1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ 60ኛ ዓመት ነጻነት በምጣኔ ሐብት ድቀት

ቅዳሜ፣ መስከረም 23 2013

ናይጄሪያ በብሪታንያ ቅኝ ግዛት ዘመን፤ ስር የሰደደው የከፋፍለህ ግዛ መርኅ መርዝ ዛሬም ውስጧ ዘልቆ ያሰቃያታል። በናይጀሪያ ግዛቶች እና ጎሣዎች መካከልም ስር የሰደደ ጥላቻ ለበርካታ ንጹሐን ዜጎች እልቂት ሰበብ ኾኗል። ቦኮሃራም የተሰኘው የእስልምና አክራሪ ቡድን ሌላው የናይጀሪያውያን ጠንቅ ኾኖ ለበርካቶች ኅልፈት ሰበብነቱ አልተገታም።

https://p.dw.com/p/3jMRw
Erdöllraffinerie in Nigeria
ምስል Construction Photography/Photoshot/picture alliance

ናይጀሪያ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት ተጋርጦባታል

ናይጀሪያ ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጣችበትን 60ኛ ዓመት ባሳለፍነው ሐሙስ፤ መስከረም 21 ቀን፣ 2013 ዓመተ ምሕረት ቀዝቀዝ ባለ ስሜት አክብራለች። በሀገሪቱ የተንሰራፋው የምጣኔ ሐብት ድቀት እና የጸጥታ ችግር የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ተደምሮበት ይኽ ልዩ ቀን በደመቀ ሳይኾን በተገደበ መልኩ እንዲከበር አስገድዷል።

በነጻነት ቀኑ የሀገሪቱ ርእሰ ብሔር ሙሐማዱ ቡሃሪ ለ«ብሔራዊ እርቅ» ጥሪ አስተላልፈዋል። የአፍና የአፍንጫ ጭምብል አጥልቀው በመዲናዪቱ አቡጃ ስታዲየም የተገኙት የ77 ዓመቱ ሙሐማዱ ቡሃሪ በነፃነት ቀኑ ወታደራዊ ሰልፍ ተመልክተዋል።

ቀደም ሲል በቴሌቪዥን ባሰሙት መልእክት ደግሞ፦ ናይጀሪያ «እንደ እድል ኾኖ ሰፊ እና ትልቅ የጥቁሮች ሀገር ኾና» ነበር ሲሉ በቊጭት ተሞልተው ተናግረዋል። «ብርቱ ጋሬጣ ግን ተደቅኖባታል» ሲሉም አክለዋል። የናይጀሪያ ምጣኔ ሐብት በዓለም ዙሪያ የኤኮኖሚ ቀውስ ከገጠማቸው ሃገራት ተርታ የሚመደብ መኾኑንም አጽንዖት ሰጥተውበታል።

Nigeria Democracy Day 2019
ምስል Reuters/A. Sotunde

ናይጀሪያ ከነጻነት ማግስት ወዲህ የነዳጅ ገጸ በረከቷን ተገን አድርጋ ምጣኔ ሐብቷ ላይ ለውጦችን ዐሳይታ ነበር። የምጣኔ ሐብቱ ግን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት ማድረጉ ሳይጎዳው አልቀረም። በካዱና ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ ተንታኝ የኾኑት ቱኩር አብዱልቃድር የናይጀሪያ ምጣኔ ሐብት ከነዳጅ ማውጣት እና ሽያጭ ባለፈም ለመሰባጠር ዳተኛ መኾኑ እንደጎዳው ይናገራሉ። በብርቱ ከተጎዳው የነዳጅ ማውጣት ዘርፍ ባሻገር ተጀምረው የነበሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች አንድም በኪሳራ አለያም በተንኮታኮተ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ባለሞያው ተናግረዋል።

«ከአርባ ዓመታት በፊት አንዳንዶቻችን ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለን የአንድ ናይራ ዋጋ አንድ ዶላር አካባቢ ነበር። ዛሬ የምናወራው በናይጀሪያ አንድ ዶላር 500 ናይራ አካባቢ እንደሚመነዘር ነው። እነዚያ ኢንዱስትሪዎች በመላ ለምሳሌ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ሞቷል ማለት ይቻላል።»

የእርስ በእርስ ግጭት፤ ድህነት እና እስልምና አክራሪነት ተደማምረው ናይጄሪያ ባለፉት ስድሳ ዓመታት የሚገባትን ያኽል እንዳታድግ ማነቆ መኾናቸው ይነገራል። የምጣኔ ሐብት ጋዜጠኛው ኢግናቲዎስ ቹክዉ በናይጄሪያ የምጣኔ ሐብት ቀውስ መከሰቱን በሚገባ ይገነዘባሉ። እንደእሳቸው ናይጄሪያን የሚያስተዳድረው የቡሃሪ መንግሥት የምጣኔ ሐብት ችግሩን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀበትም። ለመፍትኄው ግን መንግስት በርካታ ምክንያቶች ተግዳሮት ኾነውበታል ባይ ናቸው።

«የቡሃሪ መንግሥት ብቅ ያለው ልክ የሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይ ስብጥር ሲጀመር ነው፤ ግን ወዲያው ነው በምጣኔ ሐብት ቀውስ የተዘፈቅነው። ከምጣኔ ሐብት ቀውሱ ለመውጣት ለኹለት ዓመታት ታግለዋል። መጀመሪያ አካባቢ ላይ ትንሽ ለውጥ ማምጣት ችለው ነበር። ከታች ወደላይ ምጣኔ ሐብቱ ትንሽ ብቅ እንዲል አስችለው ነበር። ከክስረት፤ ወደ እዳ አልባነት፤ ከዚያም ወደትርፋማነት እና የ1,5 ምጣኔ ሐብት እድገት ዐሳይተው ነበር። በዚህ ዓመት ወደ 2,5 ከፍ እናደርገዋለን ሲሉም ተመኝተው ነበር። ከዚያ ተከትሎ የመጣው የዓለም ምጣኔ ሐብትን ያናጋው የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሺኝ ሲኾን ያም የነዳጅ ገበያውን ዋነኛ ሰለባ አድርጎታል። ለእኔ አስቸጋሪ መኾኑ ይታየኛል፤ ግን ዋናው ነገር ምንድን ነው፤ ምጣኔ ሐብቱን ለማሰባጠር የሚፈልግ አለ ወይ የሚለው ነው። አዎ ያን ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነቱ አለ።»

በእርግጥም በዋናነት የነዳጅ ሽያጭ ላይ የተመሰረተው የናይጄሪያ ምጣኔ ሐብት በነዳጅ ዋጋ መቀነስ እና በኮሮና መስፋፋት ምክንያት ብርቱ ጉዳት ደርሶበታል። ናይጄሪያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ሸቀጦች እና ምርቶች ከምታገኘው ገቢ 95 በመቶው የሚሰበሰበው ከድፍድፍ ነዳጅ እና ከመሬት ውስጥ ጋዝ ሽያጭ ነው። ከነዚህ በሚገኘው ገቢም የሀገሪቱ 40 ከመቶ በጀት ተመስርቷል።

የናይጀሪያ ርእሰ ብሔር ሙሐማዱ ቡሃሪ በሃገራቸው የተከሰተውን የምጣኔ ሐብት እና ሌሎች ችግሮች ለመቅረፍ ቊርጠኛ መኾናቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ። በናይጀሬያ የነጻነት ቀን ባሰሙት ንግግር፦ «ዛሬ ከ200 ሚሊዮን ከላቀው የሕዝብ ቊጥር ጋር በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነውብናል» ብለዋል። ለዚህ ኹሉ መፍትኄው በውሸት ትርክቶች የተጠናከሩ ቅራኔዎችን አክሽፎ ከልብ እርቀ ሰለም ማውረድ አስፈላጊ መኾኑንም አስምረውበታል።

Nigeria Borno State Monguno | Anschlag von Extremisten
ምስል picture-alliance/AP Photo/ocha/Undss

ናይጄሪያ በብሪታንያ ቅኝ ግዛት ዘመን፤ ስር የሰደደው የከፋፍለህ ግዛ መርኅ መርዝ ዛሬም ውስጧ ዘልቆ ያሰቃያታል። በናይጀሪያ ግዛቶች እና ጎሣዎች መካከልም ስር የሰደደ ጥላቻ ለበርካታ ንጹሐን ዜጎች እልቂት ሰበብ ኾኗል። ናይጄሪያ በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት እና የሚሊዮኖችን ሕይወት በቀጠፈ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ብሎም አምባገነን አገዛዝም ፍዳዋን በልታለች። ላለፉት ዐስር ዓመታት ቦኮሃራም የተሰኘው የእስልምና አክራሪ ቡድን ሌላው የናይጀሪያውያን ጠንቅ ኾኖ ለበርካቶች ኅልፈት ሰበብነቱ አልተገታም። ቡድኑ በፈጠረው ሽብር ከኹለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው ለመሰደድ ተገደዋል።

ከዚያም ባሻገር ናይጄሪያ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ተለይታ እስክትታወቅበት ድረስ ሙስና ቀፍድዶ ይዟታል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1960 ጀምሮ ሀገሪቱ በሙስና ብቻ 326 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች። ይኽ ሁሉ ተደማምሮ ናይጄሪያ በነጻነት ዘመን ያገኘችው ተስፋዋ ከስድሳ ዓመታት በኋላ ዛሬ ደብዝዞ ይታያል።

ለፖለቲካ ሣይንስ ተንታኙ ቱኩር አብዱልቃድር በነጻነት ማግስት አቆጥቁጠው የነበሩ ግዙፍ የምጣኔ ሐብት እመርታዎች ያልተንኮታኮቱት ባሉበት ቀጥ ብለዋል።

«በኹለተኛው ሪፐብሊክ ዘመን ግዙፍ የኢንዱስትሪ አብዮት ነበር ያቀጣጠልነው። በተለይ በብረት እና ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ። ናይጄሪያ በተለይ በብረት ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ አብዮት ማድረግ ፈልጋ ነበር። በአፍሪቃ ግዙፉ የብረት ኢንዱስትሪ አጃኮታ ውስጥ አቋቊመን ነበር፤ አኹን ሞቷል ማለት ይቻላል። ሌሎች የብረታት ብረት ኢንዱስትሪዎች በሰሜን ምዕራብ የናይጀሪያ ክፍል ነበሩን። በመካከለናው ናይጄሪያ አንድ፤ በደቡብ ምዕራብም ሌላ አንድ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ነበረን። በርካታ ኢንዱስትሪዎች ነበሩን። እነዚህ ኩሉ ኩባንያዎች ግን በአሁኑ ወቅት አይሠሩም። ኪሣራ ገጥሟቸዋል። ድምጥማጣቸው ጠፍቷል ማለት ይቻላል።»

Nigeria Landwirtschaft Bauern
ምስል Luis Tato/AFP

በናይጀሪያ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ የሪፐብሊክ ዘመኖች የነበሩት ለውጦች በርካታ ናይጄሪያውያን በአኹኑ ወቅት እያሰቡ የሚቆጩባቸው ናቸው። የመጀመሪያው ሪፐብሊክ ሀገሪቱ ከብሪታንያ ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ዓመታት የታየው ወቅት ነው። ይኽ ዘመን በሀገሪቱ የመጀመሪያው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲያከትም፤ በናይጄሪያውያን ዘንድ የነበረው የለውጥ ተስፋም አብሮ አክትሞ ቆይቷል። የፕሬዚደንት ሼሁ ሻጋሪ መንግሥት ናይጄሪያ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት የተላቀቀችበትን 19ኛ ዓመት የነጻነት በዓል በምታከብርበት ቀን ሥልጣን ሲረከብ የናይጄሪያ ኹለተኛ ሪፐብሊክ ይጀምራል። ዘመኑም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1979 ነበር። ይኽም ሪፐብሊክ ከአራት ዓመታት በኋላ ያከትማል።

በተለይ በዚህ በኹለተኛው ሪፐብሊክ ይታይ የነበረው የባቡር መጓጓዣ ዘርፍ እድገት፤ ምርቶች በገፍ ወደ ውጭ ሃገራት እንዲላኩ አስችሎ የነበረው የግብርናው ዘርፍ መቀዛቀዝ እንደ ፖለቲካ ሣይንስ ተንታኙ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ናቸው። እናም የናይጄሪያ መንግሥት ከግማሽ በላይ ነዋሪው ከድህነት በታች ከሚገፋው ሕይወት ወጥቶ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር የሀገሪቱ የጸጥታ ኹኔታ ባፋጣኝ ለውጥ ሊደረግበት ይገባል።

ምጣኔ ሐብቱ ላይም ፈጣን ማሻሻያ ካልተደረገ በነዳጅ ሐብት የበለጸገችው ናይጄሪያ ውስጥ ነዋሪው ከምንጊዜውም በላይ በውድ ዋጋ ነዳጅ መግዛቱ የፈጠረበትን ቊጣ ማቀዝቀዝ ይከብዳል። በናይጀሪያ 60ኛ ዓመት የነጻነት ቀን ዋዜማ የሀገሪቱ መንግሥት ቢያንስ የቤንዚን ዋጋ 15 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል። ናይጄሪያውያን ላይ የተደቀኑትን ሌሎች ብርቱ ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ እና መፍትኄ ለመፈለግ ግን መንግሥት ሌላ የነፃነት ቀን መጠበቅ እንደሌለበት ተንታኞች ይናገራሉ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ