1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታንዛኒያ ምርጫ፣ የካሜሩን እገታ

ረቡዕ፣ ኅዳር 2 2013

ማጉፉሊ ቀስበቀስ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ተቺ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ አቀንቃኞችና የመብት ተሟጋቾችን እያነቁ  ወሕኒ ቤት ሲጥሉ ወይም ከየመስሪያ ቤት ድርጅቱ ሲያፈናቅሉ ቡልዶዞሩ ከፊቱ ለሚቆም ሁሉ ምሕረት የለሽነቱ ተረጋገጠ።አድናቆት፣ዉዳሴ፣ድጋፉ ወደ ተቃዉሞ ጥላቻና ፍራቻ ተለወጠምም።

https://p.dw.com/p/3lA2v
Tansania Amtseid des Präsidenten John Pombe Magufuli
ምስል Tanzania Presidential Press Service

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የታንዛኒያ ምርጫ፣ እገታ በካሜሩን

አብዛኛዉ ዓለም የዩናይትድ ስቴትስን ምርጫ፣ የድምፅ ቆጠራ፣ ዉዝግቡንና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቷን እንዴትነት ሲያጠያይቅ፣ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ሐገር ታንዛኒያ ምርጫ አስተናግዳ፣ ፖለቲከኞቿን- አንዳወዛገበ፣ የእስካሁን መሪዋ በነበሩበት ሥልጣን መፅናታቸዉን አረጋግጣጠለች።ጆን ፖምቤ ጆሴፍ ማጉፉሊ።ታንዛኒያን ላለፉት አምስት ዓመታት የመሩት ማጉፉሊ ባለፈዉ ሳምንት ሮብ በተደረገዉ ምርጫ አሸነፍኩ አሉ፣ ተባለላቸዉ፣ በሐሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ተረጋገጠም።ሰኞ።

 «በዚሕ አጋጣሚ ለወገኖቼ ታንዛኒያዉያን በሙሉ እኔ የፖለቲካ ፓርቲያቸዉ፣ኃይማኖታቸዉ ወይም ጎሳቸዉ ቢለያይም የሁሉም ታንዛኒያዉያን ፕሬዝደንት መሆኔን ላረጋግጥላቸዉ እወዳለሁ።»

የ61 ዓመቱ ፖለቲከኛ ድል አድራጊነታቸዉ ሲረጋገጥ ካሉት ዉጪ በርግጥ ሌላ ሊሉ አይችሉም።የአሸናፊ መሪ ወግ ነዉና።ወግ ያልሆነዉ የድላቸዉ መሠረት የዴሞክራሲያዉን ይትበሓል የጣሰ፣ ከሐቅ ይልቅ በማጭበርበር፣ ከፍትሐዊነት ይብስ በጉልበት ላይ የተመሠረተ መባል-ማጠራጠሩ ነዉ።

ሰዉዬዉ ኃይለኛ ናቸዉ።በ2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የመጀመሪያዉን ዘመነ-ሥልጣናቸዉን እንደጀመሩ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር ከሙስና ለማፅዳት፣ በተለይ ዋልጌ ሚንስትሮችንና ባለስልጣናትን ለመቅጣት ጠንካራ ክርናቸዉን አሳርፈዉ ነበር።በሙስናና በሙስኞች ላይ የወሰዱት  ርምጃ ሐገራቸዉን ምጣኔ ኃብት ለማሳደግ ካደረጉት ጥረት ጋር ተዳምሮ «ቡልዶዘር» (ደፍላቂዉ) የሚል ቅፅል አትርፈዉ፣ ሕዝባቸዉ ያወድስ-ያደንቃቸዉም ነበር።

ማጉፉሊ ቀስበቀስ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ተቺ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ አቀንቃኞችና የመብት ተሟጋቾችን እያነቁ  ወሕኒ ቤት ሲጥሉ ወይም ከየመስሪያ ቤት ድርጅቱ ሲያፈናቅሉ ቡልዶዞሩ ከፊቱ ለሚቆም ሁሉ ምሕረት የለሽነቱ ተረጋገጠ።አድናቆት፣ዉዳሴ፣ድጋፉ ወደ ተቃዉሞ ጥላቻና ፍራቻ ተለወጠምም።

ተቃዋሚዎች እንደሚሉት የማጉፉሊ ጨካኝ በትር ካረፈባቸዉ ፖለቲከኞች፣ አንጋፋዉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ታንዱ አንቲፋስ ሙጋዋይ ሊሱ አንዱ ናቸዉ።ሊሱ CHADEMA የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበርና ከ2010 ጀምሮ ደግሞ የታንዛኒያ ብሔራዊ ምክር ቤት (ፓርላማ) አባል ናቸዉ።

መስከረም 7፣ 2017 የምክር ቤቱ ጉባኤ ለእረፍት ሲበን፣ ሊሱ ከመሰብሰቢያዉ አዳራሽ በአጭር እርቀት ላይ ወደሚገኘዉ ቤታቸዉ ሔዱ። ከሚኪናቸዉ ሳይወርዱ ጥይት ተርከፈከፈባቸዉ።16 ጥይት።የተኳሾቹ ማንነትና ዓላማ እስካሁን በዉል አልታወቀም።ሊሱ ግን የጥቃቱ ዓላማ «ፖለቲካዊ ግድያ ነበር» ባይ ናቸዉ።እዚያዉ ታንዛኒያ፣ ኬንያና ቤልጂግ ለ3 ዓመታት ከታከሙ በኋላ በእሳቸዉ አባባል በቡልዶዘሩ ከመደፍለቅ ተረፉ።በዘንድረዉ ምርጫም የማጉፉሊ ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆነዉ ተወዳደሩ።ማጉፉሊ «የዘንድሮዉን የምርጫ አሸነፍኩ» ያሉትም ሉዊስ እንደሚሉት የድምፅ አሰጣጡን ሒደት «ደፍልቀዉ ነዉ።»

Tansania Singida | Wahlen | Tundu Antiphas Lissu
ምስል Said Khamis/DW

«ምርጫዉ ነፃ፣ ፍትሐዊና አሳማኝ እንዲሆን ሕጉ የሚደነግገዉ ጥንቃቄና ሥርዓት በሁሉም የምርጫ ሒደት ገቢራዊ  አልሆነም።ሒደቶቹ በሙሉ የታንዛኒያን ሕዝብ እዉነተኛ ፍላጎትን ያካተተና የሚያንፀባርቅ አይደለም።»

የሊሱን ተቃዉሞ በታንዛኒያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፣ የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነርና ሌሎች የዉጪ ተቋማትም አስተጋብተዉታል።የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚንሽን እንዳስታወቀዉ በምርጫዉ ከተሰጠዉ ድምፅ ማጉፉሊ 13 ሚሊዮን የሚጠጋዉን ወይም 84 ከመቶዉን አግኝተዉ አሸነፉ።5 ዓመት የሚዘልቀዉን ሁለተኛ ዘመነ ሥልጣናቸዉን ለመጀመርም ሐሙስ ቃለ መሐላ ፈፀሙ።

«ምርጫዉ አብቅቷል።አሁን አስፈላጊዉ ጉዳይ የሐገራችንን ምጣኔ ሐብት በመገንባት ላይ ማተኮር ነዉ።ወገኖቼ! ታንዛኒያዉያን ሆይ! እኔና ምክትል ፕሬዝደንቴ ቃለ መሐላ የፈፀንበትን ሕገ-መንግስቱን ለማክበር የሚከፈለዉ ዋጋ ምንም ቢሆን ከፍለን  እንደምናከብረዉና እንደምንጠብቀዉ አረጋግጥላችኋለሁ።»

የሙጉፉሊ ዋነኛ ተቀናቃኝ ታንዱ ሊሱ ከተሰጠዉ ድምፅ 13 በመቶዉን አግኝተዋል ነዉ የተባለዉ።ከፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ጎን ለጎን በተደረገዉ የምክር ቤት አባላት ምርጫም የማጉፉሊ ቻማ ቻ ማፒንዱዚ (CCM) አብዛኛዉን መቀመጫ ተቆጣጥሯል።የታንዛኒያ የነፃነት አባት ጁሊዮስ ኔሬሬና ጓዶቻቸዉ የመሠረቱት ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ታናዛኒያ ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ከ1961 ጀምሮ ከስልጣን ተለይቶ አያዉቅም።

 

የታንዛኒያ ምርጫ

የአሜሪካኖች ምርጫና ዉዝግብ እንደታንዛኒያዉ ሁሉ ከታንዛኒያ ብዙ ሺሕ ኪሎሜትር ርቀት ምዕራብ አፍሪቃ ላይ የምትገኘዉ ኮት ዲቯር ወይም አይቮሪ ኮስት ያስተናገደችዉን አወዛጋቢ ምርጫ ሒደትና ዉጤትንም አጥልቶበታል።

ከአቮሪኮስት ወደ ደቡብ ምሥራቅ ሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር ድግም ከታንዛኒያ በስተ ሰሜን ምዕራብ 3 ሺሕ ኪሎ ሜትር የምትርቀዉ የካሜሩን ሰሞናዊ ርዕስ ግን ምርጫና ዉዝግቡ አልነበረም።ግጭት እንጂ።ለረጅም ዘመናት ዓለምንም፣ አፍሪቃንም ረስታ ዝም ያለች ትመስል የነበረችዉ ያቺ የማዕከላዊ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ለም ደናማ ሐገር ከናጄሪያ ጋር የሚያዋስናት የድንበር ግዛትዋ የአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኮ ሐራም የሽብር ዒላማ ከሆነ ወዲሕ በሽብር-ፀረ ሽብር ዉጊያ የተጠመደዉ ዓለም አካል ሆናለች።

Kamerun Kumba Schüler bei PC-Unterricht
ምስል imagebroker/imago images

ሰሞኑን የባሰባት ግን ለረጅም ጊዜ በዝምታዋ ዉጣዉ ዝም ያለችዉ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ፖለቲከኞችዋ ከያዉንዴ ማዕከላዊ መንግስት ጋር የገጠሙት ግጭት ነዉ።ካሜሩን ድሮ የጀርመን ኋላ የፈረንሳይና የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ለሁለት ገምሰዉ ይገዟቸዉ የነበሩት ግዛቶች ድምር  ናት።

ለረጅም ጊዜ ሁለቱን ግዛቶች አማክሎ ይገዛ የነበረዉ ወይም የመሰለዉ የያዉንዴ መንግሥት ጫና የበዛባቸዉ የቀድሞዉ የብሪታንያ ቅኝ ተገዢ የሰሜን ምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ካሜሩን ግዛት ፖለቲከኞች የዛሬ 3 ዓመት ግድም ነፃነት አወጁ።

አዋጁን ፕሬዝደንት ፖል ቢያ ጨርሶ የሚቀበሉት አልነበረም።እኚያ ሽቅርቅር፣ አይናፋር፣ ኮልታፋ፣ መኮላተፋቸዉን ለመደበቅ ዝምታን የሚመርጡት፣ ፈገግታ የሚያበዙት ግን መሰሪ ፖለቲከኛ ነፃነት ያወጁትን ተገንጣዮች ለመደፍለቅ የወሰዱት የኃይል እርምጃ ከደም አፋሳሽ ዉጊያ በስተቀር እስካሁን ላሰቡት ዉጤት አልመብቃቱ ነዉ ክፋቱ።በነገራችን ላይ ቢያ ካሜሩንን መግዛት ከጀመሩ ዛሬ 39ኛ ዓመታቸዉን ይዘዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR) ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ተራዉ ሕዝብ ከዉጊያዉ ያተረፈዉ ሕይወት፣አካል ሕብት ንብረቱን መገበር ብቻ ነዉ።

«በካሜሩን ሰሜናዊ ምዕራብና ደቡባዊ ምዕራብ ግዛቶች ዉስጥ በሚደረገዉ ሕዝቡ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ቀጥሏል።አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በደል መፈፀሙን የሚጠቁሙ ዘገቦች እየደረሱን ነዉ።የኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ባሁኑ ወቅት የመንግስት የፀጥታና የመከላከያ ኃይላትም፣ የታጠቁ ተገንጣይ ቡድናትም ከፍተኛ የመብት ጥሰት እያደረሱ ነዉ።»

የደፈጣ ተዋጊዎቹና የመንግስት ጦር ዉጊያ መዘዝ ሰሞኑን ለተማሪ አስተማሪዎች ተርፎ ትምሕርት ቤቶች የግድያ፤ የአጋች-ታጋቾች ድራማ እያስተናግዱ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ደቡባዊ-ምዕራብ ካሜሩን ኩማባ በተባለ ከተማ የሚገኝ ትምሕርት ቤትን የወረሩ ታጣቂዎች 6 ተማሪዎችን ገድለዋል።13 አቁስለዋል።ሟች ቁስለኞቹ በ9ኝና በ12 የዕድሜ ክልል ዉስጥ የነበሩ ነበሩ።የቅዳሜዉን ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች ማንነት በግልፅ ሳይረጋገጥ ባለፈዉ ማክሰኞ ታጣቂዎች ኩምቦ ከተባለ ከተማ 11 የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ተማሪዎችና አስተማሪዎች አግተዉ ነበር።የማክሰኞዉ እገታ በ2 ወር ዉስጥ 25ኛዉ ነዉ።ታጋቾቹ ትናንት ተለቅቀዋል።ይሁንና ሌሎች ላለመታገት ወይም ላለመገደላቸዉ ምንም ዋስትና የለም።የካሜሪንን የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ግዛትን ከማዕከላዊ መንግስቱ አስተዳደር ለመገጠል የሚሹት ኃይላት የነፍጥ ዉጊያ  ከጀመሩ ከ2017 ወዲሕ በተደረገዉ ዉጊያ 3000 ሰዉ ተገድሏል፤ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ተፈናቅሏል።  

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ