1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔ ጉዞ፤ በአፍሪቃ ደረጃ ተሸላሚ የሆነው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ ሰኔ 22 2014

«አዲስማፕ» በተባለ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራው ይህ የሞባይል መተግበሪያ በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶችን በተመለከተ ለተገልጋዮች መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፤ የአንበሳ እና ሸገር አውቶብሶችን፣የሚኒ ባስ ታክሲዎችን እና የቀላል ባቡር መስመሮችን ተከትሎ የሚሰራ ነው።

https://p.dw.com/p/4DQ2A
Äthiopien YeneGuzo App
ምስል YeneGuzo

መተግበሪያው ሰለ አዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች መረጃ ይሰጣል


በአፍሪቃ የከተሞችን የትራንስፖርት አገልግሎት አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል  የመረጃ እጥረት አንዱ ነው።ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዲጅታል ቴክኖሎጅዎችን  መጠቀም ወሳኝ  መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በአፍሪቃ ደረጃ ተሸላሚ የሆነ እና የህዝብ ማመላለሻ  አገልግሎቶችን በተመለከተ ለተገልጋዮች መረጃ በመስጠት  የአዲስ አበባ ከተማን የህዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ለማሻሻል እየሰራ የሚገኝን አንድ መተግበሪያ ያስተዋዉቃል። 
የአፍሪቃ ከተሞችን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻል የሚሰራው ፤ የዲጂታል ትራንስፖርት ለአፍሪካ/ Digital Transport for Africa/ የተባለው ድርጅት የአህጉሪቱን  ከተሞች የትራንስፖርት ዘርፍ ለማሻሻል ያግዛሉ ያላቸውን  አራት የፈጠራ ስራዎች  በዘንድሮው የአፍሪቃ የዲጂታል  የትራንስፖርት አገልግሎት  የፈጠራ ውድድር  /Africa Digital Transport Innovation Challenge/  ማሸነፋቸውን  በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
 በአፍሪቃ  ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ፤ከግል ኩባንያዎች ፣ከዩኒቨርሲቲዎች እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣100 የፈጠራ ስራዎች ተሳትፈዋል።በዚህም «ኢ ዋረን ሞብሊቲ»/eWarren Mobility/ከአቢጃ ኮትዲቯር  ፣ «ካርቱም ማፕ» /KhartouMap/ ከሱዳን ካርቱም  ፣ጎ ሜትሮ/ GoMetro /ከደቡብ አፍሪቃ ስቴለን ቦሽ እንዲሁም «የኔ ጉዞ» /YeneGuzo/  መተግበሪያ ከኢትዮጵያ አዲስ አበባ አሸናፊዎች ሆነዋል።
«የኔጉዞ» የሞባይል መተግበሪያ  በአዲስ አበባ ከተማ  የህዝብ ማመላለሻ  አገልግሎቶችን በተመለከተ ለተገልጋዮች  መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፤ የተሰራውም «አዲስማፕ» በተባለ   ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።የኩባንያው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አልዓዛር ተክሌ እንደሚሉት መተግበሪያው የአንበሳ እና ሸገር አውቶብሶችን፣የሚኒ ባስ ታክሲዎችን እና የቀላል ባቡር መስመሮችን ተከትሎ የሚሰራ ነው።

Äthiopien YeneGuzo App
ምስል Ato Alazar Tekle/YeneGuzo

መተግበሪያው ከ«ጎግል ፕሌይ»  በነጻ የሚጫን ሲሆን፤ ብዙ ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ለማድረግም ከበይነ-ገፅ ማውረድም ይቻላል።አጠቃቀሙም GPS የተባለውን ዓለም አቀፍ አቅጣጫ ጠቋሚ ዘዴ ተከትሎ ነው። 
ሃላፊው እንደሚሉት በመተግበሪያው ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ቦታ እንዲመርጡም  የቦታ አማራጮችን ዝርዝር ይሰጣል። ከዚህ  በተጨማሪ መተግበሪያው አሁን የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋት ዕቅድ መያዙንም  ገልፀዋል። ይህም የፈጠራ ስራውን በውድድሩ አሸናፊ እንዲሆን አድርጎታል። 
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑት አራቱ  የፈጠራ ስራዎች  እያንዳንዳቸው  የ30,000 የአሜሪካ ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን፤ ሽልማቱም በፈጠራ ስራዎቹ ላይ  አዳዲስ ማሻሻያዎች እንዲካተቱ ለማድረግ  የሚያግዝ ነው።በዚህ መሰረት «የኔ ጌዞ» መተግበሪያን ለማሻሻል እና ለተጠቃሚዎች በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱን አቶ አልዓዛር ገልፀዋል።

Äthiopien YeneGuzo App
ምስል YeneGuzo

«የኔ ጉዞ» መተግበሪያ የሚሰራው በአማርኛ እና በእንግሊዥኛ ቋንቋዎች ሲሆን ሌሎች ቋንቋዎችን ለማካተት እንዲሁም ያለበይነ መረብ ግንኙነት እንዲሰራ ለማድረግ በአዲሱ መርሃ ግብር ዕቅድ ተይዟል። ክፍት የመንገድ ካርታ/OpenStreetMap/ መረጃዎችን እና ምንጮችን/Turfi/ ሶፍት ዌሮችን በመጠቀም የተሰራ በመሆኑም መተግበሪያውን  ለማሻሻልም ክፍት ነው።ከዚህ ባሻገር  መተግበሪያው ተጠቃሚዎች ግብረ መልስ የሚሰጡበት አማራጭ ያለው በመሆኑ፤የተሰበሰቡ አስተያየቶችን በማካተት ማሻሻያ ይደረግበታል።
 መረጃዎች እንሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት  በአፍሪካ  ደረጃውን በጠበቀ እና በስርዓት የተደራጄ  የህዝብ ማመላለሻ  አሰራር ያላቸው ከተሞች በጣም ጥቂት ናቸው።በዚህ የተነሳ በአህጉሪቱ መቶ ሚሊዮን በላይ  በከተማ የሚኖሩ  ሰዎች የመጓጓዣ አገልግሎትን በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ የላቸውም። ይህ የመረጃ ክፍተትም  የዘርፉን አገልግሎት ዘመናዊ ለማድረግ እና ለማሻሻል ትልቅ እንቅፋት ነው።ይህንን ችግር ለመፍታት  ታዲያ አጋዥ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው።ባለሙያው እንደሚሉት «የኔጉዞ» መተግበሪያን የወለደውም በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው  ይህ መሰሉ ችግር ነው።ያም ሆኖ  ከ5 ነጥብ 2 በላይ ህዝብ  በሚኖርባት አዲስ አበባ  በዘመናዊ መልኩ የተደራጄ የመንገዶች እና የቦታ ስሞች ወይም ቁጥሮች የሉም።ይህ ችግር በአገልግሎት አሰጣጡ ረገድ እንቅፋት አልፈጠረም ወይ? ለአቶ አልዓዛር ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር።

Äthiopien YeneGuzo App
ምስል YeneGuzo

«ከሱ ጋር በተያያዘ ምንድነው ያደረግነው።«ኦፊሻሊ »የትራንስፖርት መስመሮች የሚሰሩት ዋናዋና በሚባሉ መንገዶችን እና መስመሮች ተከትለው ስለሆነ ፤ቢያንስ እነሱን በታፔላም በምንም የተሰጡ  ህብረተሰቡ ለጊዜው የሚጠቀምባቸው የመንገድ ስሞች አሉ። በአፍሪካ ከተሞች ስም የተሰየሙ። እነሱን «ማፑ» ላይ አካተናል።» በማለት በቅርብ ጊዜ የተሰየሙ መንገዶች በመተግበሪያው መካተታቸውን ገልፀዋል።
 ከዚህ በተጨማሪ ለህብረተሰቡ በተለምዶ የሚያውቃቸው የመንደር ስሞችን በዘመናዊ የሚጠሩትን ጨምሮ እንዲሁም  የታክሲ ፌርማታዎች መካተታቸውን አብራርተዋል።
 «በቅርቡ የተሰሩ ከአንድ ሺህ በላይ  ቋሚ የአውቶቡስ ፌርማታዎች ደግሞ ስም አላቸው እነሱንም እንጠቀማለን»ብለዋል።
እንደ አቶ አልዓዛር «የኔ ጉዞ» ከሶስት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገ መተግበሪያ ቢሆንም የተጠቃሚዎች ቁጥር  ብዙ አይደለም።በመሆኑም ሽልማቱ የፈጠረውን አቅም ተጠቅመው ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት እና ስለ መተግበሪያው   የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት  የተጠቃሚውን ቁጥር ለመጨመር፣ ግንዛቤውንም  ለማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ለማስፋት መታቀዱንም ጨምረው ገልፀዋል።

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ