግሞ፣  እስካሁን ለምን በፌደራል እንዲጠበቁ አልተደረገም ነበር?  ምትፈልጉትን ካበጣበጣቹ እና ካፈናቀላቹ በኋላ ነው መፍትሄ ሚታያቹ? ለማንኛውም ግሩም ሃሳብ ነው፤ ዳይ ወደ ተግባር።» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ