1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ ዛቻና ኢትዮጵያ

ሰኞ፣ ጥቅምት 16 2013

ከ1993 ጀምሮ ያጣችዉን የአሜሪካንን ወዳጅነት ዘንድሮ ከእስራኤል ጋር መታረቅን «ምርቃት» ጨምራ በ335 ሚሊዮን ዶላርና ገዛች።ከዘለቀ በርግጥ ደግ እንጂ ክፋት የለዉም። ሱዳን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ለወዳጅነቷ ፍጥምጥም የአሜሪካዉ መሪ ኢትዮጵያን «ጭዳ» ለማድረግ መቃጣታቸዉ እንጂ ለከት ያጣዉ እብሪታቸዉ።

https://p.dw.com/p/3kSsX
USA Washington | Treffen Fitsum Arega, Botschafter Äthiopien & Präsident Donald Trump
ምስል Fitsum Arega - Ethiopian ambassador to the United States

የሕዳሴ ግድብ፣ የትራምፕ ዛቻና ኢትዮጵያ


የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አምና ይኸን ጊዜ፣ «እኔ በለፋሁት የኢትዮጵያ መሪ ኖበል ተሸለሙ» ዓይነት ብለዉ ነበር።እርግጥ ነዉ ሰዉዬዉ የሚሉ የሚያደርጉት ለብዙዎች ግራ ግን ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን የፌስቡክ አርበኞችን ጨምሮ ለግራ አጋቢ መርሐቸዉ ብዙዎች ጥብቅና የሚቆሙላቸዉ ቱጃር ነጋዴ፤ ፖለቲከኛም ናቸዉ።ብሒል-ምግባራቸዉ ምናልባት ከ10 ቀን በኋላ በነበር የሚዘከር ይሆን ይሆናል፤ ዝክሩም ሆነ-ብሒሉ አምና ሥለ ኢትዮጵያ ያሉትን «ስሕተት» ብሎ ያለፈና ያስተባበለ ደጋፊ፣አድናቂ አፍቃሪያቸዉ ከነበረ የዘድሮዉን የሚያልፍበት ሰበብ ማግኘቱ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።የአሜሪካኖች መርሕ፣ የትራምፕ ማስጠንቀቂያ፣  የኢትዮጵያዉያን ቁጣና የዲፕሎማሲዉ እድምታ ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።
                                     
የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ላይ ጦርነት በጋመበት በ1998 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) በአዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ከፍተኛ ሹም በተገኙበት ኮክቴል ግብዣ ላይ የመካፈል እድል ነበረኝ።ከጀርባዬ አጀብ ብለዉ ከቆሙት አራት ሰዎች አንዱ የአሜሪካ ኤምባሲ አታሼ፣ ሁለተኛዉ ኢትዮጵያዊ የዚያ ዘመን ባለስልጣን ነበሩ።ከተቀሩት ሁለቱ፣ አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌለኛዉ «ፈረንጅ» ከመሆኑናቸዉ ሌላ በዉል አላወቅኋቸዉም።የብርጭቆ፣ጠርሙሱ ግጭት ቅጭልጭታ፣ የሰዉን ሁከታ እየሰበረ ከጆሮዬ ከሚደርሰዉ ድምፃቸዉ እንደተረዳሁት የአራቱ ሰዎች ዉይይት የኤርትራ ተቃዋሚዎች የዚያን ሰሞን ሱዳን ዉስጥ የጋራ ግንባር ስለመመስረታቸዉ ነበር። 
«የተሰበሰቡት ካርቱም-ሱዳን፣ መሪ አድርገዉ የመረጡት አብደላን----» እንዴት ጥሩ አማራጭ ይሆናሉ---እንዴትስ---?» እየጠየቁ መለሱ፤ የአሜሪካዉ ዲፕሎማት።የአሜሪካ ጠላት የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ የኤርትራ ጠላት የነበረችዉ ሱዳን፣የምታደራጀዉን የኤርትራ ጠላቶች የአሜሪካኖች አለመደገፋቸዉ በርግጥ የአስመሮች ወዳጅ ሊያሳቸዉ አይችልም።አያስደንቅምም።

BG Grand Renaissance Dam | Der äthiopische Premierminister Abiy Ahmed Ali mit dem ägyptischen Präsident Abdel-Fattah al-Sisi (2018)
ምስል Imago Images/Xinhua

ሱዳን ከዚያ ጊዜ አምስት ዓመት ቀደም ብሎ፣ ከ1993 ጀምሮ ያጣችዉን የአሜሪካንን ወዳጅነት ዘንድሮ ከእስራኤል ጋር መታረቅን «ምርቃት» ጨምራ በ335 ሚሊዮን ዶላርና ገዛች።ከዘለቀ በርግጥ ደግ እንጂ ክፋት የለዉም። ሱዳን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ለወዳጅነቷ ፍጥምጥም የአሜሪካዉ መሪ ኢትዮጵያን «ጭዳ» ለማድረግ መቃጣታቸዉ እንጂ ለከት ያጣዉ እብሪታቸዉ።
«አስማምቼ ነበር።ስምምነቱን ጥሰዋል።ይሕን ማድረግ አይችሉም።ማድረግ አይችሉም።ስምምነቱ ተደርጎ ነበር።በጣም አደገኛ ሁኔታ ነዉ።ምክንያቱም ግብፅ በዚሕ መንገድ ልትኖር አትችልም።መጨረሻ ላይ ግድቡን ያፈነዱታል።ብያዋለሁ፤ እንደገና  ሳላድበሰብስና በግልፅ እለዋለሁ።ያንን ግድብ ያፈነዱታል።የሆነ ነገር ማድረግ አለባቸዉ።ማድረግ የምትችለዉን ሁሉ አድርግ፣ ኢትዮጵያ ማድረግ አለባት።ሊኖራቸዉ ይገባል እሺ? ለኢትዮጵያ የሚደረጉ ክፍያዎቹንና ሌሎችንም  በሙሉ አቁመናል።»
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ጆን ትራምፕ።አርብ፤ ጥቅምት 23 2020።የዲፕሎማሲ-ፖለቲካዊ ይትበሐል አልገባሕ ያላቸዉ እንዳላቸዉ 4 ዓመት የደፈኑት ሰዉዬ ካርቱምን ከዋሽግተን-እየሩሳሌም ለማገናኘት ግብፅና ኢትዮጵያን ለጦርነት ሲቆሰቁሱ፣ የልዕለ ኃያሊቱ ሐገር ትልቅ ድፕሎማት ማይክ ፖምፒዮን ጨምሮ የከበቧቸዉ ሹማምንቶቻቸዉ ያጨበጨቡ ነበር።
«አበጀሕ» ማለት ይሆን? አናዉቅም።የምናዉቀዉ ሰዉዬዉ ኢትዮጵያና ግብፅ ዉጊያ እንዲገጥሙ የቆሰቆሰቡት ጊዜ፣ምክንያትና አጋጣሚ አለመታወቁ ነዉ።«ለምን?» ለሚለዉ ጥያቄ፣ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን «ያዉ ትራምፕ» ሥለሆኑ የሚል አጭር መልስ አላቸዉ።
የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ የትራምፕን መልዕክት ሐገ ወጥ፣ሉዓላዊ ሐገርን መዳፈርና ዓለም አቀፍ ሕግንም የሚፃረር ብለዉታል።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን በበኩላቸዉ ትራምፕ ያሉትን አሉም አላሉ፣ ኢትዮጵያ ከግብፅና ሱዳን ጋር የምታደርገዉ ድርድር መቀጠሉ አይቀርም ባይ ናቸዉ።ይሁንና ኢትዮጵያ ገና ከጅምሩ የአሜሪካንን «ሸምጋይነት» መቀበሏን አቶ ዩሱፍ «ስሕተት» ይሉታል።
                                    
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን ኢትዮጵያ የአሜሪካንን «ሸምጋይነት» የተቀበለችዉ በሁለት ምክንያት ነዉ።ኢትዮጵያ በራስዋ ስለምትተማመን።-አንድ።አሜሪካ ከታዛቢነት ያለፈ ሚና ሥላልነበራት-ሁለት።
የትራምፕን መግለጫ የአዉሮጳ ሕብረት ነቅፎታል።እዚያዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥም ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የምክር ቤት እንደራሴዎች ተቃዉመዉታል።የአፍሪቃ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝደንት ሲርየል ራማፎዛ ዛሬ እንዳስታወቁት ለሁለት ወራት ያክል ተቋርጦ የነበረዉ የሶስቱ ሐገራት ባለስልጣናት ድርድር ነገ ይቀጥላል።
ፕሬዝደንት ራማፎዛ ዛሬ ባወጡት መግለጫ የድርድሩን መቀጠል «አካባቢያዊ ትብብርን የሚያጠናክር፣ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ» እያሉ አወድሰዉታል።ዉዳሴዉ የአፍሪቃ ሕብረት የትራምፕን መግለጫ አለመቀበሉን የሚያረጋግጥ በዉጤም ሕብረቱ ለኢትዮያ ዲፕሎማሲ ድጋፍ መስጠቱን ጠቋሚ ነዉ።ግብፅ  የሕዳሴ ግድብ ግንባታን «ለፀጥታ ስጋት» በማለት ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለማቅረብ እንደምትሻ ከዚሕ ቀደም አስታዉቃ ነበር።የግብፁን ፕሬዝደንት አብዱል ፈታሕ አል ሲሲን ባንድ ወቅት «የኔ ተመራጭ አምባገነን» ያሉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ አርብ ከአልሲሲ በልጠዉ የግብፅን ጦር ኢትዮጵያ ላይ ለማዝመት መቃጣታቸዉ ለአልሲሲ የልብ ልብ መስጠቱ አይቀርም።
                                    
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከግብፅ ይሁን ከሌላ ሥፍራ የሚደረግባትን ጫና ለመቋቋም አቶ ዩሱፍ እንደሚመክሩት የዉስጥ አንድነቷን መጠበቅ፣ ካለፈዉ ስሕተቶቿ መማር፣ እድሎችዋን በቅጡ ማወቅና መጠቀም ግድ አለባት።

BG Grand Renaissance Dam | Der äthiopische Außenminister Al Dardeery Mohamed Ahmed und seine Delegation verlassen das US-Finanzministerium in Washington (2019)
ምስል Reuters/S. Sibeko
BG Grand Renaissance Dam | Der äthiopische Außenminister Al Dardeery Mohamed Ahmed und seine Delegation verlassen das US-Finanzministerium in Washington (2019)
ምስል Reuters/S. Sibeko

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ