1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንቦች ለአደጋ መጋለጥ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2011

በታታሪነቷ የምትታወቀው አነስተኛ ፍጥረት ንብ ህልውናዋ አደጋ ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው። ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ቁጥሯ የተመናመነው ማር አምራቿ ንብ፣ አሜሪካን ሀገርም በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥሯ መቀነሱን ጥናቶች አመልክተዋል።  ኢትዮጵያ ውስጥም እንደምዕራቡ ዓለም ባይሆንም የደን መራቆት ንብን ለአደጋ እያጋለጣት መሆኑ ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/3LTcM
Honigbiene
ምስል picture-alliance/blickwinkel/K. Wothe

«የደን መራቆት እና ኬሚካሎች ዋና ምክንያቶች ናቸው»

 

ከጎርጎሪዮሳዊው 2007 እስከ 2013 ዓ,ም ባሉት ጊዜያት ብቻ ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ከ10 ሚሊየን የሚበልጡ ንቦች ማለቃቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። በአውሮጳም በ17 ሃገራት ቁጥሯ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ስጋት አስከትሏል። ጤና ይስጥልኝ የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችሁ? ከምትሰጠው ጣፋች ምርት ማሯ በተጨማሪ እጸዋትን በማዳቀል የምትታወቀው ንብ ቁጥሯ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሄድ ውሎ አድሮ የተፈጥሮ ሚዛን መዛባትን ሊያስከትል እንደሚችል የሚናገሩም አሉ።

በሰሜን  አሜሪካ እና በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ማር አምራቿ ንብ በአሳሳቢ ደረጃ ከዓመት ዓመት ቁጥሯ እየቀነሰ መሆኑን የሚያመለክቱ የተለያዩ ጥናቶች እየወጡ ነው። እንደጥናቶቹ ንቦችን ለእልቂት ከዳረጉ ምክንያቶች ዋናዎቹ በየእርሻው ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች፣ በሽታ፣ እና ፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ናቸው። በሰሜናዊ ጀርመን አበቦች በሚያብቡበት ወቅት ንቦች እንደማይታዩ የሚናገሩት በፍራፍሬ ግብርና  ላይ የተሠማሩት ጀርመናዊት ወይዘሮ እጸዋት ለመዳቀል እንዲችሉ የንብ መንጋ ከጎበረቤት ኔዘርላንድስ ለማምጣት እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ።

«በየጊዜው 40 በመቶ ያህሉን የንብ መንጋ ማጣት እየተደጋገመ መጥቷል። አትክልቶቹ ሲያብቡም ሆነ አዝርዕቶች ሲያዘረዝሩ ንቦቹ የሉም። እነዚያን ንቦች ነው አሁን ያጣነው።»

Europäische Honigbiene, Gemeine Honigbiene
ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPHOTO

ይህን ችግር ለማስወገድም በእርሻው ዘርፍ የተሰማሩ ወገኖች እና ንብ አንቢዎች እንዲረዳዱ የሚያመቻች መተግበሪያ/አፕሊኬሽን  ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ውሏል። በዚህ አማካኝነት ነው ጀርመናዊቱ አርሶ አደር 500 ንቦችን ከኔዘርላንድ ማግኘት የቻሉት። ንቦቹ ከአበባው ቀስመው ለሚያዘጋጁት ማር ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ምሥጢር በሚያደርጉት የማዳቀል ጥበብም ሰዎች የሚመገቡትን እንዳያጡ የማድረግ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ይነገራል። የአሜሪካኑ ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደው አንድ ጥናት ንቦች በየዓመቱ 15 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣውን በሀገሪቱ የሚመረተውን  የምግብ እህል እንደሚያዳቅሉ ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ማር የሚያመርተው የንብ መንጋ ቁጥር እየተመናመ መሄዱ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረበትም በቅርቡ ይፋ አድርጓል።  

በሆለታ የምርምር ማዕከል ንብ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሠራው ዘርፍ የሠራው አቶ ጆኒ ግርማ፤ በዘመናዊ መንገድ ንብ በማንባት ሥራ ከተሰማራ ዓመታት ተቆጥረዋል። ወጣቶች  የአካባቢያቸዉን ደን እየጠበቁ ንብ በማንባት ሥራ ገቢ ማግኘት እንዲችሉ እያደረገ የሚገኘው የአፒስ አግሪቢዝነስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ጆኒ  አውሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ እንደሚታየው ባይሆንም ኢትዮጵያም ውስጥ የንቦች ቁጥር መቀነሱን ይናገራል።

«የንብ መንጋ ሁኔታን ስንመለከት በኢትዮጵያ ሁሉም ቦታ የመቀነስ ነገር አለ። እኛ ሀገር ያለው የመቀነስ ሁኔታ አውሮጳ ወይም ያደጉት ሃገራት ጋራ እንደምንሰማው አይደለም።»

Afghansistan Bienenzucht und Honigproduktion
ምስል picture alliance/dpa/EPA/G. Habibi

የንብ መንጋ እየቀነሰ መሄዱን  ብቻ ሳይሆን ምክንያት ሊሆን ይችላል ያለውንም አክሎ የሚገልፀው የአካባቢ ተፈጥሮን በመከባከብ ፤ በተፈጥሮ መንገድ የሚመረት የማር ምርትን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭች ገበያ ማቅረብ መጀመሩን የገለፀልን አቶ ጆኒ ግርማ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የንብ መንጋ ቀንሷል የሚለው ያለፉት ዓመታት የነበረውን በማነፃፀር ነው።

«እንግዲህ እንደሚታወቀው አርሶ አደሩ ንብ የሚያገኘው ንቡ ወልዶ እየተከፈለ ሲሄድ ነው። በባህላዊ መንገድ የሚሠራትን ቀፎ እየሰቀለ ነው ንብ የሚያገኘው በተለይ አበባ በሚያብብበት ጊዜ፤ እና የዛሬ አምስት ዓመት እና አስር ዓመት 100 ቀፎ ቢሰቅል እስከ 60ም እስከ 70ም እስከ 80ም ቀፎ ንብ ይይዝለታል በሁለት እና በሦስት አራት ወር ውስጥ ማለት ነው በአበባ ወቅት ጊዜ። አሁን ግን ያ በጣም ቀንሷል። 100 ቢሰቅል ምናልባት 30 ወይ 40ው ነው ንብ የሚይዝለት።»

ቀደም ሲል እንደተገለጸው በተለይ በአውሮጳ እና በሰሜን አሜሪካ ለንቡ መንጋ እየተመናመነ መሄድ ኬሚካሎች እና በሽታ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ከንቦች ጋር በቅርበት የሚገናኘው ባለሙያ እንዲህ ያስረዳል።

Bienensterben
ምስል Imago/Nature Picture Library/D. Woodfall

«አንዱ እና ዋናው የእጸዋቱ እየተመናመነ መሄድ ነው። አሁን ደን እንደድሮ አይደለም ያለው በተለያዩ ቦታዎች ላይ፤ አበባ በደንብ አያገኝም ንቡ በደንብ ለመራባት ማለት ነው። ሁለተኛው ቁልፍ ነገር ደግሞ ፀረ አረም ፀረ ተባይ ነው፤ በተለይ መሀል ሀገር ላይ በጣም በብዛት ነው የሚጠቀመው አርሶ አደሩ።»

እሱ በሚመራው ድርጅት ሥር በሚንቀሳቀሱ የንብ አንቢ አካባቢዎች በዓመት ሦስት ጊዜ ማር እንደሚመረት የገለፀልን የአፒስ አግሪቢዝነሥ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ፤ የማር እና ሰም ምርትን የምታስገኘው ንብ ከዚያ ያለፈ ሚና አላት የሚባለውን  በምሳሌ ያጠናክራል።

«አስቀድሞ እኔ ምርምር ማዕከል ሥሠራ ነበር፤ የንብ ምርምር ማዕከል ውስጥ ጥናቶች ነበሩን። የንቦች የማዳቀል ጥቅም ምን ያህል እንደሆነ። እናም ብርትኳን ላይ ጥናት ነበረን ፤ ጥናቱ እንዴት ነበረ፤ ከንብ ጋር በቀፎ ተደርጎ በንብ የተዳቀለ፤ ሌላው ደግሞ በክፍት ቦታ ግን ዝግ የነበረ ነበር። እናም በንብ የተዳቀለው ውኃ ያለው፤ በጣም ጣፋጭ ነው፤ ክብነቱም ትልቅ ነው።»

Afrikanische Honigbiene Apis mellifica adansonii
ምስል picture-alliance/Wildlife/M. Harvey

በገጠር አካባቢ በባህላዊ መንገድ ንብ ያነቡ የነበሩ ወገኖችን በማሰልጠን በዘመናዊ መንገድ ሥራቸውን በማከናወን የተሻለ ምርት እንዲያገኙ በማድረግ ተግባር የተሰማራው የንብ ወዳጅ፤ ዛፍ ከሌለ ንብ የለም፤ ንብ ከሌለ ጣፋቹ ማር የለም የሚል ምክሩን ከዚህ ቀደምም በዚሁ ዝግጅታችን እንዳካፈለን ይታወስ ይሆናል። የዛሬ ሁለት ዓመት ጀርመኗ ቦን ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተካሄደ እና 338 ፕሮጀክቶች ከተሳተፉበት ተፈጥሮን የሚንከባከብ ዘመናዊ የግብርና ስልት ተመራጭ ሆኖ ለተሸለመ ፕሮጀክቱ የንቦች ህልውና ወሳኝ ነው። እንዲህ ለአደጋ የተጋለጠችውን ንብ ለመጠበቅ በግልም ሆነ ለገበያ አልመው ንብ በማንባት ተግባር የተሰማሩ ወገኖች እና አርሶ አደሮች ተቀናጅተው መሥራት እንደሚኖርባቸው ይመክራል።

በአውሮጳም ሆነ በሰሜን አሜሪካ በተለይ በቀዝቃዛው የክረምት ወራት ቁጥራቸው በጣም እንደሚቀንስ የሚነገረው ንቦች፤ አካባቢያቸው ለኑሯቸው ካልተመቻቸ በፀደይ እና በጋው ወቅትም ተመናምነው እንደሚታዩ ነው ጥናቶች ያሳዩት። ማር ጋጋሪዋ ንብ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጉዳት መዳረጓ እንዲቀንስ ኬሚካልን በእርሻ ቦታ የመጠቀሙ ልማድ እንዲታሰብበት የመከረው ከንብ ጋር ቅርበት ያለው ባለሙያ ደንን የማልማቱን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አፅንኦት ሰጥቷል። 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ