1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖርድ ራይን ቤስትፋለን ፌደራዊ ግዛት ምርጫ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 9 2014

በኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚካሄደው ምርጫ ሁሌም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ምርጫ ነው። በዚህ የተነሳም ምርጫው «ትንሹ የፌደራል ጀርመን ምርጫ» ተብሎ ይጠራል።የዚህም አንዱ ምክንያቱ ምዕራብ ጀርመን የሚገኘው የኖርድራይን ቬስትፋለን ግዛት የበርካታ ህዝብ መኖሪያ መሆኑ ነው ።የግዛቲቱ ነዋሪ 18 ሚሊዮን ይጠጋል። ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውም የጎላ ነው።

https://p.dw.com/p/4BR8O
Landtagswahl in Nordrhein-Westfalen - CDU-Wahlparty - Hendrik Wüst
ምስል Rolf Vennenbernd/dpa/picture alliance

የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ግዛት ምርጫ


ራድዮ ጣቢያችን በሚገኝበት በምዕራብ ጀርመኑ የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ባለፈው እሁድ በተካሄደ ምርጫ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በጀርመንና ምህጻሩ ሴ ዴ ኡ ቀንቶታል።ፓርቲው በአብላጫ ድምጽ አሸንፎ የበላይነቱን ይዟል። በዚህ ምርጫ ከሁለት ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ ጀርመንን የሚመራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህጻሩ ኤስ ፔዴ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ እጅግ አነስተኛ የተባለ ውጤት ማምጣቱ እያነጋገረ ነው።የፌደራል ጀርመን አጠቃላይ ምርጫ በተከናወነ፣ በስምንት ወሩ የተካሄደው የእሁዱ የኖርድራይን ቬስትፋለን ምርጫ «የጎርጎሮሳዊው 2022 የጀርመን ትልቁ ምርጫ» ነው የሚባለው።በዚህ ምርጫም  የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ሴዴ.ኡ 35.7 በመቶ ድምጽ አሸንፏል። ሴዴኡ ከጎርጎሮሳውያኑ 2005 ዓም አንስቶ እስከ 2021 ዓም ድረስ በብቸኛዋ ሴት የቀድሞዋ የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ነበር የሚመራው። የእሁዱ ውጤት ፓርቲው ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደ ምርጫ ካገኘው ድምጽ በ2 በመቶ ከፍ ያለ ነው። የሴዴኡው ፖለቲከኛ የግዛቲቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቩስት ፓርቲያቸው ምርጫውን እንዳሸነፈ ይፋ ሲሆን ባሰሙት ንግግር ፓርያቸውን ጠንካራ ያደረገው ህዝቡ የሰጠው ድምጽ መሆኑን ገልጸዋል።
«የኖርድራይን ቬስትፋለን መራጮች በግልጽ ወስነዋል ፣እኛን ሴዴኡ በኖርድራይን ቬስትፋለን አሸንፈናል። ህዝብ የሰጠን ድምጽ በክልሉ ጠንካራ ፓርቲ አድርጎናል። ከዚህ በኋላ መጪውን መንግሥት የመመስረትና የመምራቱ ስራ የኛ ነው። »
ቩስተ ይህን ቢሉም የግዛቲቱን መንግሥት ዳግም መምራታቸውን ከወዲሁ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አልተቻለም።  ግዛቲቱን ማን ይመራል የሚለው  ወደፊት በሚካሄዱ ድርድሮች ነው የሚወሰነው።  
በእሁዱ ምርጫ ኤስ.ፔ.ዴ 26 በመቶ ድምጽ ነው ያገኘው። ውጤቱም ከጎርጎሮሳዊው 2017 ዓመተ ምህረት በፊት የኤስፔዴ ጠንካራ ይዞታ በነበረው በኖርድራይን ቬስትፋለን ፓርቲው በግዛቱ የ76 ዓመት ምርጫ ታሪክ ያገኘው እጅግ አስከፊው ውጤት ተብሏል።የፓርቲው እጩ ቶማስ ኩቻቲ ውጤቱ የተጠበቀ እንዳልነበር ጠቅሰው  ሽንፈቱን በጸጋ ተቀብለዋል። ሆኖም አንደኛ ያሉት ግባቸው ግን መሳካቱን ተናግረዋል።
«ውጤታችን ከጠበቅነው በታች ነው። ጠንካራ ፓርቲ መሆን እንፈልጋለን። ግን አልተሳካልንም። በጥቂት በመቶዎች ከ ሴ ዴ ኡ ያነሰ ውጤት አምጥተናል። ዛሬ አንድ ነገር እርግጠኛ ሆኗል። የወግ አጥባቂዎቹንና የለዘብተኛዎቹን ጥምረት ለማሰናከል ችለናል። ይህ የመጀመሪያው ግባችን ነው።በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ይህ መንግሥት አብላጫ ድምጽ አይኖረውም።»
በርካታ የጀርመን መገናኛ ብዙሀን ባለፈው ጥቅምት ስልጣን የያዙትና አሁንም በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኙት ሄንድሪክ ቩስት ግዛቲቱን ይመራሉ ብለው ነው የሚጠብቁት።ይሁንና ኩቻቲ እንዳጠቆሙት በግዛቲቱ የቀድሞ የሴ ዴ ኡ ተጣማሪ ለዘብተኛው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ያገኘው ድምጽ አነስተኛ በመሆኑ ሁለቱ ፓርቲዎች ተጣምረው መንግሥት ሊመሰርቱ አይችሉም ።
ከኤስ ፔ ዴ ፓርቲው አመራሮች አንዱ ላርስ ክሊንግል በሰጡት አስተያየትም የፓርቲውን ሽንፈት አምነው ፓርቲያቸው በግዛቲቱ ሃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። 
«በመጀመሪያ ደረጃ በግልጽ በምርጫው ተሸንፈናል። ሴዴኡ ኖርድ ራይን ቬስትፋላይን ተቆጣጥሯል። አሁን ግዛቲቱን የሚመሩት የሴ.ዴ.ኡው ፖለቲከኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ሹስት ቀጣይ ተግባር አዲስ መንግሥት ለመመስረት መደራደር ነው። አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣው ትናንት ማታም ብለነዋል፤ ኢስፔዴ በኖርድራይን ቬስትፋልን ሃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ነው። » 
ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚሟገተው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ በአሁኑ ምርጫ ከሁለ የተሻለ የሚባል  ድምጽ አግኝቷል፤ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲው 18.2 በመቶ ያገኘው ድምጽ ሲሆን ይህም ከዛሬ አምስት ዓመቱ ምርጫ በሶስት በእጥፍ የጨመረ ነው።ውጤቱም በግዛቲቱ  ለሚመሰረተው ጥምር መንግሥት  ለፓርቲው የአንጋሽ ፓርቲ ቦታ አስገኝቶለታል። «አማራጭ ለጀርመን» በምህጻሩ አ.ኤፍ.ዴ የተባለው ጽንፈኛ ፓርቲ ደግሞ በምርጫው ከፍተኛ ኪሳራ ነው ያስመዘገበው ።የዛሬ አምስት ዓመት አግኝቶ ከነበረው 7.4 በመቶ አሽቆልቁሎ 5.4 በመቶ ድምጽ ብቻ ነው ያገኘው።ግራዎቹ ደግሞ ከአ ኤፍ ዴም በባሰ በዛሬ አምስት ዓመቱ ምርጫ ካገኑት 4.9 በመቶ ድምጽ ከግማሽ በላይ ቀንሰው ወደ 2.1 በመቶ ዝቅ ብለዋል። በርካታ የጀርመን መገናኛ ብዙሀን ባለፈው ጥቅምት ስልጣን የያዙት ሄንድሪክ ቩስት ግዛቲቱን ይመራሉ ብለው ነው የሚጠብቁት።
በኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚካሄደው ምርጫ ሁሌም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ምርጫ ነው። በዚህ የተነሳም ምርጫው «ትንሹ የፌደራል ጀርመን ምርጫ» ተብሎ ይጠራል። የዚህም ምክንያቱ ምዕራብ ጀርመን የሚገኘው የኖርድራይን ቬስትፋለን ግዛት የበርካታ ህዝብ መኖሪያ መሆኑ ነው ።የግዛቲቱ ነዋሪ  18 ሚሊዮን ይጠጋል። ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም የጎላ ነው።ለዚህም አንዱ ማሳያ የጀርመን የድንጋይ ከሰል መቀነት ሩርገቢት የሚባለው ስፍራ መገኘቱ ነው። ከሌሎች የጀርመን ግዛቶች በተለየ ልዩ ልዩ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ መሆኑም በግዛቱ የሚካሄድ ምርጫ ከሚገዝፍባቸው ምክንያቶች ውስጥ ነው። ክላውስ ሹበርት የተባሉ በሙንስተር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የኖርድራይን ቬስትፋለን ምርጫ ለምን እንደሚገን ሲያስረዱ ከምክንያቶቹ አንዱ የግዛቲቱ ትልቅነት መሆኑን ገልጸዋል። እርሳቸው እንዳሉት የግዛቲቱ ስፋት ከጀርመን ጎረቤት ከኔዘርላንድስ ጋር ይስተካከላል። ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢዋም እንዲሁ ከኔዘርላንድስ ጋር ይቀራረባል። እናም ይላሉ ሹበርት በኖርድራይን ቬስትፋለን የሚሆነው ሁሉ መላ ጀርመንን የሚወክል ነው።በህዝብ ብዛት ከሌሎች የጀርመን ግዛቶች ትልቁን ስፍራ የሚይዘው ኖርድ ራይን ቬስትፋለን፣በርካታ አነስተና ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚገኙበትም ግዛት ነው። አብዛኛዎቹ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ በነዳጅ ዘይትና በምግብ ዋጋ ንረት እየተፈተኑ ነው።
ካ2017 ዓም ምርጫ በኋላ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ግዛቲቱን ከነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጋር ሲመራ ቆይቷል።ሶሻል ዴሞክራቱ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልትስ የሚመሩት መንግሥት ሶስት ፓርቲዎች ማለትም ኤስፔዴ  አረንጓዴዎቹ  የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ተጣማሪ መንግሥት ነው። በዚህ ዓመት የተመሰረተው የሾልትስ መንግሥት በሩስያ የዩክሬን ወረራ፣በዋጋ ግሽበት፣ ጀርመን የሩስያ ጋዝ አቅርቦት ጥገና መሆን ያስከተለው ቀውስ በመራጩ ላይ ተጽእኖ ሳያሳድር እንዳልቀረ ተገምቷል።ምንም እንኳን ኤስ ፔ ዴ ከቀድሞዎቹ ምርጫዎች ዝቅተኛ የተባለው ውጤት ቢያስመዘግብም ደጋፊዎቹ ግን አሁንምተስፋ አልቆረጡም።ከመካከላቸው አንዷ አዲስ ሴሊሚ የተባለች ደጋፊ ለፓርቲው በጎ አመለካከት እንዳላት ትናገራለች። ይሁንና ከአሸናፊው ሴዴ ኡ ጋር ሲነጻጸር ልዩነት ችሩ አለመሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም።
«በሁለተኛ ደረጃ ላይ መገኘታችን አዎንታዊ ነው።እንደሚመስለኝ ከኤስ ፔ ዴ እጩ ቶማስ ኩቻቲ ጋር ጥሩ የሚባል የምርጫ ዘመቻ አካሂደናል።አዎ እርግጥ ነው አንደኛ ከወጣው ፓርቲ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ ግን ጥሩ አይደለም።» 
አሁን በዚህ ምርጫ ውጤት መሠረት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ አንጋሽ ተብሏል። ፓርቲው ጀርመን ተጣምረው ከሚመሩት ሶስት ፓርቲዎች አንዱ ነው። እንደ አሁኑ የፌደራል መንግሥት ዓይነት ማለትም ከኤስ ፔዴና ከነጻ ዴሞክራቶቹ ጋር መጣመር ወይስ ከሴዴኡ ጋር መንግሥት መመስረት ነው ምርጫው የሚለው አሁን ግልጽ አልሆነም። በዚህ የተነሳም የመንግሥት ምስረታው ድርድር ቀላል እንደማይሆን ተገምቷል። ይሁንና ሴዴኡና አረንጓዴዎቹ ጥምር መንግት ሊመሰርቱ የመቻላቸው እድል የሰፋ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ሁለቱ ፓርቲዎች በአየር ንብረት ጥበቃ ጉዳይ ላይ የጋራ መሰረት አላቸው። ሆኖም በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ግን ልዩነቶች አሏቸው።ከሁሉ ትልቁ የሀገር ውስጥ ፀጥታ ጉዳይ ነው። በኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚመሰረተው ጥምር መንግሥት ኤስፔዴን ለዘብተኛውን ነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ ወይም ደግሞ የአረንጓዴዎቹና የምርጫ አሸናፊ የሴዴኡ ይሁን የሚለየው በመጪዎቹ ሳምንት ከሚካሄደው ድርድር  በኋላ ይሆናል። 

Köln | Landtagswahl in Nordrhein-Westfalen
ምስል Marius Becker/dpa/picture alliance
Landtagswahl in Nordrhein-Westfalen - Stimmabgabe Wüst
ምስል Sascha Schuermann/Getty Images
Deutschland Wahlplakate - Landtagswahl 2022 NRW
ምስል Revierfoto/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ