1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 23 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2014

የኢትዮጵያውያን ድል ስለተስተጋጋባባቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንትና አመራር ምርጫ፤ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ ቡንደስሊጋ፤ እና የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ላይ ዳሰሳ ይኖረናል።

https://p.dw.com/p/4GBdX
Bundesliga | Schalke 04 v Union Berlin
ምስል Matthias Koch/IMAGO

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለም መድረኮች ድል ተቀዳጅተዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መክፈቻው አጨቃጫቂ ቢሆንም፤ ፕሬዚደንት እና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫውን ትናንት አካኺዶ አመራሩን ሰይሟል። ከአዲስ አበባ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል። ለደቡብ አፍሪቃው ማሜሎዲ ሳንዶውንስ የሚጫወተው ኢትዮጵያዊው የእግር ኳስ አጥቂ አቡበከር ናስር ግብ በማስቆጠር ብቃቱን እያስመሰከረ ነው።  ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን ግብ አስቆጥሯል። በሳምንቱ መጨረሻ በነበረው ግጥሚያ ቦርመስን 9 ለ0 በመረምረም የግብ ጎተራ አድርጎታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ዑኒዬን ቤርሊን ሻልከን በሜዳው ጉድ ሠርቶታል። በሜዳ ቴኒስ የሴቶች ፉክክር የዓለማችን ኮከቧ ሴሬና ዊሊያምስ ዛሬ በአሜሪካ የሜዳ ቴኒስ መክፈቻ የስንብት ጨዋታዋን ታከናውናለች።

አትሌቲክስ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በነበሩ የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከጀርመን ሜክሲኮ፤ እስከ ሰሜን አየርላንድ አውስትራሊያ ድረስ በነበሩ የሩጫ ፉክክሮች በድል ተንበሽብሸዋል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ሰሜን አየርላንድ አንትሪም ውስጥ በነበረው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ጀማል ይመር ክብረወሰን በመስበር ነው ያሸነፈው። ጀማል በብሪታኒያዊው ጄኦፍሬይ ካምዎሮ ተይዞ የቆየውን በብሪታንያ ምድር የተገኘ ክብረወሰን መስበር የቻለው 00:59:03 በመሮጥ ነው። ጄኦፍሬይ ካምዎሮ እጎአ በ2016 ካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ ላይ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ፉክክር ያሸነፈው 00:59:10 በመሮጥ ነበር።  በዚሁ ውድድር ተስፋሁን አካልነው፣ 1:01.43 በመጥ የ4ኛ ደረጃን አግኝቷል። በሴቶች ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው 1:04.21 ሮጣ በማጠናቀቅ የ1ኛ ደረጃን ተቀዳጅታለች። በ39 ሰከንዶች ብቻ የተበለጠችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፀሐይ ገመቹ የ2ኛ ደረጃን አግኝታለች።

አውስትራሊያ በተኪያኼደ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ደግሞ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በቀለች ጉደታ 1:08.05 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። በወንዶች ፉክክር 1:05.51 በመሮጥ ኢትዮጵያዊው አትሌት ኪሮስ አሸናፊ የ2ኛ ደረጃን አግኝቷል።

በ39ኛው ሜክሲኮ ማራቶንም ትናንት ኢትዮጵያውያኑ ድል ተቀዳጅተዋል። በሴቶች ፉክክር አትሌት አማኔ በሪሶ 2:25.05 በመሮጥ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር ለ1ኛ ደረጃ ድል በቅታለች። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሙሉዬ ደቀቦ፣ 2:31.07 በመሮጥ የ3ኛ ደረጃን አግኝታለች። ኬኒያዊቷ የማራቶን ሯጭ ሲንቲያ ቼፕቺሪር ኮስጌይ የ2ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በሜክሲኮ ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኬኒያዊው አትሌት ኤድዊን ኪፕሮፕ ኪፖቶ የሀገሩን ልጆች ኬኔዝ ኪፕላጋት ሊሞ እና ሮህንዛስ ሎኪታም ኪሊሞን አስከትሎ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን በመቆጣጠር ለድል በቅቷል።

Fußball FC Bayern | Symbolbild
ምስል Christof Stache/AFP/Getty Images

ጀርመን ሊቨርኩሰን ከተማ ውስጥ ትናንት በተካሄደ የ1500 ሜትር ውድድርም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ነፃነት ደስታ 4:07.53 በመሮጥ የ1ኛ ደረጃን ተቀዳጅታለች።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

የቅድመ ምርጫ ሒደቱ እና መክፈቻው ላይ ውዝግብ ቢታይበትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት እና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ትናንት ተከናውኗል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለአፍሪቃ ኤኮኖሚ ኮሚሽን (ECA)አዳርሽ ውስጥ በተከናወነው ምርጫ 138 ሰዎች ድምፅ ሰጥተዋል። የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች እና ማኅበራት በምርጫው ተሳትፈዋል። ለፕሬዚደንትነት በእጩነት ከቀረቡት መካከል የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት አቶ ኢሣያስ ጂራ በ94 ድምፅ በድጋሚ ተመርጠዋል። ተፎካካሪያቸው አቶ መላኩ ፈንታ 27 ድምፅ እንዲሁም አቶ ቶኪቻ ዓለማየሁ 17 ድምፅ ማግኘታቸውም ተዘግቧል። የፓሪስ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህን ምርጫውን አዲስ አበባ በአዳራሹ ተገኝታ ተከታትላለች። 

ወደ ደቡብ አፍሪቃ በማቅናት ለማሜሎዲ ሰንዳውንስ የሚጫወተው ኢትዮጵያዊው የእግር ኳስ አጥቂ አቡበከር ናስር ግብ በማስቆጠር ብቃቱን እያስመሰከረ ነው።  ማሜሎዲ ሳንዶውንስ ትናንት ከሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ጋር በነበረው ግጥሚያ 68ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አቡበከር 2ኛዋን ግብ ያስቆጠረው በ90ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የመጀመሪያዋ ግብ 80ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው በማርሴሎ አሌንዴ ነው። እስካሁን አቡበከር ለማሜሎዲ ሰንዳውንስ ተቀይሮ እየገባ 2 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

ፕሬሚየር ሊግ

Liverpool - Manchester City
ምስል Frank Augstein/AP Photo/picture alliance

ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ታሪክ ከፍተኛ ግብ በማስቆጠር የተመዘገበ ክብረወሰን ተካፋይ ኾኗል።  ሊቨርፑል ክብረወሰን ያስመዘገበው ቅዳሜ ዕለት ቦርመስን 9 ለ0 በመረምረም ነው። ከዚህ ቀደም ማንቸስተር ዪናይትድ ሁለቴ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ አንዴ በተመሳሳይ የ9 ለ0 ከፍተኛ የግብ ክፍያ አሸንፈዋል። ቅዳሜ እለት በነበረው ግጥሚያ ሊቨርፑል ቦርመስን በበርካታ ግቦች አሸንፎ ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ማለት ችሏል። ቦርመስ በ3 ነጠቡ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ገብቷል።

የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ ድክመት ያሳየው ቡድናቸው እንደ ቅዳሜ ዕለቱ ንቁ ኾኖ መጫወት እንዳለበት አሳስበዋል። የቦርመሱ ድልንም «ያልተለመደ» ብለውታል። ተጋጣሚያቸውን በሰፊ ግብ ለማዋረድ ሳይሆን ኳስን በሚገባ ተጫውቶ አስፈላጊውን ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውንም አክለዋል። ረቡዕ ማታ ከኒውካስል ጋር ለሚኖራቸው ግጥሚያ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጠዋል። ኒውካስል ዩናይትድ ትናንት ከዎልቨርሐምፕተን ዎንደረረስ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ትናንት በነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች ዌስትሀም ዩናይትድ አስቶን ቪላን 1 ለ0 አሸንፏል። ቶትንሀም ሆትስፐርን ሲያስጨንቁ የነበሩት ኖቲንግሀም ፎረስቶች የማታ ማታ በተከላካይ ጥፋት ለ2 ለ0 ሽንፈት ተዳርገዋል። በአጠቃላይ የትናንቱ ጨዋታ ግን ኖቲንግሀም ፎረስት የአንቶኒዮ ኮንቴ ቶትንሀም ሆትስስፐርን እጅግ በልጦ ታይቷል።

Fußball - Premier League - Liverpool vs Burnley
ምስል imago images/Colorsport

አርሰናል አራተኛ ጨዋታውንም ቅዳሜ እለት ማሸነፍ ችሏል። የቀድሞ የመድፈኞቹ ኮከብ ግብ ጠባቂ ቤርንድ ሌኖ ላይ 2 ግቦች ያስቆጠሩት አርሰናሎች 1 ግብም አስተናግደዋል። ከአንቶኒዮ ኮንቴ ጋር በነበራቸው እንካ ሰላንቲያ ቀይ ካርድ ያዩት አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል በሌሉበት ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፏል። ሁለቱን ግቦች ለቸልሲ ያስቆጠረው ራሂም ስተርሊንግ ነው። ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን 4 ለ2 ማሸነፍ ችሏል። በድል ጎዳና የሚገሰግሰው አርሰናል ፉልሀምን 2 ለ1 በማሸነፍ በፕሬሚየር ሊጉ እስካሁን የተደረጉ አራት ግጥሚያዎችን በድል አጠናቋል። ረቡዕ ዕለት አስቶን ቪላን በሜዳው ኤሚሬት ስታዲየም ያስተናግዳል። ማንቸስተር ዩናይትድ ሳውዝሀምፕተንን እንዲሁም ብራይተን ሊድስ ዩናይትድን 1 ለ0 አሸንፈዋል። ኤቨርተን ከብሬንትፎርድ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።

ቡንደስሊጋ፦

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዑኒዬን ቤርሊን ከፍተኛ ግብ በተመዘገበበት ጨዋታ ቅዳሜ ዕለት ሻልከን በሜዳው 6 ለ1 አሸንፏል። ትናንት በነበሩ ሁለት ግጥሚያዎች ኮሎን እና ሽቱትጋርት ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ፍራንክፉርት ቬርደር ብሬመንን 4 ለ3 አሸንፏል። ባየርን ሙይንሽን ከትናንት በስትያ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን በሜዳው አስተናግዶ አንድ እኩል ወጥቷል። ባየርን ሙይንሽንን ከሽንፈት የታደገችው ግብ 83ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው በሌሮይ ሳኔ ነው። ለሞይንሽንግላድባኅ ማርኩስ ቱርማን 43ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሔርታ ቤርሊንን፤ ሆፈንሀይም አውግስቡርግን እንዲሁም ፍራይቡርግ ቦሁምን 1 ለ0 አሸንፈዋል። ላይፕትሲሽ ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 ሲሸኝ፤ ማይንትስ በሜዳው በባየርን ሌቨርኩሰን የ3 ለ0 ሽንፈትን አስተናግዷል።

Bundesliga  | SV Werder Bremen v Eintracht Frankfurt
ምስል Cathrin Mueller/Getty Images

ላሊጋ፦

በስፔን ላሊጋ ግጥሚያዎች ባርሳ ትናንት ዘና ብሎ ሲያሸንፍ የማታ ማታ ለድል የበቃው ሪያል ማድሪድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል። የባየርን ሙይንሽን ኮከብ ግብ አግቢ የነበረው ፖላንዳዊው አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ባርሴሎና ውስጥም የግብ አዳኝነቱን ቀጥሏል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በላሊጋው ሦስት ግጥሚያዎች አራት ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ትናንት ከሪያል ቫላዶሊድ ጋር በነበረው ጨዋታ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ለሁለተኛ ጊዜ በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ባርሴሎናን ለድል አብቅቷል። ፔድሪ እና መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው 2 ደቂቃ ላይ ሠርጂዮ ሮቤርቶም አስቆጥረው ባርሴሎናን ለ4 ለ0 ድል አብቅተዋል። 

በሌላ የላሊጋው ግጥሚያ በቪንሺየስ ጁኒዮር 12ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረች ግብ ሲመራ የቆየው ሪያል ማድሪድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል። ከእረፍት በፊት የኤስፓኞሉ ጆሴሉ 43ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ቡድኑን አቻ በማስውጣቱ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ ሪያል ነጥብ የመጣል ስጋት ውጦት ነበር። የማታ ማታ 88ኛው ደቂቃ ላይ እና በጭማሪው 10ኛ ደቂቃ ላይ ካሪም ቤንዜማ አከታትሎ ባስቆጠራቸው ግቦች ግን ሪያል ማድሪድ ኤስፓኞላን 3 ለ1 ማሸነፍ ችሏል።

ምስል Kirsty Wigglesworth/AP Photo/picture alliance

የሜዳ ቴኒስ፦

በሜዳ ቴኒስ ፉክክር ለ23 ጊዜያት የዓለማችን ኮከብ ኾና ዋንጫዎችን የሰበሰበችው ሴሬና ዊሊያምስ አርተር አሸ ስታዲየም ውስጥ ዛሬ ስንብት ታደርጋለች። በስንብት ግጥሚያዋም ከሞንቴኔግሮዋው ዳንካ ኮቪኒች ጋር ትጋጠማለች።  ሴሬና ዊሊያምስ ከሜዳ ቴኒስ ውድድር እንደምትሰናበት ይፋ ያደረገችው ከሦስት ሳምንታት በፊት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ