1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናሚቢያ አረንጓዴ ሃይድሮጂን የኃይል ምንጭ ለአዉሮጳ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 20 2014

አውሮጳ ከሩሲያ በነዳጅና በጋዝ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማቆም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የደቡብ አፍሪቃዊትዋ ሀገር ናሚቢያ በነዳጁ ዘርፍ አዉሮጳን መርዳት እችላለሁ እያለች ነዉ። ናሚቢያ ይህን ያሳወቀችዉ ባለፈው ሳምንት ዳቮስ ስዊዘርላንድ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የኤኮኖሚ መድረክ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4BzTR
Weltwirtschaftsforum in Davos | Namibia
ምስል DW

ናሚቢያ በየዓመቱ እስከ 300,000 ቶን አረንጓዴ ሃይድሮጅን ለማምረት እቅድ ይዛለች

የአውሮጳ ህብረት ከሩሲያ በነዳጅና በጋዝ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማቆም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የደቡብ አፍሪቃዊትዋ  ሀገር ናሚቢያ በነዳጁ ዘርፍ የአዉሮጳ ህብረትን እኔ መርዳት እችላለሁ እያለች ነዉ። ናሚቢያ ይህን ያሳወቀችዉ ባለፈው ሳምንት ዳቮስ ስዊዘርላንድ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ሲሆን ልረዳ እችላለሁ ብላ የቀረበች የመጀመርያዋ ሃገርም ተብላለች።

H2 Hydrogen Molekül Symbolbild
ምስል Alexander Limbach/imago images

ናሚቢያ ከምትሸጣቸዉ ሀብቶችዋ መካከል የፀሐይ ብርሃን እና የንፋስ ኃይል ይገኝበታል። በዓመት ከሦስት ሺህ ሰዓት በላይ የፀሀይ ብርኃን ከሚገኝባቸዉ የዓለማችን ደረቅ ሀገራት መካከል ናሚቢያ አንዷ ናት። ናሚቢያ ፀሐይና ነፋስን በመጠቀም ከባሕር ውኃ ውስጥ እንደ ኤሌትሪክ ኃይል የሚሰጠዉን አረንጓዴ ሃይድሮጅን የሚባለውን ንጥረ ነገር ለማዉጣት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። የአውሮጳ ህብረት ከከርሰ ምድር የሚገኝ ነዳጅ ላይ ያለውን ፍላጎት እና ጥገኝነት በመቀነስ ከባሕር ውኃ ውስጥ የሚገኝ አረንጓዴ ሃይድሮጅን የተባለ ለከባቢ አየር ጥራት እጅግ ምቹ የሆነ የኃይል ማመንጫ እየፈለገ መሆኑን አታዉቋል።  

የናሚቢያ የግሪን ሃይድሮጂን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ኦቤት ካንጆዜ፤ ዳቮስ፣ ስዊትዘርላንድ ላይ በተካሄደዉ በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ሃገራችን ይህን የኃይል ምንጭ ለመነገድ ፅኑ ፍላጎት አላት ብለዋል።

«ይህች ሃገር ይህ ሀብት ያላት  ነች። ነገሮችን በቁም ነገር የምትይዝ ሃገርም ናት። እዚህም ለንግድ ዝግጁ ነን ብለን  በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ መድረክ ስብሰባ ላይ ተገኝተናል።  ይህ ነው የሽያጭ ውጥናችን ።»

አረንጓዴ ሃይድሮጂን የተባለዉ የኃይል ምንጭ የሚመረተው ከውኃ ዉስጥ የሃይድሮጂን ሞለኪል የተባለዉን ንጥረ ነገር በመለየት ነው። ይህ አይነቱ የኃይል ምንጭ የአየር ንብረትን ከብክለት ለማዳን የአዉሮጳ ህብረት እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2050 ዓም ድረስ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል ያቀደው ቁልፍ ምሰሶም ነው። በዚህም መሰረት ህብረቱ ከከርሰምድር የሚገኝ የነዳጅ ኃይልን ከመጠቀም እንዲሁም ራሱን ከሩሲያ ነዳጅና እና ጋዝ ግዢ ጥገና ከመሆን ይገላግላል።

በዚህ ወር የአውሮጳ ኮሚሽን የከርሰ ምድር ነዳጆችን የሚጠቀሙ በርካታ ኢንዱስትሪዎችና ተሽከርካሪዎችን ለመተካት በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ቶን ታዳሽ ሃይድሮጅን የኃይል ምንጭን ከውጭ ለማስገባት እንደሚፈልግ ገልጿል።

የናሚቢያ ባለስልጣናት ይህን የአዉሮጳን ፍላጎት ወደ ሃገራቸዉ በማምጣት ጓጉተው ነበር። ባለስልጣናቱ ባለፉት ወራቶች በርሊንና ፓሪስን ጨምሮ የአውሮጳ ሃገራት ዋና ዋና ከተሞችን ጎብኝተዋል። ጠቃሚ ዉይይቶችንም አካሂደዋል። ናሚቢያ እንደ ጀርመን፤  ቤልጅየምና ኔዘርላንድ ካሉ ሃገራት ባለሥልጣናት ጋር ታዳሽ ሃይድሮጅን የኃይል ምንጭን ለመግዛት  ፍላጎት እንዳለ የሚገልጽ መግለጫን አግኝታለች። የናሚቢያ ብሔራዊ የፕላን ኮሚሽንም መሪ የሆኑት ካንጆዚ፣ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ ፍላጎቱና ጥያቄው እንደጨመረ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

በርሊን የሚገኘዉ የጀርመን መንግሥት የቀድሞ ቅኝ ግዛት የሆነችዉ ደቡብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር ናሚቢያ ወደፊት ከዉኃ የሚገኝ የኃይል ምንጭን እንድታመርት ለመርዳት 40 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቷል ። የጀርመን መንግሥት ከናሚቢያ አንድ ኪሎ ሃይድሮጅን ከአንድ ይሮ ከሃምሳ ሳንቲም እስከ ሁለት ዩሮ ለመግዛት እንደሚችል ተስፋ አድርጓል። 

"በናሚቢያ የተመረተዉ የሃይድሮጅን የኃይል ምንጭ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረዉ እና በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ይሆናል። ከፍተኛ መጠን ያለው ሃይድሮጅን ያስፈልገናል። በፍጥነትና በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት እንፈልጋለን። ናሚቢያ በከፍተኛ መጠን በዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብ ትችላለች።"

Weltwirtschaftsforum in Davos | Namibia
ምስል DW

ሲሉ ባለፈዉ ነሐሴ ወር የተናገሩት የቀድሞው የጀርመን የምርምር ሚኒስትር አንያ ካርሊቼክ ናቸዉ።

ናሚቢያ በአካባቢዋ ፖለቲካዊ መረጋጋት ከሚታይባቸዉ ደቡባዊ አፍሪቃ አገሮች መካከል አንዷ ናት። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢኮኖሚው ዘርፍ ስትታገል የቆየችም ሃገር ናት። ይህ የሆነው በናሚቢያ የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ፣ በተከሰተ ድርቅ እና በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ነው። አሁን ደግሞ በዩክሬን ያለው ጦርነት በናሚቢያ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ  እንዲኖርና የምግብ እጥረት እንዲከሰት ዳርጓል። ናሚቢያ የሚያስፈልጋትን አብዛኛውን ነገር ለማሟላት ከውጭ በሚመጣ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚም ነች። ናሚቢያ አሁን ልታመርት የተዘጋጀችዉ አረንጓዴ ሃይድሮጂን የኃይል ምንጭ፤ የሃገሪቱን ኦኮኖሚ  ለማጎልበት ይረዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።  

ናሚቢያ በደቡብ ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍል የመጀመሪያውን አረንጓዴ ሃይድሮጂን ፕሮጀክት ለመሥራት የጀርመንን ሃይድሮጂን ኢነርጂ ማምረቻ አይነት መርጣለች። ፕሮጀክቱ ውሎ አድሮ በየዓመቱ እስከ 300,000 ቶን የሚደርስ አረንጓዴ ሃይድሮጅን የሃይል ምንጭ ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ