1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻዱ ፕሬዚዳንት ተገደሉ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2013

ለስድስተኛ መንበረ ስልጣን ዳግም የተመረጡት የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ አማጺያንን የሚወጉ ወታደሮቻቸውን በጦር ግንባር በመጎብኘት ላይ ሳሉ ተገደሉ። የፕሬዚዳንቱን ሞት ተከትሎ የቻድ መንግሥትና ፓርላማ የተበትኖአል። በሟቹ ፕሬዚዳንት የሚመራ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ቻድን ለቀጣይ 18 ወራት ያስተዳድራል ተብሎአል።

https://p.dw.com/p/3sIBH
Tschad N'Djamena 2020 | Präsident Idriss Deby Itno
ምስል Blaise Dariustone/DW

ለስድስተኛ መንበረ ስልጣን ዳግም የተመረጡት የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ አማጺያንን የሚወጉ ወታደሮቻቸውን በጦር ግንባር በመጎብኘት ላይ ሳሉ ተገደሉ። የ68 ዓመቱ የቻድ ፕሬዚዳንት በሳምንቱ መጠናቀቅያ ወታደሮቻቸዉን በጦር ሜዳ እየጎበኙ ሳሉ በተተኮሰባቸዉ ጥይት ቆስለዉ በደረሰባቸዉ ጉዳት ሕይወታቸዉ ማለፉም ተዘግቦአል። የማዕከላዊ አፍሪቃዊትዋ ሃገር ቻድን ከ 30 ዓመታት በላይ ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ኤድሪስ ዴቢ ለስድስተኛ ዘመነ ስልጣን ዳግም መመረጣቸዉ የተሰማዉ ትናንት ሰኞ ነበር። ቻድ መዲና ኒንጃሚና የሚገኘዉ የሃገሪቱ የምርጫ ቦርድ የ 68 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ኤድሪስ ዴቢ 79 በመቶ ድምፅን በማግኘት በአብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል ሲል አዉጆ ነበር። በ 1990 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት የቻድን መንበረ ስልጣን ተቆጣጥረዉ የነበሩት እና ሃገሪቱን በጠንካራ ክንዳቸዉ ያስተዳደሩት ሟቹ ፕሬዚዳንት ዴቢ፤ በቻድ  ባለፈዉ ሚያዝያ ሦስት ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የምርጫዉ አሸናፊ እንደሆኑ በእርገጠኝነት ሲነገሩ እንደነበርም ተዘግቦአል። እንድያም ሆኖ በምርጫዉ ወቅት በርካታ የፕሬዚዳንት ዴቢ ተቀናቃኝ እጩዎች በመታየታቸዉ ዴቢ ጥርጣሪ ዉስጥ ገብተዉ ነበር።  የዴቢ መንግሥት በቻድ ተቃዋሚዎች ለዓመታት ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደረጉ በመከልከሉም ይታወቃል። የፕሬዝዳንት ዴቢን ሞት ተከትሎ የቻድ መንግሥትና ፓርላማ የተበተነ ሲሆን በሟቹ ፕሬዚዳንት ልጅ ማሐማት ኢድሪስ ዴቢ የሚመራ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት አገሪቱን ለቀጣይ 18 ወራት እንደሚያስተዳድር ተነግሯል።

 

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ