1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ ዳግም ድል፣ የአሜሪካ ክፍፍል

ሰኞ፣ የካቲት 8 2013

ትራምፕ ከቀዝቃዛዉ የዋሽግተን ዓየር፣ ከፖለቲካ ጥልፍልፍ፣ እሰጥ አገባ፣ ዉጣ ዉረዱ ብዙ ርቀዉ ከዚያ ምቹ፣ ዉብ፣ቅንጡ ደሴት፣ ፀጥ፣ ረጋ፣ ለብ-ሞቅ ያለዉን ዓየር እየማጉ በተመሰረተባቸዉ ክስ የሚደረገዉን ክርክር ይከታተላሉ።

https://p.dw.com/p/3pONk
USA Impeachment Trump Senat
ምስል U.S. Senate TV/REUTERS

የትራምፕ ዳግም ድል፣ የአሜሪካ ክፍፍል


የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ ሕዳር በተደረገዉ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ ተሸንፈዉ ከዋይት ሐዉስ ሲሰናበቱ «የሆነ ጊዜ፣በሆነ መንገድ እንመለሳለን።» ብለዉ ነበር።«የሆነ» ያሉት ጊዜና መንገድ መቼና እንዴት እንደሆነ በርግጥ አናዉቅም።በሕዝብ ድምፅ የተሸነፉት ቱጃር ፖለቲከኛ በሕዝብ ሐብት፣ ንብረት፣ ሕይወት፣ ሥርዓት ላይ አደረሱት ተብሎ የተመሠረተባቸዉ ክስ ግን በሴናቶሮች ዉሳኔ ዉድቅ ሆነ።«ተሸንፈዉ አሸነፉ።»የአሜሪካ ትላልቅ ፖለቲከኞቹ ክፍፍልም ቀጠለ።ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።
                         
በአወዛጋቢ ምርጫ ስልጣን ያዙ።ጥር 2017(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) እንዳወዛገቡ፣ ትልቋን፣ የዴሞክራሲ ቀንዲሊቱን ሐገራቸዉን ከዓለም እንደነጠሉ  4 ዓመት መሩ ወይም ኖሩ።ዘንድሮ ከሕዳር እስከ ጥር እንዳወዛገቡ፣ ተቀናቃኞቻቸዉን እንደተሳደቡ፣ የምርጫ ሽንፈትን እንቢኝ እንዳሉ፣ በፍርድ ቤት ችሎት እንዳሟገቱ፣  ከሕዳር-እስከ ጥር ቆዩ።ጥር 6 ደጋፊዎቻቸዉን በምክር ቤት እንደራሴዎች ላይ አሳመፁ።
                                        
«በፅናት እንታገላለን።---በፅናት ካልታገላችሁ ከእንግዲሕ ሐገር አይኖራችሁም።--ይሕንን ምርጫ አሸንፈናል።በከፍተኛ ድምፅ አሸንፈናል።በሐገራችን ርዕሠ-ከተማ መሰብሰብ አለብን።-----ደካማ ከሆናችሁ ሐገራችንን ዳግም መያዝ አትችሉም።»
ደጋፊዎቻቸዉ አመኗቸዉ።ዘመቱም።ሽብር።ካፒቶል ሕንፃ።ጥር 6።የአሜሪካ የዴሞክራሲ ተምሳሌት፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች መቀመጫ፣ የሕግጋት ማርቀቂያ-ማፅደቂያ፣ የመሪ-ሚንስትር ጄኔራሎች  የመሪ አዛዥነት ሥልጣን፣ ሹመት ማረጋገጪዉን ሕንፃ ወረሩ፤ ሰባበሩት፤ መዘበሩት፤አወደሙትም።በሁከቱ አንድ ፖሊስን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገደሉ።
ሰዉዬዉ ግን ግድያ ጥፋቱ ሳይቆረቁራቸዉ፣ ሳይጠየቁም።ከዋይት ሐዉስ በክብር ተሰናበቱ።አሉም «ታላቅ ሥራ ሰርቻለሁ።እመለሳለሁም።» ጥር 20።
«የሠራነዉ ነገር በጭራሽ አይታመንም።እናንተ ባትኖሩ መስራት አልችልም ነበር።ስለዚሕ በቃ አሁን ልሰናበታችሁ።እንወዳችኋለን በሆነ ዓይነት እንመለሳለን።ይሕንን ተዓምር አብሬያቸዉ የሰራኋቸዉን የዋሽግተን ዲሲ ታላላቅ ሰዎችን በሙሉ ላመሰግን እወዳለሁ።መልካም ኑሮ።በቅርቡ እናያችኋለን።»
አምና ይሔኔ፣ የዘንድሮዉን ፕሬዝደንት ለማሳጣት ሕግ አልፈዉ የዩክሬን መሪን በማስፈራራታቸዉ ተከሰዉ ነበር።አሸነፉ።ዘንድሮ የተከሰሱት ጥር 6 ዋሽግተንን ያሸበረዉን ጥቃት አነሳስተዋል በሚል ነበር። 
አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በቀድሞ ተፎካካሪያቸዉ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተመሰረተዉን የክስ (Impeachment) ሒደትና የምክር ቤት እንደራሴዎችን ሙግት መከታተል አለመከታተላቸዉን ሲጠየቁ «አልከታተልም» አሉ።ባጭሩ።ለአሜሪካ ሕዝብ «ብዙ የምስራዉ ስላለ» ከሚል ምክንያት ጋር።
የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፖሊሲ ግን ከጥር 6 ጀምሮ ክሱን ከመቀመር፣በምክር ቤታቸዉ ከማስፀደቅ፣ ለሕግ መወሰኛዉ ምክር ቤት (ሴኔት) ከማቅረብ እና ሙግቱን ሰዓት በሰዓት ከመከታተል፣የቦዘኑበት፣ ሒደቱን ከመተንተን በተከሳሽ ላይ እንዲፈረድ ከመጣጣር የቀደመ ሥራና ፍላጎት አልነበራቸዉም።
ሴትዮዋ በቁመት-ክብደት ግዝፈት እሳቸዉን የሚያጥፉትን እኒያን በሐብት ጉልበት የሚታበዩ፣ እብሪተኛ፣ ላፋቸዉ ለከት፣ ለጥፉ ምግባራቸዉ ፀፀት ቢሱን ቀኝ ፅንፈኛ፣ ቱጃር ፖለቲከኛን አሜሪካ ሕዝብ ፊት ማንበርከክ ሳይመኙ ሳይሹ አይቀሩም።

Weltspiegel 12.02.2021 | USA Washington | Impeachment | Nancy Pelosi
ምስል Erin Scott/REUTERS
USA Ohio US-Präsident Donald Trump
ምስል Reuters/J. Ernst

ፔሎሱ የሚመሩትን ምክር ቤት ወክለዉ ሴኔቱ ዉስጥ የተሟገቱት እንደራሴ ጄሚ ራስኪን የዴሞክራቲክ እንደራሴ፣ ሴናተሮችና ፖለቲከኞች ጥረት፣ልፋት፣ ፍላጎት ዴሞክራሲን፣ ሕገ-መንግስትንና ፍትሕን ማስከበር ነዉ እያሉ ተሟገቱ።«ትራምፕ በቀሰቀሱት መንጋ፣ ምክር ቤታችንን አስወረሩ።እኛ ምክር ቤታችንን ከጥቃት ተከላከልን።ትራምፕ ሕገ መንግስታትችንን ጣሱ፣ ተከላከልን።እነሱ ዴሞክራሲያችንን ለማርከስ ሞከሩ እኛ እንዲያንሰራራ አደረግን፣ከዉድቀት አነሳነዉም።»
ከትራምፕ ጠበቆች አንዱ ግን እዉነቱ ተቃራኒዉ ነዉ ይላሉ።ዴሞክራቶችን ያወግዛሉ።
«እሳቸዉ ሥልጣን ለቅቀዉ ተራ ዜጋ በሆኑበት በዚሕ ወቅት የፌዝ ክስ መሠረቱ።ይሕ በጥድፊያ የተቀነባበረና በሕገ-መንግሥቱ ላይ ያልተመሰረተ ቧልት፣ የዴሞክራቶቹ የምክር ቤት እንዴራሴዎች (ትራምፕን ለመጉዳት) ላለፉት 5 ዓመታት ያልተሳካላቸዉን ምኞችት ለማሳካት ያደረጉት የመጨረሻ መፍጨርጨር ነዉ።»
ዋሽግተን ይቀዘቅዛል።ሰሞኑን ደግሞ በበረዶ ተሸፍኗል።ማር-ኤ-ላጎ፣ ፓልም ቢች-ፍሎሪዳ ግን ያዉ እንደ ወትሮዉ አይሞቅም-አይቀዘቅዝምም።ዶናልድ ትራምፕ እዚያ ናቸዉ።ማር ኤ ላጎ።ከሰላሳ ስድት ዓመታት በፊት በ10 ሚሊዮን ዶላር የገዙት ልዩ የመዝናኛ ቦታ ዘንድሮ ወደ 2 መቶ ሚሊዮን ዶላር ይገመታል።

USA Impeachment Trump Senat | Michael van der Veen
ምስል U.S. Senate TV/REUTERS
Amtsenthebungsverfahren gegen Trump - Jamie Raskin
ምስል U.S. Senate TV via REUTERS

ትራምፕ ከቀዝቃዛዉ የዋሽግተን ዓየር፣ ከፖለቲካ ጥልፍልፍ፣ እሰጥ አገባ፣ ዉጣ ዉረዱ ብዙ ርቀዉ ከዚያ ምቹ፣ ዉብ፣ቅንጡ ደሴት፣ ፀጥ፣ ረጋ፣ ለብ-ሞቅ ያለዉን ዓየር እየማጉ በተመሰረተባቸዉ ክስ የሚደረገዉን ክርክር ይከታተላሉ።

ጠበቃ፣ የሕግ አዋቂዎችን፣ ዴሞክራቲክ-ሪፐብሊካን እንደራሴዎችን ከካፒቶል ካዳራሽ፣ አሜሪካኖችን በየሥፍራዉ 5 ቀን ያከራከረዉ ሙግት ትናት አበቃ።ችሎቱን የመሩት ዳኞች ፕሬዝደንት ፔትሪክ ሌይ 
                                    
«ለክሱ የድጋፍ ድምፅ የሰጡ 57፣ የተቃወሙ 43።እዚሕ ከተገኙት ሴናተሮች ሁለት ሶስተኛዉ ጥፋተኛ ነዉ የሚል ድምፅ አልሰጡም።የሴኔቱ ዳኞች፣ ተከሳሹ፣ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ በተመሠረተባቸዉ ክስ ጥፋተኛ አለመሆናቸዉን አረጋግጠዋል።»

ብይኑ፣ ለናንሲ ፔሎሲ በርግጥ አናዳጅ ነበር።
«እነዚሕ ፈሪ ሴናቶሮች ፕሬዝደንቱ ያደረሱትን ጥፋት ማየት አልቻሉም።(ዉሳኔዉ) እንግዲሕ ለሐገራችን የሚያስከትለዉ ነገር ትልቅ ቅጣት የሚገባዉን ጥፋት አገም ጠቀም አድርጎ ማለፍ ነዉ።የፅሕፈት መሳሪያዎችን አላግባብ የሸጡትን እንመረምራለን።ርዕሠ-ከተማችን ዉስጥ ሕይወት ያጠፋ ሁከት የቀሰቀሱ ሰዎችን ግን አንቆጣጠርም።»

ለ45ኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ግን ዳግም ታላቅ ድል።«ትክክለኛዉ አርበኝነት አሁን ተጀመረ» አሉም-ካሉበት።በ1868 የዴሞክራቲኩ ፕሬዝደንት አንድሪዉ ጆንሰን ተከሰዉ ጥፋተኛ ከመባል በአንድ ድምፅ ልዩነት አምልጠዋል።በ1974 የሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ሳይከሰሱ ሥልጣን ለቀዋል።በ1998 የዴሞክራቶቹ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ተከሰዉ 55-ለ45 በሆነ ድምፅ ነፃ ወጥተዋል።
የሪፐብሊካን ፓርቲን የሚወክሉት ዶናልድ ትራምፕ በመከሰስ ሶስተኛዉ ፕሬዝደንት ናቸዉ።ሁለቴ በመከሰስ፣ ከስልጣን ከተሰናበቱ በኋላ በመከሰስም የመጀመሪያዉ ናቸዉ።
ያሁኑ ክስ  ዉድቅ እንዲሆን ድምፅ የሰጡት 43ቱም ሴናቶሮች ትራምፕ ይመሩት የነበረዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴዎች ናቸዉ።ሰባት የሪፐብሊካን ሴናተሮች ግን የድሮ አለቃቸዉ እንዲወነጀሉ ድምፅ ሰጥተዋል።ትራምፕ እንዲወነጀሉ ድምፅ ከሰጡት 57 ሴናተሮች፣ 50ዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮች ናቸዉ።
ይሕ የድምፅ እና የአቋም ልዩነት ትራምፕ ስልጣን ለቅቀዉም ዲሞክራቶችን-ከሪፐብሊካን፣ ሪፐብሊካንን-ከሪፐብሊካኖች እንደከፋፈሉ መቀጠላቸዉን አመልክቷል።ቢፈረድባቸዉ ኖሮ በርግጥ የሚለቁት ሥልጣን የለም።ይሁንና ዳግም የመመረጥም ሆነ የመንግስት ሥልጣን የመሾም መብታቸዉ ይገፈፍ ነበር።አሁን ግን አንዱም መብታቸዉ አልተነካም።ጥር 20 እንዳሉት ዋይት ሐዉስ ይመለሱ ይሆን?

USA Trump Impeachment I Patrick Leahy
ምስል U.S. Senate Television/AP Photo/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ