1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ጦርነት ኤኮኖሚያዊ ምክንያቶች

ረቡዕ፣ ኅዳር 30 2013

በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰው "ጦርነት የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ፤ የተፈጥሮ ሐብቷን እና በየአመቱ ከአበዳሪዎች እና ለጋሾች የምታገኘውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለመቆጣጠር የሚደረግ ነው" በማለት በኦሬጎን ዩኚቨርሲቲ የአፕላይድ ኤኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን መለሠ በአሜሪካኑ ፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት ላይ ጽፈዋል። 

https://p.dw.com/p/3mRBf
Äthiopien Tigray | Hauptstadt Mekele
ምስል MICHAEL TEWELDE/AFP/Getty Images

ከኤኮኖሚው ዓለም፣ ከረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን መለሠ ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት ከኤኮኖሚያዊው ጉዳይ ይልቅ ፖለቲካዊ ልዩነቶች በርትተው የኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት እና ህወሓት የሚመራውን የትግራይ ክልል ወደ ጦርነት ገፍተዋቸዋል። በኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ካሳሁን መለሠ እንደሚሉት ግን፦ ህወሓት የፌድራል መንግሥቱን ሲቆጣጠር በእጁ የነበሩ ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማጣቱ ዋንኛ ገፊ ምክንያት ነው። 

ረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን መለሠ በአሜሪካኑ ፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት ላይ በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰው "ጦርነት የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ፤ የተፈጥሮ ሐብቷን እና በየአመቱ ከአበዳሪዎች እና ለጋሾች የምታገኘውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለመቆጣጠር የሚደረግ ነው" በማለት ጽፈዋል። 
በዚሁ ሐተታ ይኸን ሐብት መቆጣጠር የሚችለው ዐቢይ ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ለሶስት አስርት አመታት ገደማ ህወሓት እንዳደረገው ሁሉ የፌድራል መንግሥቱን የሚመራው ወይም የፌድራል መንግሥቱን የሚቆጣጠር ነው ብለዋል። 

"ባለፉት 27 አመታት የፌድራል መንግሥቱን ሥልጣን በዋንኛነት የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ቢሆንም ህወሓት ትልቅ ተጽዕኖ ነበረው።" የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን መለሠ በዚህም ዋና ዋና የኤኮኖሚ አውታሮችን ተቆጣጥሮ ነበር ሲሉ ይናገራሉ። ለዚህም እንደ መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ፣ እንደ መስፍን ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉ የትግራይ የመልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ተቋማት በገበያው የነበራቸውን ሚና ይጠቅሳሉ። 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. 34 የትግራይ የመልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ድርጅቶች የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ መደረጉን አስታውቋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ድርጅቶቹ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል። 
ከዚህ በተጨማሪ "ቀጥተኛ የውጭ ዕርዳታ የሚቀበለው የፌድራል መንግሥቱ ነው። ለምሳሌ በመለስ ዜናዊ የመጨረሻ ዓመታት ኢትዮጵያ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በአመት በአማካኝ ትቀበል ነበር። ይኸ ደግሞ የመንግሥትን ግማሽ የሚሆን በጀት ነው። ይኸንን መቆጣጠር ማለት ወዴት ኢንቨስት እንደሚደረግ ለምን እንደምትጠቀም የሚወስነው የፌድራል መንግሥቱን የተቆጣጠረ ኃይል ነው።" ሲሉ የኤኮኖሚ ባለሙያው ካሳሁን መለሠ ያብራራሉ። 

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከመያዛቸው በፊትም ሆነ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ብርቱ ችግር ውስጥ ነበር። የመንግሥት ባለሥልጣናት ደጋግመው እንዳሉት በዚህ ምክንያት ምጣኔ ሐብታዊ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ነበር። በዚህ መሠረት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተወሰነ ድርሻ እንዲሸጥ ተወሰነ። የተለያዩ ሕግጋት ማሻሻልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብትን ከገባበት ቅርቃር ሊያወጡ ይችላሉ የተባሉ እርምጃዎች ተግባራዊ ሆኑ። አብዛኞቹ ኢሕአዴግ ከመፍረሱ በፊት ህወሓት ባለበት የተወሰኑ ናቸው። በእርግጥ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ቀይራለች።

እነዚህ ምጣኔ ሐብታዊ ማሻሻያዎች ወይም የብር ለውጡ አሁን ከተቀሰቀሰው ውጊያ ጋር ምን ያገናኘዋል? ህወሓት በኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት የነበረውን የበላይነት ማጣቱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ለተቀሰቀሰው ውጊያ ምን አይነት አስተዋፅዖ አበረከተ? በጉዳዩ ላይ በኦሬጎን ዩኚቨርሲቲ የአፕላይድ ኤኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን መለሠ ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ከረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን መለሠ ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ