1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 3 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 3 2013

ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና በእንባ ተውጦ መሰናበቱ በርካታ አድናቂዎቹን ሆድ አስብሷል። ምንም እንኳን ቀደም ሲል ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ጋር በዝውውር ምክንያት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ለ21 ዓመታት ከልጅነቱ አንስቶ ክፉውንም ደጉንም ካየበት ቡድን መሰናበቱ ግን ቀላል አይመስልም።

https://p.dw.com/p/3ylZS
Spanien Lionel Messi
ምስል Pau Barrena/Getty Images/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

እሁድ ነሐሴ 2 ቀን፣ 2013 ዓ.ም በይፋ በተጠናቀቀው የቶኪዮ ኦሎምፒክ የ2020 ውድድር በአራት አትኬቶች ከተገኘው ሜዳሊያ ውጪ የኢትዮጵያ ቡድን በጋራ እጅግ ደካማ የሚባል ውጤት በመያዝ አጠናቋል። በሜዳሊያ ሰንጠረዡም 56ኛ ደረጃን ይዞ ነው ውድድሩን የቋጨው። ገና ከመነሻው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የነበረው ውዝግብ ባልተፈታበት ኹኔታ ከውድድሩ መክፈቻ አንስቶ የኢትዮጵያ ቡድን ደካማ አቀራረብ ይዞ ታይቷል።  

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ምንም እንኳን በአራት አትሌቶች የተናጠል ድንቅ ውጤት ቢያስመዘግብም፤ እንደ ቡድን ግን ዘንድሮ በርካቶችን እጅግ ያበሳጨ እና ያሳፈረ ውጤትን ይዞ አጠናቋል። አንገስ ቶሮውድ የባለፈውን እና የ2020ውን ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከሰሐራ በታች ለሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት የቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዘገባ ሠርቷል።  በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ቡድን አጀማመሩ ድንቅ መሆኑ ብዙ እንድንጠብቅ አድርጎን ነበር ይላል የስፖርት ጋዜጠኛው እና ተንታኙ አንገስ።  

Japan Tokio | Olympische Spiele 2020 | Selemon Barega
ምስል The Yomiuri Shimbun/AP Images/picture alliance

«ቡድኑ አጀማመሩ ላይ ሰለሞን ባረጋ ባስገኘው የወርቅ ሜዳሊያ ድንቅ የሚባል ነበር። እጅግ በጣም አስደማሚ ውጤት ነበር፤ ምክንያቱም ሰለሞን የተፋለመው የዓለም ክብረወሰን ባለቤት እና የዓለማችን ፈጣን ከኾነው የዩጋንዳው አትሌት ጋር ነበር።»

በእርግጥም አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የቶክዮ ኦሎምፒክ የፍጻሜ ፉክክር በስተመጨረሻ ላይ በድንቅ ኹኔታ ተስፈንጥሮ በመውጣት ያስገኘው ድል ከበርካቶች አዕምሮ የማይጠፋ ነው። የዓለማችን ፈጣኑ አትሌት እና የወርቅ ሜዳሊያውን ያገኛል ተብሎ ተገምቶለት የነበረው ጆሹዋ ቼፕቴጊ ለኢትዮጵያዊው ዕንቁ እጁን ሰጥቷል። እናም ይላል አንገስ።

«እናም በእውነቱ የአጨራረስ ቴክኒኩን ያገኘበት ስልት ሙሉ ለሙሉ ትክክል የሚባል ነው። ለኢትዮጵያም ድንቅ ነው። በተለይ ያን የእነ ኃይለ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለን አመርቂ የድል ዘመን አስታውሶኛል። ሁለቱም የብሪታንያው ሞ ፋራህ ከመምጣቱ በፊት በተከታታይ በኦሎምፒክ ያስገኙትን ድል አስታውሶኛል። »

«ያ ጥሩ ነገር እንድናስብ ተስፋ አጭሮ ነበር። ግን እንዳለመታደል ኾኖ ግን ኢትዮጵያ ያገኘችው ብቸኛ ወርቅ ያ ብቻ ነው። የቀረው ጊዜ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትግል ነበር ማለት ይቻላል።»

ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ውድድሩ በሰለሞን ባረጋ ከተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ ውጪ በለሜቻ ግርማ በ3000 ሺሕ ሜትር የመሰናክል ውድድር ሁለተኛ በመውጣት አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። ይህ ውጤትም እጅግ የሚደነቅ ነው። በጉዳፍ ጸጋዬ እና ለተሰንበት ግደይ ደግሞ ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በጠአቃላይ ውድድሩን በአራት ሜዳሊያዎች ነው ያጠናቀቀችው።

Olympische Spiele Tokio | Gudaf Tsegay Äthiopien
ምስል INA FASSBENDER/AFP

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት ሲፈን ሀሰን አሸናፊ በኾነችበት ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ 3ኛ በመሆን የነሐስ ተሸላሚ ብትሆንም ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት ነበር። በውድድሩም ብርቱ እና ልብ የሚነካ ፉክክር ዐሳይታለች። በ5ሺህ ሜትር የጉዳፍ ጸጋዬ ፉክክርም እጅግ የሚበረታታ ነው። ጋዜጠኛ አንገስ ተጨማሪ ታዋቂ አትሌቶች ዘንድሮ በቡድኑ አለመታቀፋቸው ግራ እንዳጋባው ይናገራል።

Olympische Spiele Tokio | Gudaf Tsegay Äthiopien
ምስል INA FASSBENDER/AFP

«በአምስት ሺህ ሜትር በተደጋጋሚ የዓለም ባለድል የኾነው ሙክታር እድሪስ በውድድሩ አልነበረም። ዘንድሮ ለምን ተሳታፊ እንዳልኾነ ይገባኛል። በማጣሪያው ወቅት መስፈርቱን ማሟላት ስላልቻለ ነው። ግን ማጣሪያው ለምን በበጋ ወቅት እጅግ በጊዜ እንደተደረገ ሊገባኝ አልቻለም። ሌሎች ሃገራት እዳደረጉት በርካታ ውድድሮች ከተከናወኑ በኋላ ማጣሪያው ዘግየት ብሎ ቢሆን ኖሮ የተደረገው በርካታ አትሌቶች ብቃት እና ዝግጁነት ሊኖራቸው ይችል ነበር ማለት ይቻላል። በማራቶኑም ዘርፍ በጣም አስቀያሚ በኾነ መልኩ ነው የተጠናቀቀው። ይመስለኛል በለንደን ማራቶን የሴቶች ፉክክር ወቅትም ሦስቱም አትሌቶች በዚያ ማራቶን ውድድሩን አቋርጠው ነበር።  እናም ያ ታሪክ አሁንም ተደግሟል። ስለዚህ በአትሌቶቹ ዝግጅት እና መሰናዶ ላይ አንዳች የኾነ ልክ ያልኾነ ነገር አለ።»

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎች በሜዳሊያ ሠንጠረዡ 56ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ተፎካካሪ ጎረቤት ኬንያ እጅግ በተሻለ ውጤት 19ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። አራት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነሐስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው ኬንያ በረዥም ርቀት ውድድሮች ላይ ብርቱ ተፎካካሪዎቿ ብቃታቸውን አስመስክረዋል። ኬንያን ከመላው ዓለም በ11 ሜዳሊያ 18ኛ ደረጃ ይዞ የሚቀድማት የቼክ ሪፐብሊክ ቡድን ሲሆን፤ ከአፍሪቃ ግን የሚስተካከላት አልተገኘው። ኬንያዎች ያልተጠበቀ ውጤት ማግኘታቸውን አንገስ ይናገራል።

Olympia 2020 Tokio | Russland vs Türkei | Volleyball
ምስል Carlos Garcia Rawlins/REUTERS

«እጅግ የሚገርም ነው በእውነቱ። ምክንያቱም በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ኬንያውያን በተቃራኒው ሊጨነቁ ይገባል ብዬ ነበር ሳስብ የነበረው። መጀመሪያ አካባቢ ላይ ሜዳሊያ ማግኘት ተስኗቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በድንገት አራት ሜዳሊያዎችን አገኙ። ኢማኑዌል ኮሪዬ በ800 ሜትር ርቀት ድንቅ ውጤት አመጣ። ለኢትዮጵያውያን አድማጮች እንደምናገር ይገባኛል ግን ከዓለማችን ድንቅ አትሌቶች አንዷ የኾነችው ፌይዝ ኪፕዬጎን በ500 ሜትር ርቀት ውድድር የቀድሞ ድሏን አስጠብቃለች። እናም ይህች አትሌት  በ500 ሜትር የኦሎምፒክ ድሏን በማስጠበቅ ከወንዶች የ800 ሜትር ባለድሉ ዴቪድ ሮዲሺያ በኋላ ሁለተኛዋ አትሌት ናት። በእርግጥ በማራቶን ደግሞ ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ፔሬዝ ጄፕ ቺርቺዬር አለችልህ። ኤሊውድ ቺፕቾጌም አለልህ። ኤሊውድ ቺፕቾጌ ላይ የሚደርስ አትሌት የሚኖር አይመስለኝም። በማራቶን ዘርፍ ደረጃውን ከፍ ያደረገ ልዩ አትሌት ነው።»

የስፖርት ተንታኝ እና ጋዜጠኛው አንገስ የኢትዮጵያውያን በኦሎምፒክ የሜዳሊያ ፉክክር ጎልተው ዐለመታየታቸው አሳዛን መኾኑንንም ጠቁሟል። በአጠቃላይ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድር፦ ዩናይትድ ስቴትስ 113 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ብራታቷን ዐሳይታለች። ከአጠቃላይ ሜዳሊያዎቹ 39ኙ የወርቅ እንዲሁም 41ዱ የብር ናቸው፤ ቀሪዎቹ የነሐስ።

ቻይና ዩናይትድ ስቴትስን በመከተል በ88 የሜዳሊያ ብዛት የኹለተኛ ደረጃ አግኝታለች። 38 የወርቅ፣ 32 የብር እና 18 የነሐስ ሜዳሊያ ነው ያገኘችው። ከዚያ በመቀጠል ጃፓን በ58 ሜዳሊያዎች የሦስተኛ ደረጃን ይዛለች። 27 የወርቅ፣ 14 የብር እና 17 የነሐስ ሜዳሊያዎች እዛው አዘጋጅ ሀገሯ ጃፓን ውስጥ ቀርተዋል።

Olympia 2020 Tokio | Abschlussfeier
ምስል THOMAS PETER/REUTERS

የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድርን ለማዘጋጀት ፈረንሳይ ከጃፓን ተረክባለች። ከወዲሁም ዝግጅቷን መጀመሯ ተሰምቷል። በ2024 የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ለማሰናዳት የፈረንሳይ ቡድን ከወዲሁ ልምምድ እና ዝግጅቶችን ማድረግ መጀመሩም ተዘግቧል። ለ16 ቀናት በ33 የስፖርት አይነቶች ተከናውኖ 339 ሜዳሊያዎችን ለብቁ አትሌቶች በማጥለቅ የዘለቀው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ግጥሚያ በጀርመናዊው የዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባኅ ንግግር ተዘግቷል።

እንደአጀማመሩ ሁሉ በዳንስ እና በብራሃናት ትርዒት የተዘጋውን የኦሎምፒክ ዝግጅት ፕሬዚደንቱ፦ «የተስፋ ግጥሚያዎች የወንድማማችነት እና የሰላም» ብለውታል። ተሳታፊ ሃገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በየሀገሮቻቸው ድክመት እና ጥንካሬያቸውን የሚገማገሙበት ቀናት ከፊት ይጠብቃቸዋል።  በተለይ ከኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ይጠበቃል።

እግር ኳስ

Spanien | Pressekonferenz | Fußballer Lionel Messi
ምስል Joan Monfort/AP/picture alliance

ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች ስንወጣ፦ ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና በእንባ ተውጦ መሰናበቱ በርካታ አድናቂዎቹን ሆድ አስብሷል። ምንም እንኳን ቀደም ሲል ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ጋር በዝውውር ምክንያት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ለ21 ዓመታት ከልጅነቱ አንስቶ ክፉውንም ደጉንም ካየበት ቡድን መሰናበቱ ግን ቀላል አይመስልም። ለፈረንሳዩ ፓሪስ ሳንጃርሞ ቡድን ደጋፊዎች ግን አስደሳች ነበር። ብዙዎች ሜሲ ወደ ፓሪስ ሳንጃርሞ ሊያቀና ይችላል የሚል ግምት አሳድረዋል። እሱ በበኩሉ፦ «ገና ምንም ያረጋገጥሁት ነገር የለም» ብሏል። «በርካታ የስልክ ጥሪዎችን ፍላጎቱ ካላቸው በርካታ ቡድኖች አስተናግጄያለሁ» ያለው አርጀንቲናዊው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ፦ «ገና ሁሉኑም ነገር አልቋጨኹም እየተነጋገርን ነው» ሲልም አክሏል። የ34 ዓመቱ አጥቂ ደህና ገንዘብ ለሚከፍለው ቡድን የሁለት ዓመት ውል መፈረም ይፈልጋል። ወደ ፓሪስ ሳንጃርሞ ያቀናል የሚለው አስተያየት ግን ያመዝናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ