1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትምህርት ቁሳቁስ የዋጋ ንረት እና አዲሱ ስረዓተ ትምህርት

ዓርብ፣ መስከረም 13 2015

ከስረዓተ ትምህርቱ መተግበር ጋር ተያይዞ በተማሪ ወላጆች ዘንድ ቅሬታን ከፈጠሩ ነገሮች የትምህርት ቁሳቁስ የዋጋ ንረት እና አልቀመስም ማለት ተጠቃሾች ናቸው ። በተጨማሪም በአዲሱ ስረዓተ ትምህርት ቀደም ሲል በነጻ የነበረው፤ የትምህርት ክፍያ ተጠይቀናል » የሚሉ ሰዎች ቅሬታቸውን በተለያየ ሁኔታ እያቀረቡ ነው።

https://p.dw.com/p/4HG52
Äthiopien Studierende Tigray Universität
ምስል Solomon Muchie/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት

ጤና ይስጥልን አድማጮች የአዲሱ የትምህርት ዘመን በአዲስ ስዓተ ትምህርት መጀመር ፣ የትምህርት ቁሳቁስ የዋጋ ንረት ያስከተለው ምሬት እና በቀድሞያ የታላቋ ብሪታንያ ንግስት ኤልሳቤት ዳግማዊት የቀብር ስነ ስረዓት ላይ የታደሙ አፍሪቃውያን መሪዎች በተስተናገዱበት ሁኔታ ላይ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ያሰባሰበው የዛሬው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን ተጀምሯል። ታምራት ዲንሳ ነኝ
መሸጋገሪያ
በኢትዮጵያ አዲሱ የትምህርት ዘመን በአብዛኛው የመንግስትና የግል ትምህርት ባሳለፍነው  መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል። የዘንድሮው ትምህርት አጀማመር ከወትሮ የተለየ ያደረገው ደግሞ አዲሱን ሥርዓተ ትምህት ገቢራዊ በማድረጉ  ነው ፡፡ የትምህርት ሚንስቴር ላለፉት 5 ዓመታት ሲያዘጋጀው እንደቆየ የተነገረለት  አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከዓለማቀፍ  እና የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች ውጭ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ባሉ የግል እና  የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ገቢራዊ ተደርጓል። አዲሱ ስረዓተ ትምህርት  የእንግሊዘኛ ቋንቋን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከ 1ኛ እስከ 12 ክፍል እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ ሆኖ ተቀርጿል። 
ከ1ኛ - 6ኛ ክፍል  ግብረገብ ፣ አገር በቀል ዕውቀት ፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣  በአዲስ መልክ የሚሰጡ የትምህርት አይነቶች  ናቸው። 3ኛ ክፍል በክልሎቹ ውስጥ በስፋት የሚነገረውን ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ ተማሪዎቹ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲወስዱት ይደረጋል። ከ7ኛ ና 8ኛ ክፍል ሳይንስ ኬሚስትሪ እና ፊዚክስ በመባል በተናጥል ይሰጥ የነበሩት  የትምህርት አይነቶች አሁን አጠቃላይ ሳይንስ በሚል ተጠቃለው በአንድ የትምህርት አይነት ይሰጣል። የአዲሱ ስረዓተ ትምህርት ገቢራዊ መደረግ ከባለሞያዎች እና ከህብረተሰቡ የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል። በተጨማሪም አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር በተለይ በትምህርት ቁሳቁስ ላይ የታየው የዋጋ ንረት ደግሞ በራሱ ሌላ ምሬት ሆኖ በሳምንቱ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ ሃሳቦችን  አስተናግዷል።
ኢትዮጵያ ከበደ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ይህንኑ በተመለከተ በፌስ ቡክ ባሰፈሩት ሃሳብ 
በየአመቱ የስርዓተ ትምህርቱን መቀያየር አገሪቷ ላይ ምን ያህል የኢኮኖሚ ድቀት እንደምያስከትል ለመረዳት ተስኗቸዋል። የትምህርት ጥራት መጽሀፍ ብቻ በየአመቱ በመቀየር አይመጣም ። ሁሉም ወንበሩን ሲነካ እስኪወርድ  የራሱን አሻራ ጥያለሁ ለማለት ስረዓቱን ለመቀያዬር ደፋ ቀና ይላል። እዉነት ለተማሪ አዝኖ ከሆኔ በወቅቱ አስፈትኖ ወደቀጣዩ መሄድ ያቃተዉ መንግስት ለስረአት ለውጥ ብዙ ያወራልናል። በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። 
ቃዲ ቃዲ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው 
ትምህርትን ፖለቲካ አታድርጉት ።  በማለት በሰጡት አስተያየት ሚኒስትሩ ከመጡ ጀምሮ ሰለፈተና አስተዳደር ብቻ እንጂ እያስጨነቃቸው ያለው አዲሱ ስርአተ ትምህርትን ለመተግበር ቁልፍ ሰለሆነ የመማሪያ ና ማስተማሪያ መጽሃፍት ህትመትና ስርጭት አይደለም በማለት ስረዓተ ትምህርቱ ቢተገበርም የመማሪያ መጽሐፍት ስርጭት ትኩረት መነፈጉን በገለጹበት ሃሳባቸው ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ያለ መጽሃፍት እንዴት ነው ትምህርት በደማቅ ሁኔታ የሚጀመረው በማለትም ትምህርት በድምቀት መጀመሩን የተቹበትን ሃሳብ አጋርተዋል። 
ታደሰ ሲሞን የተባሉ አስተያት ሰጭ በበኩላቸው የስረዓተ ትምህርቱን ገቢራዊ መደረግ በበጎ ጎኑ ማየታቸውን በገለጹበት ሃሳባቸው 
«በጣም የሚበረታታ ተግባር ነው »  ብለዉታል። «ትምህርት ላይ መስራት ትውልድን ማሻገር የነገ የአገራችን እጣፈንታ የሚወስንአምራች ኃይል መገንባት ነው።» በማለትም ሃሳባቸውን አጋርተዋል። 
ግርማ ሎቤ በበኩላቸው  
ትልቁ ስጋቴ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጀመር አለመጀመሩ ሳይሆን ""የትምህርት ግብዓት በበቂ ሁኔታ" አለመዘጋጀቱና አለመሠራጨቱ  ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ። በተለይ ይላሉ አስተያየት ሰጪው  አሁን ላይ ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ በራሳቸው አቅም material's Soft copy ፕሪንት አድርገው እንዲወስዱት የተቀመጠው አቅጣጫ ዋስትናው አሳሳቢ ነው።
ትልቁ ስጋቴ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መጀመር አለመጀመሩ ሳይሆን """የትምህርት ግብዓት በበቂ ሁኔታ"" አለመዘጋጀቱና አለመሠራጨታቸው ነውና አሁን ላይ ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ በራሳቸው አቅም material's Soft copy ፕሪንት አድርገው እንዲወስዱት የተቀመጠው አቅጣጫ ዋስትናው አሳሳቢ ነው።
ከስረዓተ ትምህርቱ መተግበር ጋር ተያይዞ በተማሪ ወላጆች ዘንድ ቅሬታን ከፈጠሩ ነገሮች የትምህርት ቁሳቁስ የዋጋ ንረት እና አልቀመስም ማለት ተጠቃሾች ናቸው ። በተጨማሪም በአዲሱ ስረዓተ ትምህርት ቀደም ሲል በነጻ የነበረው፤ የትምህርት ክፍያ ተጠይቀናል » የሚሉ ሰዎች ቅሬታቸውን በተለያየ ሁኔታ እያቀረቡ ነው። 
አባ ገዳ ሮባ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ባሰፈሩት ሃሳባቸው 
«ሁለት ልጆች አስተምራለሁ። ደብቴር ፣ እስክሪብቶ ፣ ቦርሳ ፣ ዩኒፎርም እና የምዝገባ ለአንድ ተማሪ 3ሺ ፈጅቶብኛል» ይላሉ። ለኔ 6ሺ ያስፈልገኛል። አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ነፃ የነበረዉን የትምህርት ቤት ክፍያ አስቀርቷል።» በማለት የገጠማቸውን አካፍለዋል።
በለው ቶለሳ የስረዓተ ትምህርቱን አስፈላጊነት ነገር ግን ሊደረግ ይገባዋል ብለው ባሰፈሩት የጥንቃቄ ሃሳባቸው 
«የትምህርት ግብዓት ፣ በጄት እና አግባብነቱ  ከጅምሩ ይታስብበት።»  ብለዋል። ሥርዓተ ትምህርቱ ሊጓዝ የሚገባ ርቀት መሄድ ይኖርበታል። ያሉት አስተያየት ሰጪው በተለይም ሶስት ጉዳዮችን በትኩረት ቢያካትት ባ,ሉት ሃሳባቸው ፦1 የሰው ኃይል ተፈላጊነትን መሰረት ያድረገ ፣ አከባቢ ተኮር ትምህርት ወይም ህዝብን ያማከል  እና እንዲሁም ውጤታማነት ታሳቢ ሊad,ርግ ይገባል፤ ይህ ደግሞ የተማረ ስራ አጥነትን ይቀንሳል « በማለትም ሃሳባቸውን አጋርተዋል።  
ወደ ተከታዩ ዘገባችን ስንሸጋገር የታላቋ ብሪታንያ ንግስት በነበሩት ንግስት ኤልሳቤት የቀብር ስነ ስረዓት ላይ የተገኙ አፍሪካውያን መሪዎች የተስተናገዱበት ሁኔታ አወዛጋቢ አስተያየቶችን አስተናግዷል። በቀብር ስነ ስረአቱ ላይ የተገኙ የተወሰኑ አፍሪካውያን መሪዎች በአውቶቢስ ተችነው ሲሄዱ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ገጾች ላይ ሲንሸራሸር መታየቱን ተከትሎ በርካታ አሉታዊ አስተያየቶች ሲሰጥ ታይቷል ። የሃሳቡ መነሻ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የአንዳንድ አዉሮጳ ሃገራት መሪዎች በተናጥል በግል ተሽከርካሪዎቻቸው ወደ ስፍራው እንዲጓዙ ተደርጓል የሚል እንደሆነ ነው የተሰራጩት መረጃዎች የሚያመለክቱት ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ይህንኑ «በአንድ አውቶቢስ የመጓዝ ሃሳብ አልቀበልም አሉ» በሚል የተሰራጩ መረጃዎች ለእርሳቸው ምስጋና እና ዉዳሴ አስገኝቶላቸዋል። ነገር ግን በወቅቱ የመሪዎቹ በዚህ መልክ እንዲጓዙ ስለመደረጉ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በሁኔታው ላይ ሃሳባቸውን ያጋሩ ሰዎችን ሃሳብ ግን መመልከት ይቻላል። 
ካናሪ ሙጉሜ የተባለው ታዋቂ ዩጋንዳዊ ጋዜጠኛ በትዊተር ባሰፈው ሃሳብ በንግስቲቱ የቀብር ስነስረዓት ላይ የተሳተፉ አፍሪካውያን መሪዎች ልክ ከሰፈራችን በአውቶቢስ ተጭነው ወደ መዝናኛ ስፍራ የሚጓዙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ይመስሉ ነበር » ብሏል።
ኢማኑኤል ሊቡምባ የተባሉ አስተያየት ሰጬም በተመሳሳይ በትዊተር ባሰፈሩት ሃሳባቸው « ወደ እንግሊዝ የተጓዙት መሪዎቻችን ልክ እኛን በሚይዙት ሁኔታ ነበር አቀባበል የተደረገላቸው » ብለዋል። 
የሰላም ሚንስትር ሚንስትር ዲኤታ ታዬ ደንደአ በስነ ስረዓቱ ላይ የተሳተፉትን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ባሞካሹበት የትዊተር መልዕክታቸው 
«እምቢኝ የምልባቸው ጊዜያቶች አሉ» ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ቅኝ ያልተገዛች ኩሩ ሃገር ናት ያሉት ታዬ «የአድዋ ታሪካችን ለዚህ ምስክር ነው» ብለዋል።  ፈጽሞ በደል አንቀበልም ፣ በጭራሽ አናደርገውም፤ ክብርት ፕሬዚዳንት ይህን በማድረግዎ እንኳን ደስ ያልዎት ፣ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር መሰረት ሁሉም ሉአላዊ ሃገራት እኩል ናቸው ብለዋል። 
ቤቢሾ ነኝ በሚል ስም ፌስ ቡክ ላይ በተሰጠ አስተያየት «ሀገራችን በቀኝ ግዛት አለመገዛቷ እና እንደማትገዛ ዳግም ማሳያ ነው። ክብርት ፕረዚዳንት ጀግኒት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለነጮች ባለመንበርከክ የአባቶቻችን አደራ በብቃት ተወጥታለች። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት በራሱ ኩራት ነው። ለነጮች ለዘመናት እንቆቅልሽ የሆነባቸውን የኢትዮጵያ አልበገር ባይነት ነገም እንደ ትናንቱ ይቀጥላል» ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የራሳቸውን "ዘ ቢስት" ተብሎ የሚጠራውን ብረት ለበስ መኪና ተጠቅመው ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ተዘግቧል። 
በጉዳዩ ላይ ዘገባ ያወጣው ዘ ኢንዲፔንደንት  «ለፕሮግራሙ ፀጥታ እና ለሁሉም ደህንነት ሲባል የክቡር እንግዶች መኪናቸውን እና ጠባቂዎቻቸውን Royal Hospital Chelsea የሚባለው ስፍራ እንዲያቆሙ ተደርጓል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ካለባቸው ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የተነሳ በራሳቸው መኪና እንዲጓዙ ተደርጓል" ብሏል። 
እንግዲህ አድማጮች ለዕለቱ ያልነው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅንት ዝግጅታችንም የእስካሁኑ ነበር ጤና ይስጥልን ። 

ታምራት ዲንሳ

Großbritanien I Chinas Vizepräsident Wang Qishan trifft vor dem Staatsbegräbnis von Königin Elizabeth II. in der Westminster Abbey ein
ምስል PHIL NOBLE/AFP
Tod von Queen Elizabeth II
ምስል Victoria Jones/empics/picture alliance
DW Learning by Ear Afghanistan Herat
ምስል DW
Äthiopien | Einführung eines neuen Lehrplans
ምስል Shwangizaw Wegayehu/DW

ሸዋዬ ለገሠ