1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተማሪዎች አዲሱን ዓመት በዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ አሳልፈዋል

እሑድ፣ መስከረም 1 2015

እንደዛሬው ያሉ የዘመን መለወጫ በዓላትን ከቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ ጋር ተሰባስቦ ማክበር ከተለመዱ የኢትዮጲዊነት እሴቶች አንዱ ነው ፡፡ ለዕረፍትና ለበዓል ተማሪዎቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው በሸኘው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት ወደ አካባቢያቸው መሄድ ያልቻሉ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግን በቅጥር ግቢው ውስጥ ይገኛሉ፡፡፡

https://p.dw.com/p/4GhLY
Äthiopien I
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የትግራይ ተማሪዎች አዲሱን ዓመት እንዴት ይሆን የተቀበሉት?

እንደዛሬው ያሉ የዘመን መለወጫ በዓላትን ከቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ ጋር ተሰባስቦ ማክበር ከተለመዱ የኢትዮጲዊነት እሴቶች አንዱ ነው ፡፡

ለዕረፍትና ለበዓል ተማሪዎቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው በሸኘው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት ወደ አካባቢያቸው መሄድ ያልቻሉ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎች ግን  በቅጥር ግቢው ውስጥ ይገኛሉ፡፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በሎጅስቲክ እና ሳኘላይ ማኔጅመንት የሦስተኛ ዓምት ተማሪ የሆነውና ከትግራይ ራያና አላማጣ የመጣው ግርማይ ንጉሱ አዲሱን የ2015ዓ.ም. የተቀበለው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ በሚገኝ ባዶ የመኝታ ክፍል ውስጥ ነው፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት የተነሳ ከቤተሰቦቹ ከተለያየ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ እንደሆነው የጠቀሰው ግርማይ በተለይ እንደዛሬ አይነት በዓል ሲመጣ የቤተሰብ ናፍቆት እንደሚበረታበት ይናገራል፡፡

Äthiopien I Tigray-Studenten auf dem Campus zum Jahreswechsel
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በበዓል ቀን በርካታ ትዝታዎች አሉኝ የሚለው ግርማይ ‹‹ አባቴ ሚስት ለማግባት በግ እንዴት እንደሚታረድና እንደሚገፈፍ ማወቅ አለብህ ይለኝ ነበር፡፡ በግ በመግፈፍ ከታናሽ ወንድሜ ጋር የምንፎካከረው መቼም አይረሳኝም፡፡ አሁን ላይ ቢያንስ አኔ በሕይወት አለው እነሱ ግን በምን ሁኔታ እንዳሉ አላውቅም፡፡ ይህም ዘወትር አእምሮዬን ይረብሸኛል ›› ሲል ለዶቼ ቬለ DW ገልጿል፡፡

በዚሁ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ከትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የመጣውና የሦስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ የሆነው ሀበን በርሄ ተመሳሳይ ስሜት እንዳለው ይናገራል፡፡ ተማሪ ሀበን እንደሚለው ዩኒቨርስቲው ለእረፍት ሲዘጋ ተማሪዎች ወደ የቤተሰቦቻቸው ቢሄዱም እኔና ሌሎች ጦርነት ካለባቸው አካባቢዎች የመጣን ተማሪዎች እዚሁ ለመቅረት ተገደናል ይላል፡፡

Äthiopien I
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በዩኒቨርቲው መዘጋት ምክንየት የተማሪዎች የምግብ አገልግሎት በመቋረጡ በመጀመሪያ ሳምንታት በችግር ውስጥ እንደነበሩ የሚናገረው ሀበን ‹‹ ያም ሆኖ ዩኒቨርስቲው በክፍሎቹ ገብተን እንድናድር ፈቅዶልናል፡፡ እስከአሁንም አንዳንድ በጎ የሆኑ ሰዎች በሚያደርጉልን ድጋፍ ምግባችንን በከፊልም ቢሆን እያገኘን ነው ›› ብሏል ፡፡

ጦርነቱ ባይኖር የዛሬውን የአዲስ ዓመት በዓል ከቤተሰብ ጋር እናሳልፍ ነበር የሚሉት ግርማይና ሀበን መጪው ዘመን ሰላም የሰፈነት እንዲሆንም የበረታ ምኞት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ