1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ፕሮጀክቶችና የአውሮጳ ህብረት የንግድ ትብብር

ረቡዕ፣ ነሐሴ 6 2012

ቻይና በአፍሪቃ በተለይም በኢትዮጵያ ካከናወነቻቸው በርካታ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ የ “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ" ኢኒሼቲሽ መርሃግብሯ አካል የሆነው ቀላል የከተማ ባቡር መስመር ግንባታ ተጠቃሽ ነው::

https://p.dw.com/p/3grCg
China  Xi'an Frachtzug Neue Seidenstraße
ምስል picture-alliance/dpa/Imaginechina/L. Qiang

በሞባይል ስልክ ግብይት በኢትዮጵያ 


ቻይና በአፍሪቃ በተለይም በኢትዮጵያ ካከናወነቻቸው በርካታ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ የ “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ" ኢኒሼቲሽ መርሃግብሯ አካል የሆነው ቀላል የከተማ ባቡር መስመር ግንባታ ተጠቃሽ ነው:: በዋና መዲናይቱ አዲስ አበባ ከ 33 ሚልዮን ዶላር በሚልቅ ወጪ በ 13 ወራት ውስጥ የግንባታ ስራው ተጠናቆ አምና አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሲልክ ሮድ ጠቅላላ ሆስፒታልም የዚሁ ዕቅድ ሌላው አካል ሆኖ ይጠቀሳል:: በኢትዮጲያ ከሚገኙት አያሌ የቻይና ድርጅቶች መካከል በጤናው ዘርፍ የተሰማራው ኦፊ ሆልዲንግ ካምፓኒ የግንባታ ስራውን ያከናወነው ይህ ግዙፍ ሆስፒታል ዘመናዊ የምርመራ መሳሪያዎች የተሟሉለት እና 11 ወለሎች ያሉት ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ሆስፒታሉ በተለይም ለተሻለ ሀክምና እርዳታ ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረጉ ጉዞዎችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሪን ከማዳኑም በላይ በህክምናው ዘርፍ የዕውቀት ሽግግርን ለማሳለጥም እንደሚረዳ የታመነበት ነው:: ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ማብቂያ በዓለም የኮረና በሽታ ከተስፋፋ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንኑ የቻይናው ሲልክ ሮድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑ የሚታወስ ነው:: የዶይቼ ቨለ የቤጂንግ ወኪል አክስል ዶርሎፍ "ኢትዮጵያ ለቻይናው የሲልክ ሮድ ዕቅድ ያላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን" ፤መነሻ አድርጎ በቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ የተነደፈውን የሲልክ ሮድ ዕቅድና የአውሮጳውያኑን የንግድ ማህበረሰብ አባላትና የቻይና የንግድ ትብብር እንቅስቃሴ በተመለከተ ለጀርመንኛው ፕሮግራም ክፍል ያጠናቀረውን ዘገባ ይሆናል በዛሬው ዝግጅታችን ተርጉመን የምናቀርበው::
ቻይና ከፍተኛ የገንዘብ በጀት በመመደብ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ገቢራዊ በማድረግ በዓለም ዙሪያ የባህር ወደቦችን ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎችን፣ መንገዶችን፣ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን እና የቴሌኮሙኒኬሽን አውታረ መረቦችን በመገንባት ከበርካታ ሀገራት ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሯን ከማጠናከሯም በላይ የቤጂንግን ዓለማቀፍ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ላለፉት ዓመታ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ችላለች::በቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ሃሳብ አመንጪነት እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2013 ዓ.ም ገቢራዊ የሆነው የ “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ” ኢኒሼቲቭ በቻይና እና ወዳጅ ሀገራት መካከል የሁለትዮሽ የምጣኔ ሀብት እና የኢንቨስትመንት ትስስርን ለማጠናከር የተጀመረ መሆኑ ይጠቀስ እንጂ፤ ዋና ዓላማው ከዚህም የላቀ መሆኑ ነው የሚነገረው:: ይኸውም የአውሮጳ ፣ የእስያና የአፍሪቃ ሀገራትን ከግጭት ነፃ በሆነ ታላቅ የኢኮኖሚ ትብብር በቀደመው የሲልክ ሮድ ትግበራ በመደገፍ ማስተባበር ሲሆን ፤ ከ 70 የሚልቁ ሀገራትን ያስተሳሰረው ሲልክ ሮድ የህዝብ ለህዝብ ልውውጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና ተሳታፊ ሀገራት ጥቅምን እንዲጋሩ በማድረግ እሳቤ ላይ ተመስርቶ ወደ ተቀሩት የዓለም ሀገራትም ለማስፋፋት ቻይና በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴዋን ማጠናከሯ ታውቋል ፡፡
በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የቻይና አውሮጳ ህብረት የኢንቨስትመንትና የንግድ ትብብር ስምምነት ቻይና የውጭውን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከወሰደችው የማሻሻያ መርሃግብር በኋላ ከፍ እያለ መምታቱን ልዩ ልዩ ጥናቶች ይገልጻሉ:: የአውሮጳ ህብረትን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ኩባንያዎች ለቻይና የዕድገት ታሪክ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ሲሉ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ማመስገናቸውንም ግሎባል ታይምስ ዘግቧል:: ባለፉት 20 ዓመታት በቻይና የተደረገው ይኸው የኢኮኖሚ እና የታክስ ማሻሻያ መርሃግብር በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች በተለይም አውሮጳ ህብረት ፤ በተለያዩ የንግድ የልማትና እና የኢንቨስትመንት ዘርፎች በአገሪቱ በቀጥታ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አድርጓቸዋል:: የውጭ ኢንቨስተሮችን የግብር ጫና ለመቀነስም የተጨማሪ እሴት ታክስ ቀጥተኛ ያልሆነ ግብርን ወደ ተገልጋዮች ወይም ዋና የመጨረሻ ተጠቃሚዎች የሚተላለፍበት የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል::
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እስካሁን ከግዙፉ የቻይናው ሲልክ ሮድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት የተገኙት ውጤቶች ትኩረት የሚስቡ ናቸው የሚለው የዶይቼ ቨለ የፔኪንግ ወኪል ዶርሎፍ ያም ቢሆን ዛሬም ድረስ መላ ያልተገኘለት ዓለማቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ ለፕሮጀክቱ ቀጣይ የስራ እንቅስቃሴ እጅግ ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን በዘገባው አመልክቷል:: ዶርሎፍ ጥቂት ወራት መለስ ብሎ የነበረውን ሁነትም ያስታውሳል:: ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማዕከላዊ ቻይና ሁቤ ክፍለሃገር ዉሃን ከተማ ከተቀሰቀሰ በኋላ በያዝነው የአውሮጳውያኑ ዓመት ሚያዝያ 14,2020 ዓ.ም የመጀመሪያው የቻይና-አውሮጳ የካርጎ የጭነት ባቡር 35 ኮንቴይነር የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን፣ የእጅ ጓንቶችን እንዲሁም ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ የኮረና ቫይረስ መከላከያ አልባሳትን በእርዳታ ለመለገስ በምዕራባዊቷ የጀርመን ግዛት በምትገኘው የዱይስቡርግ ከተማ ባቡር ጣቢያ አዲስ በተዘረጋው መስመር ደረሰ:: ቻይና ይህ ዓይነቱ የህክምና ቁሳቁሶች ልገሳ ያደረገችው ከ 12 ሚልዮን የሚልቁ የዉሃን ከተማ ነዋሪዎች በኮቪድ-19 ቫይረስ መጠቃታቸው በሚነገርበት ወቅት ነበር:: የአውሮጳ ሀገራት በኮረና ወረርሽኝ ክፉኛ በተጠቁበት እና አንዱ ሃገር ለሌላው የህክምና ቁሳቁስ የመርዳት አቅም ባጠረበት በዛ የጭንቅ ሰዓት ቤጂንግ ለሀገራቱ በተለይም ለጣሊያ ያደረገችው ይህ ፈጣን የህክምና መርጃ ቁሳቁሶች ልገሳ "ቻይና በዉሃን ግዛት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ በሽታው ተላላፊ መሆኑን ፈጥና አላሳወቀችም" በሚል ይሰነዘርባት የነበረውን ነቀፌታ ጋብ አድርገው ከቻይና ጋር የመሰረቱትን የቆየ የኢንቨስትመንት ትብብር ዳግም እንዲያጤኑት ይህ ሁነት አስገድዷቸዋል::
"የቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዛሬ ዓለምን እየፈተነ በሚገኘው የኮረና ወረርሽኝ ቀውስ ስጋት ወቅት የሲልክ ሮድ ፈንድ እያከናወናቸው የሚገኙትን ልዩ ልዩ አመርቂ ተግባራት የሚገልፁ ዘገባዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙ ግሎባል ታይምስ "የሕይወት መንገድ እና አማራጮች" በሚል ዓብይ ርዕስ ባወጣው አንድ ዘገባው ጠቅሷል:: በቻይናው ፕሬዝዳት ዢ  ጂፒንግ ገቢራዊ የሆነው አዲሱ የሲልክ ሮድ መርሃግብር ቻይና ከእስያ አፍሪቃ እና የአውሮጳ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ትብብር ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማጠናከር እና ለማስተሳሰር ያለመ ነው:: ከዓላማዎቹም መካከል የቻይና ኩባንያዎች በእነዚሁ ሀገራት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማድረግ ብሎም የንግድ የምጣኔ ሃብት የኢንቨስትመንት እና የመሰረተ ልማት መርሃግብሮችን ማስፋፋት በተጨማሪም የሀገራቱን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ  ይጠቀሳሉ:: ይኸው የቻይና የብድር ፣ የኢንቨስትመንት፣  የንግድ እና የመሠረተ ልማት ትስስር መርሐ ግብር ደግሞ በሌሎች ሀገራት የባህር ወደቦችን የባቡር መስመሮችን የመሰረተ ልማቶችን እና የኢንዱስትሪ ማስፋፊያዎችን ለማከናወን እንዲረዳቸው እንደ ሲልክ ሮድ ፈንድ ያሉ አማራጮችን ለመጠቀም እንዲችሉም የሚረዳ ነው:: ፕሬዝዳንት ዢ ይህን አዲሱ ዕቅዳቸውን ዓለማቀፉ ማህበረስብ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግም የሲልክ ሮድን መርሃ-ግብር ዓላማና ግብ የሚያስተዋውቅ ጉባኤ ለሁለት ጊዜያት በሀገራቸው አዘጋጅተዋል:: ባለፈው ዓመትም በቤጂንጉ ጉባኤ ከ 100 የሚልቁ ሀገራት ተወካዮች ተካፋይ ሆነዋል::ቻይና በተለይም በታዳጊ ሀገራት ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ከመደበችው በጀት ውስጥ በዕርዳታ፣ በወለድ አልባ ብድርና በረዥም ጊዜ አነስተኛ ብድር የሚሰጥ እንደሆነም በእነዚሁ ጉባኤዎች ፕሬዝዳንት ዢ በይፋ ገልፀዋል::
 " በአዲሱ የሲልክ ሮድ መርሃግብር በዓለም ዙሪያ ያለውን የንግድ ልውውጥ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በማድረግ የሁሉም ሀገራት ዕድገትና ብልፅግና ከፍ እንዲል እንፈልጋለን:: ማዕቀፉ ለጋራ ልማት እና ዕድገት ቁልፍ መንገድ ነው::ተጨባጩ ዕውነታ የጋራ የመሠረተ ልማት ትስስር መርሐ ግብር ስምምነቶቹ የሀገራትን ኢኮኖሚና ልማት ማፋጠናቸው ብቻ ሳይሆን ለቻይናም ሆነ ለሀገራቱም ተጨማሪ አማራጭ የስራ ዕድሎችንም የሚያስገኙ ናቸው" ነው ያሉት::
ቻይና የምትከተለው የሚያበረታታ ገቢያ-ተኮር ማሻሻያ መንገድ ፣ አውሮጳውያኑ በቻይና ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ከቻይና ጋር የተቀራረበ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለዓመታት ፈጥሮላቸዋል :: የአውሮፓ ህብረት እና ቻይና እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1975 ዓ.ም በይፋ የንግድ አጋርነት ስምምነት በመፈራረም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ መጀመራቸውም ይታወቃል:: ተጨባጩ ዕውነታ አከራካሪ ቢሆንም ቻይና ግን አዲሱን የሲልክ ሮድ መርሃ-ግብር እንደ ሰጥቶ መቀበል ለሁሉም ወገን የሚበጅ እጅግ ጠቃሚ ነው ስትል ታወድሰዋለች:: 2020 ዓ.ም ለቻይና-አውሮጳ ህብረት ግንኙነት ወሳኝ ዓመት እንደሚሆን ከአሁን ቀደም ቃል የተገባ ቢሆንም የኮረና ወረርሽኝ መስፋፋት በዕቅድ የተያዙ ጉባኤዎች እንዲሰረዙ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውም እንዲቀዛቀዝ ዓብይ ምክንያት ሆኗል:: ምንም እንኳን በቻይና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት በዛው በቻይና እንቅስቃሴ በሚያደርጉ የአውሮጳ ህብረት የተለያዩ ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ ቢያስከትልም ፣ የቻይና ወቅታዊ ምላሽ እና የወሰደቻቸው ፈጣን እርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸው ኩባንያዎቹ በቻይና በሚያከናውኑት ቀጣይ የልማት እንቅስቃሴ ዕምነት እንዳሳደረባቸው በቻይና የአውሮጳ ህብረት የንግድ ምክርቤት ፕሬዝዳንት ዮርግ ቩትከ ገልፀዋል:: የኮረና ወረርሽኝ በቻይና ገበያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድርም በአሁኑ ወቅት በቻይና የተዘረጋውን ዓለማቀፍ የንግድ ሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለት መተካት ቀላል አለመሆኑም ሃላፊው አስረድተዋል:: በዘመናዊ ቴኮኖሎጂ እና ዘርፈ ብዙ በሆነ ዕምቅ ጥበብ እንዲሁም ከፍተኛ ሙያ ባለው የሰው ኃይል የሚመራው የቻይና ገበያ ጠንካራ የሆነ መሰረተ ልማቱን በዓለም ዙሪያ ዘርግቷል:: ይህን በቀላሉ ማየት ትልቅ ስህተት ነው ይላሉ ቩትከ:: "በቻይና ውስጥ አብዛኛዎቹ የአውሮጳ ኩባንያዎች በመጪዎቹ ዓመታትና አስርተ ዓመታት ውስጥ በሰፊው እንደሚያድጉና የአካባቢውን ገበያ እንደሚቆጣስጠሩ እናምናለን:: ገበያው ለካምፓኒዎቹ መኖርና ሕልውና እጅግ ወሳኝ ነው:: ያም ቢሆን የውጭ ኢንቨስተሮችን ለማነቃቃት ከተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ባሻገር በኮቪድ-19 ምክንያት የተዳከመው የግሉ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲያገግም ተጨማሪ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ" ነው ያሉት::
"በቻይና የሚገኙት የአውሮጳ ኩባንያዎች እስከ ጥር ወር ድረስ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነበር:: በሀገሪቱ የኢንሸስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ለተፈቀደላቸው ሰዎችም የንግዱ ሁኔታ ጥሩ ሆኖ ቆይቷል:: እዚህ ላይ ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን አያሌ የአውሮጳ ኩባንያዎችም ወደ ቻይና መጥተው የንግድ እንቅስቃሴ ማከናውን የሚፈልጉ ግን ደግሞ ያልቻሉ መኖራቸውን ነው" :: ባለፉት ዓመታት ቻይና የአውሮጳ ኩባንያዎች በብድርና በሽርክና ገበያዎች በሀገሯ እንዲሰማሩ ፈቅዳለች። የቻይና እና የአውሮጳ ህብረት የንግድ ሽርክና ምን ዓይነት አተያይ አለው ተብለው የተጠየቁት ቩትከ በግላቸው የተደባለቀ ስሜት መኖሩን ነው ያስረዱት ፕሬዝዳንቱ::

China Guiyang Infrastrukturausbau Neue Seidenstraße
ምስል picture-alliance/dpa/Imaginechina/D. Gang
Infografik China's new Silk Road ES
Dokumentation ZDF Die neue Seidenstraße
ምስል ZDF

"ባለፈው ጥር ወር ላይ በቻይና የአውሮጳ ንግድ ምክር ቤት ያቀረበው ጥናት እንዳመለከተው በቻይና የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ዙሪያ የሚሰነዘረው ወቀሳ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው እንጂ አንዳችም ኢኮኖሚያዊ አተያይ ወይም ገፅታ የለውም:: ሁለተኛ ነገር ሁሉም ነገር ቻይና ላይ ያተኮረ ሆኗል:: ይህ ደግሞ ለብዙሃኑ አሳማኝ አይደለም:: በቅድሚያ ቻይና ከእኛ ጋር የሁለትዮሽ የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ስታደርግ አቅም እና ጥንካሬያችንን መሰረት አድርጋ ነው:: ቻይና የውጭ ኢንቨስተሮችን የበለጠ ለመሳብ እና ምጣኔ ሃብቷን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ የማሻሻያ ረቂቅ ተግባራቂ ከማድረጓም በላይ 90 በመቶ ያህሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ በቻይናውያን ኩባንያዎች ስር የሚጠቃለልበትም አሰራር ተዘርግቷል::"
ቻይና ከወሰደችው የታክስ ማሻሻያ ዋና ተጠቃሚዎቹ በሀገሪቱ በግንባታ፣  በብረታብረት ምርት ኢንዱስትሪ እና በትራንስፖርት ዘርፍ ተሰማርተው የመሰረተ-ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶችን የሚያስፋፉ ተቋማት ናቸው:: ለምሳሌ ፓኪስታን ግሪክም ይሁን ሰርቢያ ቻይና አዲሱን የሲልክ ሮድ ፕሮጀክት ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በ 140 ያህል ሀገራት የምታከናውናቸውን የልማት እና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሚያጠቃልል ሲሆን እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ ዋናው ቻይና ከወዳጅ ሀገራት ጋር ለምትመሰርታቸው ሽርክናና ትብብሮች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ዋና አካል ተደርገው ይቆጠራሉ:: ሆኖም በአሁኑ ወቅት በቻይናም ሆነ በመላው ዓለም የኮረና ወረርሽኝ መስፋፋት ለቻይናው አዲሱ የሲልክ ሮድ ኢኮኖሚ ቤልት ኢኒሼቲቭ ወይም ትሥሥር ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል::
የኮቪድ-19 ወረርሽን ከተከሰተበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የወጪና የገቢ ምርቶች ንግድ የዕቅድ አፈጻጸም ከተገመተው በታች ሆኗል:: ሀገራት ለረጅም ጊዜያት ድንበሮቻቸውን ዘግተው ቆይተዋል:: የሎጂስቲክ አገልግሎትና እንቅስቃሴም ተዳክሟል:: አሁንም ቢሆን ሁኔታዎች የተሻሻሉ አይደሉም:: ምንም እንኳን በሁለተኛው ሩብ ዓመት የቻይና ምጣኔ ሃብት ዳግም ማንሰራራት ቢያሳይም ኮቪድ-19 ዛሬም ድረስ መፍትሄ አለማግኘቱ ዓመቱን በሃገሪቱ ለሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ አስከፊ አድርጎታል:: ዋንግ ኢዌ ቤጂንግ በሚገኘው ሬንሚን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ናቸው:: በቻይናው "አዲሱ ሲልክ ሮድ" ዕቅድ ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምር አካሂደዋል:: የኮሮና ቀውስ በዕቅዱ ትግበራ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አስከትሏል ቢሆንም ግን የምጣኔ ሃብቷን እድገት አያስተጓጉለውም ብለዋል::

"የኮረና ወረርሽኝ በሲልክ ሮድ ዕቅድ ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ እና ቀውስ በጣም ሰፊ ነው:: ኢኒሼቲቩ በሀገራቱ መካከል በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትሥሥርን የመሰረተ ቢሆንም አሁን ግን ፈታኝ ችግር ገጥሞታል:: ሰዎች ከቦታ ቦታ በሚደርጉት ዝውውር በቫይረሱ የመጠቃት እድል ስለሚኖራቸው እርስ በእርስ የመተማመን እሴታቸውን ሸርሽሮታል::በርካታ የቻይናውያን ሰራተኞች በጥር ወር ለፀደይ ፌስቲቫል ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ወደ አፍሪቃም ሆነ ወደ አውሮጳ መመለስ አልቻሉም:: ዋናው ትልቁ ችግር ገንዘብ ነው:: ያም ቢሆን ምናልባትም በያዝነው ዓመት ምጣኔ ሃብታቸው ከሚያድግ ሀገራት አንዱና ብቸኛው የቻይና ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል::
ለአውሮጳ ህብረት የሲልክ ሮድ ኢኒሼቲቭ ከኮረና መስፋፋት ቀደም ብሎም ቢሆን አየር ላይ እንደተገነባ ግንብ እምብዛም መሰረቱ የጠነከረ አልነበረም :: በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ የአውሮጳ ህብረት የንግድ ምክርቤት ባካሄደው ጥናት በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ ያመለከቱ የአውሮጳ ኩባንያዎች ቁጥር ከ 15 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቁሟል:: ቻይና ዋና ከምትላቸው የንግድ ሸሪክ ሀገሮች ተጠቃሚ ልትሆንባቸው በምትችልባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገበያዋን የማስፋፋት ዕቅድ አላት የሚሉት በቻይና የአውሮጳ ህብረት ንግድ ምክርቤት ፕሬዝዳንት ቩትከ ይሁን እንጂ በምስራቅ አውሮጳ እንኳ የሚገኙ ኩባንያዎች ጉጉት እና ፍላጎት አሁን ላይ ቀንሶ ታይቷል ሲሉ ነው ያብራሩት::

"በኢኒሼቲቩ የተጣሉት ተስፋዎች አለመተግበራቸው ተሳትፎው እንዳይጎለብት አድርጎታል:: ከ 8 ዓመታት በፊት ቻይና ከ 17 የመካከለኛው እና የምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት ጋር የደረሱበት ስምምነት በሀገራቱ መካከል የኢንቨስትመንት ትብብሩን በእጅጉ ያጠናክረዋል ተብሎ ቢታመንበትም አምና በተካሄደው የክሮሺያው ስብሰባ የታሰበው ውጤት አለማምጣቱ ተገምግሟል:: ምክንያቱም በወቅቱ ቻይና ዓላማዋን በግልፅ ለማስተዋወቅ አለመቻሏ፣ ከአሁን ቀደም በሰጠቻቸው ተስፋዎች ላይ ፀንታ አለመገኘቷና አጓሮቿ የሚፈልጉትን ዋስትና ልታረጋግጥ ባለመቻሏ ፕሮጀክቱ ስኬት ማስገኘት አልቻለም:: ለምሳሌ ጥያቄው የኢንቨስትመንት ትብብር ቢሆንም ነገር ግን ከምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች እንደ ፖም እና ልዩ ልዩ ተጨማሪ የአትክልት ምርቶችን መግዛት የስምምነቱ አካል አልነበረም"

Duisburg | Der «Yuxinou»-Zug kommt in Duisburg an
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

የዶይቼ ቨለ የቤጂንግ ወኪል ዶርሎፍ በዘገባው ማጠቃለያ እንዳለው አዲሱ የቻይና የሲልክ ሮድ ዕቅድ ከተለያዩ ወገኖች "የዕዳ ፖሊሲ ወጥመድ" የሚል ትችት እና ነቀፌታም እየገጠመው ይገኛል :: ቻይና ደሃ ሀገራትን ከማይወጡበት የብድር ወጥመድ ውስጥ እየከተተች ነው የሚለው ወቀሳ በተለዩ ወገኖች ሲስተጋባ የቆየ ነው:: ለልማት ፕሮጀክቶቹ እንቅስቃሴ ማከናወኛ ብድሩን የሚሰጡት የቻይና ባንኮች ሲሆኑ አያሌ ሀገራትም መመለስ ያለባቸውን ዕዳ በጊዜ ለመክፈል ባለመቻላቸው ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል:: አንዳንድ ሀገራትም ይህንኑ ስጋት ከገንዘብ ብድር ይልቅ የጥሬ እቃዎች አቅርቦት እንዲሟላላቸው ፍላጎት እያሳዩ ነው:: ሆኖም ዋናው ስጋት የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቻይና ላይ የፖለቲካ ጥገኛ የመሆኑ አደጋም ጭምር ነው:: ዘ ኢኮኖሚስት በአንድ ዕትሙ እንደ አፍሪቃ ያሉ ደሃ ሀገራት ከቻይና ጋር በተናጠል የሚያደርጉት ድርድር ዞሮ ዞሮ የሚጠቅመው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉልበት ያፈረጠመችውን ቻይና በመሆኑ ሀገራት የድርድር ስሌት እና አካሄዳቸውን በጥልቀት እንዲፈትሹ መክሯል::
 
አክስል ዶርሎፍ / እንዳልካቸው ፈቃደ

 

አዜብ ታደሰ