1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታቀደዉ ብሔራዊ ምክክርና የባልደራስ አቋም

ሐሙስ፣ ጥር 5 2014

በኢትዮጵያ ሊደረግ በታሰበው ብሔራዊ ምክክር የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉአላዊነትን ማስቀጠል እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ማስቀመጡን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ገለፀ። መንግሥት በሕወሓት ላይ የሚወስደውን እርምጃ ማቆሙ ትልቅ አደጋ አዝሏል፣ እናም የድርጅቱን ወታደራዊ አቅም በመስበር መቋጨት ይገባዋል ብሏል።

https://p.dw.com/p/45Td4
Balderas For True Democracy party president Eskindir Nega
ምስል Solomon Muchie/DW

መንግሥት የትግራይ ሕዝብንም ነፃ ሊያወጣ ይገባል

በኢትዮጵያ ሊደረግ በታሰበው ብሔራዊ ምክክር የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉአላዊነትን ማስቀጠል እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ማስቀመጡን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ገለፀ።
ፓርቲው ዛሬ በሰጠው መግለጫ በእሥር ላይ ቆይተው ባለፈው አርብ የተለቀቁት ከፍተኛ አመራሮቹ ተገኝተዋል።
የአመራሮቹ እሥር ፖለቲካዊ ፍላጎት እንደነበርና በይቅርታ ሳይሆን ነፃ በመሆናቸው መለቀቃቸውንም አመራሮቹ ተናግረዋል።
የተፈቱበት ሂደት ድንገተኛ እንደነበርም ገልፀዋል።
ሕወሓት አሁንም የኢትዮጵያን አንድነት ሊፈታተን በሚችል ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል ያለው ባልደራስ መንግሥት በሕወሓት ላይ የሚወስደውን እርምጃ ማቆሙ ትልቅ አደጋ አዝሏል፣ ይልቁንም የድርጅቱን ወታደራዊ አቅም በመስበር መቋጨት ይገባዋል ብሏል።
በዚህ ዙሪያ መንግሥት እስከ ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ድንበር መረብ ድረስ ሕግን ማስከበር እንዳለበት እና በአፈና ውስጥ ይገኛል ያለውን የትግራይ ሕዝብም ነፃ ሊያወጣው እንደሚገባ አሳስቧል።
የሕወሓት የፖለቲካ እና የጦርነቱ ዋነኛ ቀያሾች ያላቸው እና ጉዳያቸው በሕግ ጥላ ሥር የነበረ እሥረኞች ከሰሞኑ መፈታታቸው የሕግ የበላይነትን የጣሰ ውሳኔ ብሎታል ባልደራስ።
መንግሥት የግዛት አንድነትን የማስጠበቅ ኋላፊነት እንዳለበት የገለፀው ፓርቲው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ለመንግሥት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ብሏል።
ሕይወታቸውን በጦርነት ያጡ ዜጎችን መካስ የሚቻለውም ቢያንስ አዲስ ሕገ መንግሥት በማውጣት መሆኑንም ፓርቲው ተናግሯል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ነገ ወደ አፋር፣ ቅዳሜ ደግሞ ወደ ባሕርዳር እና ተፈናቃዮች ወደሚገኙበት አካባቢ በመሄድ ሕዝብ ላደረገው ተጋድሎ ምስጋና እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

Balderas For True Democracy party president Eskindir Nega
ምስል Solomon Muchie/DW

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ