1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታስሩት ጋዜጠኞች፤ የጃዋር «የምስጋና ጉዞ» የህዝብ አገልግሎቶች የተነፈገችዉ ትግራይ

ዓርብ፣ ሰኔ 3 2014

«ሑከትና ብጥብጥ በማነሳሳት» ወንጀል ተጠርጥረዉ የታሰሩ ጋዜጠኞች ላይ ተጨማሪ 8 ቀናት መፈቀዱ፤ በትግራይ ወደ አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ የህዝብ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በመቋረጣቸው ነዋሪዉ ችግር ዉስጥ መግባቱ፤ እንዲሁም የፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ «የምስጋና ጉዞ» በተሰኙ ዘገቦች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን ይዘናል።

https://p.dw.com/p/4CXJc
Social Media Apps | WhatsApp Facebook Twitter Instagram
ምስል Nasir Kachroo/ZUMA Press/imago images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 «ሑከትና ብጥብጥ በማነሳሳት» ወንጀል ተጠርጥረዉ የታሰሩ ጋዜጠኞች ላይ ፖሊስ ለሚያደርገዉ ምርመራ ተጨማሪ 8 ቀናት መፈቀዱ፤ በትግራይ ወደ አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ እንደ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ባንክ የመሳሰሉ የህዝብ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በመቋረጣቸው ነዋሪዎች ለከፋ ኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ ችግር መጋለጣቸው ፤ እንዲሁም  የፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ «የምስጋና ጉዞ» በተሰኙ ዘገቦች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምቀን በዚህ ዝግጅት ይዘናል። 


 «ሑከትና ብጥብጥ በማነሳሳት» ወንጀል ተጠርጥረዉ የታሰሩት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣መዓዛ መሐመድ እና ሰለሞን ሹምዬ በዋስ እንዲለቀቁ ተላልፎ የነበረዉ ዉሳኔ ተሽሮ፤ በጋዜጠኞቹ ላይ ለሚያደርገዉ ምርመራ ፖሊስ ተጨማሪ 8 ቀናት ተፈቀዶለታል። ባለፈዉ ግንቦት ሠላሳ የዋለዉ የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሦስቱ ጋዜጠኞች እያንዳደቸዉ በ10 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ወስኖ ነበር። ይሁንና ከሳሽ አቃቤ ሕግ ዉሳኔዉን በመቃወም ይግባኝ በማለቱ ጋዜጠኞቹ አልተፈቱትም።   
ዞሉ ዙዙ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ፤ አይ እውነተኛ የፍትህ ተቋም ግንባታ። ፍትህ እንዲህ በጠረባ ስትዘረር ማየት እንደ ዜጋ እንዴት ያማል? ጎበዝ መላ ፈልግ፤ ነግ በኔ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል። 
የጉድ ሃገር። መቼም በዚህ ልክ ሀገራችን ወርዳ አታውቅም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት ዮናስ ሰለሞን ናቸዉ። 
ታደለ ግዛቸዉ በበኩላቸዉ፤ ወይ ፍትህ። ፍርድ ቤቶች በፖለቲከኞች ታጭቀው በባለስልጣናት ትዕዛዝ ፍትህ ይነፈጋል፤ ብለዋል። 
ግዛቸዉ ገብሬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቆይ የምን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ነው? ሲሉ በጥያቄ ረዘም ያለ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። ቆይ የምን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ነው? መጀመሪያውኑ ግለሰቦቹ ዋስትና የጠየቁት ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀው ጊዜ  ስላለቀ አይደለም ነበር እንዴ? አካሔዱ የገባችሁ ግልፅ ብታደርጉልኝ ካለቀ በኋላ ከሆነ የፖሊስ አቤቱታ እና የከ/ፍ/ፍቤቱ ትዕዛዝ ሊተች የሚገባው ይመስላል። እባካችሁ የገባችሁ አስረዱኝ ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።  
አፈናና ጭቆናን የለመደ አንደበት ነፃነቱን ሲያገኝ ያለቅጥ መናገርም መብቱ ይመስለዋል ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት አሰግድ በእዉቀቱ ናቸዉ። እንደአሰግድ በእዉቀቱ ሁሉ ብሩክ ያሲኖም ተመሳሳይ አስተያየት አስቀምጠዋል። 
ብሩክ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ የፍትህ ሂደት ነው፤ ሲሉ ይጀምራሉ። የፍትህ ሂደት ነው።  የህግ አስፈፃሚና የህግ ተርጓሚ አካላት ህጉ በሚፈቅደው እስከተጓዙ ድረስ ያን ያህል የሚያበሳጭ የሚያወራጭ ነገር አይደለም፤ የህግ አፈፃፀሙ ክፍተት አለው ከተባለ ለሁሉም እንዲስተካከል ጥረት ማድረግ እንጂ በሚድያና በፖለቲከኛ ላይ ሲሆን መጯጯሁ አይገባም፤ ሲሉ ጋዜጠኞቹ ይታሰሩ የመናገር ነፃነት ይደፈቅ አይነት ነገር አስተያየታቸዉን ፅፈዋል። 
 ዘንድሮ ሰው አየሁ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ይህን ሕግ አንለውም፤ የእገታ የበላይነት ነው። ከገባህ ነገ ተራው ያንተ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 
ወልደሰንበት ጥበበ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ወይ ጉድ ፤ ሲሉ ነዉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ። ወይ ጉድ፤ የተሰጠውን ታርጋ ስትመለከት እንቆቅልሽ ጨዋታ ይመስላል ። ድሮ ሰዎች ፀረ ሰላም የግ*7  እና የኦነ* ደጋፊ እየተባሉ በጨለማ ቤት ይሰቃዩ ነበር። አሁንም በተመሳሳይ ያው ተደገመ። ወይ ጉድ ብለዋል። 

Gefangener hinter Gittern (Symbolbild)
ምስል YAY Images/imago images

ጥበበ ተስፋዬ የተባሉ የፊስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ ፍትህ ፍትህ ለሀገራችን ህግ፣ ህግ የግለሰቦች ፍላጎት ማስፈፀሚያ ከመሆን ነፃ ከወጣ፤ ሕዝብ ፍትህ ያገኛል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 
በላይ አንለይ የተባሉ የፊስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ፍትህ ወዴት አለሽ? ሲሉ አጠር ባለ ጥያቄ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። 
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የአሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ኦፌኮ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፤ ፖለቲከኛ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ  «የምስጋና ጉዞ» ብለው የሰየሙት በአውሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለመገናኘት የሚያደርጉትን ጉዞ ከጀርመን ጀምረዋል። አቶ ጀዋር መሐመድ ባለፈው ቅዳሜ በደቡባዊ የጀርመን ከተማ ፉርት ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተገናኝተዋል። የጉዟአቸውን ዓላማ «የምስጋና እና የቀጣይ ፖለቲካዊ ጉዞ አቅጣጫ ማሳያ » ብለውታል። አቶ ጀዋር ከጀርመን በተጨማሪ፤ በፈረንሳይ ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቤልጅየም እና ኖርዌይ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ማሕበረሰቦች ጋር ተገናኝተዋል።
አቤል አሌክስ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ ጃዋርን የሚጠላ ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ በርታልን ስለሠላም መስበክህን አታቁም። ሀገራችንን ማን እንደጎዳት መንግሥትም ህዝብም አውቆ ለተሻለ ወንድማማችነት እየሰራ ነው፡፡ ሀገር የምትገነባው በቂም በቀል ሳይሆን አብሮ ለሠላም ዘብ በመቆም ነው ስለዚህ በጀዋር ሙሉ እምነት አለን። ሀገራችንን ወደ ሠላም ከሚመልሱት ውስጥ አንዱ ጃዋር ነዉ ሲሉ አስተያ,ታቸዉን ሰጥተዋል። 
ሄለ ገሠሠ በበኩላቸዉ፤ ጀዊ ልቦና የሰጠህ እግዜሀብሄር ይመስገን። በዚሁ ቀጥልበት። ወንድማችን እንወድሀለን ጀዌ ሲሉ አጠር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል። 
ዘካሪያስ ሽብሩ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፤ ብሔረተኝነትህን ብትተው ኖሮ ይላሉ ብሔረተኝነትህን ብትተው ኖሮ ወይም አሁን ያለህን ሀሳብ ቀድመህ ብታመነጭ ኖሮ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አንተ ትሆን ነበር ብለዋል። 
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኖራለች ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት፤ ፍራፍሪ ብርሃኔ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያን ከፅንፈኞች የሚጠብቅ አምላክ አይትኛም አያንቀላፋም፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።   
ስብሃት አስማረ በበኩላቸዉ፤ አሁን ሰው አገኘን። ትልቅ ማስተዋል ነው ሲሉ ያሞግሳሉ። በርታልን ጀዋር እግዚአብሄር ከቅን አስተሳሰብ ጋር ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 
እየተከታተልነዉ ነዉ። በጣም ተስፋ ሰጭ አቅጣጫን እየጠቆመ ነዉ። መደማመጡን ይስጣቸዉ ኢሊቶቻችን፤ ምሁሮቻችን ሲሉ አስተያየታቸዉን ፌስቡክ ላይ ያስቀመጡት ደግሞ መሃመድ ገሜ የተባሉ ተጠቃሚ ናቸዉ። 

Äthiopien I Jawar Mohammed
ምስል Mulugeta Ayene/AP Photo/picture alliance

አወል ኡመር የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ደግሞ፤ ጃዋር የሚናገረዉ እና ሲከተለዉ የነበረዉ የፖለቲካ ፍልስፍና ሰማይ እና መሬት ነዉ ሲሉ ነዉ አስተያ,ታቸዉን የፃፉት። 

መአዛ አስቻለዉ ቤተፅናት የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በአስተያየታቸዉ ይጠይቃሉ። እና ህዝብና ሀገርን ለዛ ምስቅልቅል አሳልፈው ከሰጡት ኣንዱ ሆኖ አሁን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ እያለን ነው በቃ?
ክፍሌ ማሞ በበኩላቸዉ nomore# ሲሉ ነዉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት። nomore#- የሠላም መደፍረስ መነሻ ምክንያቶች ኃላፊነት የማይሰማቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፖርቲ መሪዎች ስለሆኑ ፖርቲዎቹ ይፍረሱ። በቃ# ብለዋል። 
ብሩክ ያሲኖ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ  ተጠቃሚ፤ የፈገግታ ምስል አስቀምጠዉ ነዉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት፤ ዋናው ነጥብ ሚስተር ጁሃር መሃመድ እና አባሪዎቻቸው  መሰሎቻቸው ከእስር የተለቀቁት  የብልፅግና ፓርቲ በድንገት በወሰነው የይቅርታ ውሳኔ መሆኑ አያወያይም። አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ዘግተዋል። 
 
በትግራይ ከአንድ ዓመት ገደማ ለሚሆን ጊዜ እንደ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ባንክ የመሳሰሉ የህዝብ አገልግሎት ሙሉበሙሉ በመቋረጣቸው የትግራይ ነዋሪዎች ለከፋ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ችግሮች መጋለጣቸውን የገለፁት በዚህ ሳምንት ነዉ። ለአንድ ዓመት የቴሌኮም አገልግሎት በትግራይ ሙሉበሙሉ በመቋረጡም በሚልዮኖች የሚገመቱ ቤተሰቦች ተጠፋፍተዋል፣ ባንኮች በመዘጋታቸው ዜጎች ገንዘብ የላቸዉም።
ሙሉጌታ ራያዉ፤ እና አሁንስ ምን ተስፋ አለ? ይላሉ በጥያቄ፤ እና አሁንስ ምን ተስፋ አለ? የምናውቀውን ከምትደጋግሙልን የተሻለ ተስፋ ሰጪ ወሬ የለም እንዴ? በትግራይ ቤተሰቦቻችን ችግር ውስጥ ናቸው፤ ሲሉ  ሙሉጌታ ራያዉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። 
ሞሃመድ ያኩቤ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ምንም የማያቀው ድሃው ህዝብ ያሳዝናል። ግን የሄን ችግር ያመጣው የራሱ ህውሃትመሆኑን መዘጋት የለበትም ሲሉ አስተያየት ፅፈዋል። ፀጋዬ ብርኃኔ በበኩላቸዉ ፤ ይነጋል ህዝቤ ይህም ያልፋል ሲሉ ነዉ ነዉ አጠር ያለ አስተያየት ያስቀመጡት። አቤቱ ጌታ ሆይ ፊትህን መልስ- ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት ፍቅሬ ሙላዉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸዉ። አብዱላ አሚን ኢብራሂም የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ፤ እዛ out of cash ከሆነ እኛ ጋር ግን ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ነዉ የሆነዉ ብለዋል።  
ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ አሸባሪው ህወሃት ነው። የትግራይ ህዝብ መንቃት አለበት፤ ሲሉ የፃፉት ሌላዉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሞሃመድ አልዩ ናቸዉ። ገብረሃና ባልቻ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ በትህነግ መንገድ ሳይሆን በራሱ መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ህዝብ መድረስ አለበት፤ ብለዋል። የሰውን ልጅ በረሃብ፣ በመድሐኒት እጥረት እንዲሞት መፍረድ የጭካኔ ጥግ ነው። ሁሉም የዘራትን ያጭዳል፤ ሲሉ ጴጥሮስ ጴጥሮስ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። 
በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚቀመጡ አስተያየቶች እጅግ ለሚዲያ የማይመጥኑ፤ ከአስተማሪነታቸዉ ይልቅ የሰዉን ክብር የሚነኩ ፤ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ የሚያጋጩ ፤ የጥላቻ ንግግሮች በመሆናቸዉ አሳዛኝ ከሁሉም በላይ ደግሞ አሳሳቢ ያደርገዋል። በሦስት ርዕሶች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን መርጠን እና ጨምቀን ያቀረብንበት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት ለማዳመጥ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

Äthiopien l Funktionsunfähige ATM Automaten in Mekele, Tigray
ምስል Million Haileselassie/DW

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ