1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ ግጭት እና ዘላቂው መፍትሔ

እሑድ፣ የካቲት 1 2018

የፌደራል ኃይሎች ከአወዛጋቢዎቹ ከአላማጣ እና ኮረም እንዲሁም ከሌሎች አጎራባች ከተሞች መውጣታቸው ከተሰማ በኋላ ነዋሪዎች ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ከከተሞቹ መሸሽ መጀመራቸው ሌላው ስጋቱ እንዲጨምር ያደረገ ክስተት ነበር። በትግራይ የድሮን ጥቃቶች በሁለት አካባቢዎች ተፈጸሙ የመባሉ ዜና በሀገር ውስጥም በውጭም ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/58GWc
በትግራይ  የድሮን ጥቃቶች በሁለት አካባቢዎች ተፈጸሙ የመባሉ ዜና በሀገር ውስጥም በውጭም ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።
በትግራይ  የድሮን ጥቃቶች በሁለት አካባቢዎች ተፈጸሙ የመባሉ ዜና በሀገር ውስጥም በውጭም ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል። ምስል፦ Million Haileslassie/DW

የትግራይ ግጭት እና ዘላቂው መፍትሔ

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በትግራይና በአማራ ክልል አወሳኝ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱ ሲዘገብ በትግራይ የዳግም ጦርነት መነሻ እንዳይሆን አስግቶ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ-እና-ከትግራይ የሚካሄዱ በረራዎችን ለቀናት ማቋረጡ ደግሞ ስጋቱን ይበልጥ አባብሶት ቆይቷል። የፌደራል ኃይሎች ከአወዛጋቢዎቹ ከአላማጣ እና ኮረም እንዲሁም ከሌሎች አጎራባች ከተሞች  መውጣታቸው ከተሰማ በኋላም ነዋሪዎች ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ከከተሞቹ መሸሽ መጀመራቸው ሌላው ስጋቱ እንዲጨምር ያደረገ ክስተት ነበር።

ይህን ተከትሎም በትግራይ  የድሮን ጥቃቶች በሁለት አካባቢዎች ተፈጸሙ የመባሉ ዜና በሀገር ውስጥም በውጭም ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል። የአፍሪቃ ኅብረት ፣የተመድና የአውሮጳ ኅብረት ክስተቱ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ችግሩም በውይይት እንዲፈቱ ማሰሳቢያ እስከመስጠት ደርሰዋል።

ከዚያም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የነፈገው፣ የፕሬቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት ፈራሚ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ ችግሩን በንግግር ለመፍታት ፈቃደኛ መሆኑን  አስታወቋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም። ሆኖም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ "ትግራይ አሁን አንጻራዊ ሰላም" እንዳለው፣ሆኖም "ማንኛውም መጠነኛ" ያሉት "ትንኮሳ"  ግን የመንግሥታቸው ሥጋት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የዛሬው እንወያይ  ሰሞኑን በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ፣ መሠረታዊውን ችግር እና ዘላቂ መፍትሔውን ይመለከታል ። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚወያዩ ሦስት እንግዶችን ጋብዘናል ።እነርሱም ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪ ፣ አቶ ሲሳይ አስምሬ በጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህር እና የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁር ፣ አቶ ነጋልኝ መኳንንት የዓለም አቀፍ የግጭትና የዲፕሎማሲ ተመራማሪ፣ አቶ ዳንኤል ብርሃነ ጋዜጠኛ ፣ የፖለቲካ ተንታኝ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናቸው።

ሙሉውን ውይይት ለመከታተል የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

ኂሩት መለሰ