1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታሳሪዎች እና የእስረኞች ቦታ መለዋወጥ

ዓርብ፣ ኅዳር 7 2011

በበፍቃዱ ኃይሉ:- የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንበረ ሥልጣኑን ከመቆጣጠራቸው በፊት ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ሌሎች የአሁን ባለሥልጣናትን ጨምሮ እርሳቸውም ላይ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው እንደነበር ከዚህ ቀደም ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ነገሮች ቀስ በቀስ እየተለወጡ፣ የቀድሞ ታሳሪዎች አዳዲሶቹ አሳሪዎች እየሆኑ መጥተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/38Ovd
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

የቀድሞው እስረኛ ብ/ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እና የፖለቲካ ስደተኛ የነበሩት ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ የጦር ባለሙያዎች ኦሮምያ እና አማራ ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ሆነው በቅርቡ ተሾመዋል፡፡ ሜ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በሙስና ተጠርጥረው ሲታሰሩ፣ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምሥጢራዊ የበላይ መሪ «ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ሰኔ 16፣ 2010 የተሞከረውን የግድያ ሴራ በማቀነባበር ተጠርጥረዋል»፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ነገሮች እንዳልነበሩ ሆነው ኢሕአዴግ ሳይቀየር የገነባው ስርዓት በመቀየሩ ፊተኞች ኋለኞች ሆነዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አይደፈሬ የነበሩት የፀጥታ ክፍሉ ሠራተኞች እና የሚቴክ መሪዎች በዚህ ሳምንት ለእስር ሲዳረጉ፣ አዲስ አበባ በዳግም ግርምት ተመልክታለች፡፡

አለቀ ሲባል እያደር የሚያገረሸው «የሽግግር» ወቅቱ የሰበር ዜና ጋጋታ የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን መሠረት ካደረገው ያለፈው ወር ሹመት ቀጥሎ በቀላሉ የማይበርድ አነጋጋሪ የእስር ዜና አስከትሎ መጥቷል፡፡ በለውጡ አፍላ ዕድሜ ላይ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ የሚለው ዜና ሲነገር በደስታ ጮቤ የረገጡ ሰዎች፣ አዳዲሶቹ ተጠርጣሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ሲሰሙ በተመሳሳይ የደስታ ስሜት ፈንጥዘዋል፡፡

ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ የለውጥ ሒደቱ የጀመረ ሰሞን፣ ብዙኃን የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ቢያስደስታቸውም፣ ለደረሰው ሰብኣዊ ቀውስ ግን ካሣው ቢቀር ሕጋዊ ተጠያቂነት መኖር አለበት የሚል አቤቱታ ነበራቸው፡፡ ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነቢብ ብዙ ጊዜ በፍቅር እና ይቅርታ የተቃኘ ስለነበር፣ የመብት ጣሾቹ ከነበደላቸው ከፍትሕ ሊያመልጡ ነው የሚል ቁጭት በብዙዎች ውስጥ ነበር፡፡ ይህ ቁጭት በተለያየ ጊዜ በባለሥልጣናት ላይ የደቦ ፍርድ እስከማነሳሳት የደረሰ ቁጭት ነው፡፡ ቁጭቱ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ብዙ የመንግሥት ተቋማት ያለ ይሉኝታ በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፉ፣ ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከዓመት ዓመት በጀታቸው እያለቀ ነገር ግን ውጤታቸውን ሳይመለከት የቆየው ሕዝብ እና ታዛቢ፣ የይቅርታው ትርክት ለአዳዲሶቹ እና ለመጪዎቹ ባለሥልጣናት ሳይቀር መጥፎ ምሳሌ ይሆናል የሚል ስጋት ነበራቸው፤ የመንግሥት ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ቀርተው ያለ ተጠያቂነት በይቅርታ ማለፍ ካሁኑ ይልቅ ለወደፊቱ አሳሳቢ ነው፡፡

የዚህን እስር እርምጃ አንድምታ በተለያየ መንገድ የተረዱት ሰዎች አሉት፡፡ አንዳንዶች በይቅርታ ሥም ተድበስብሶ ሊቀር የነበረው የፍትሕ ጉዳይ መልስ የሚያገኝበት በር እንደተከፈተ ሲመለከቱ፣ ሌሎች ደግሞ የቀድሞዎቹ የፖለቲካ ልኂቃን የፖለቲካ ሥልጣናቸውን እንዲያጡ ከተደረገ በኋላ የኢኮኖሚ አስኳላቸውም እንደተሰበረ አድርገው የወሰዱትም አሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመጡ ወዲህ የደኅንነት እና ፀጥታ ማስከበር አቅማቸው ደክሟል፣ የኃይል የበላይነት ከመንግሥት እጅ ወጥቷል፣ ስርዓት-አልበኝነት ሊሰፍን ይችላል ብለው እየሰጉ ባሉበት ሊያመልጡ ያሰቡ ጉምቱ የቀድሞ ሠራዊት አባል ሳይቀሩ ታድነው መያዛቸው የደኅንነቱ እና ፀጥታ አስከባሪው አካል መልሶ አቅም አግኝቷል ማለት ነው የሚል እፎይታ ሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ሜ/ጄኔራል ክንፈ የተያዙት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደመሆኑ፣ ከዚህ በፊት የታየው እና የትግራይ ክልል ከፌዴራል ክልሉ የለውጥ እርምጃዎች ያፈነገጡ አካሔዶች ታርመዋል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል፤ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ከእስሩ ዜና በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ጭላንጭል ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ቀደም የሙስና እስሮችን በተመለከተ የሚሰማው ቅሬታ በመረራ ጉዲና (ዶ/ር) ቋንቋ «አሳ ነባሪዎቹን ትቶ ትንንሾቹን አሳዎች» በማጥመድ ላይ ያተኮረ ነበር፤ በተጨማሪም፣ በአምና የፖለቲካ እስረኞች ፍቺ ወቅት እንደተነገረን፣ ከዚህ በፊት የነበሩት የሙስና እስሮች በገዢው ቡድን ውስጥ የተለየ አስተሳሰብ ያራመዱትን ሰዎች መምቻ እንደነበር ነው፡፡ የአሁኑ ግን ለመስማት በሚያሳፍር ሁኔታ የተመዘበሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መሪዎች እና ከጥቂት ወራት በፊት አይደፈሬ የነበሩ ባለሥልጣናት በመታሰራቸው ቅሬታው እምብዛም ጎልቶ አልተደመጠም፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ግን አሉ፡፡ ቅሬታዎቹ የሚቀርቡት በሁለት ጎን ነው፡፡ አንዱ ወገን ‹ሥልጣንን ተገን አድርገው የሕዝብ ንብረት የመዘበሩት እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ገና ሌሎችም በርካታ የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ ከሁሉም የኢሕአዴግ ግንባር አባላት መካከል ለፍርድ መቅረብ አለባቸው› የሚሉት ወገን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ‹ይህም ሌላ የፖለቲካ ድራማ ነው፤ ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ልዩነት ሲኖር ተሸናፊው ቡድን እንደሚታሰረው ነው አሁንም ተሸናፊዎች ተጠርጥረዋል ተብለው የሚታሰሩት› ይላሉ፡፡ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩት እና ከገዢው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉት ብዙኃን መገናኛዎች ነገሩን ከስር ከስር እየተከታተሉ ማራገባቸው እና ያራገቡበት መንገድ ከዚህ በፊት የፖለቲካ እስሮች ሲፈፀሙ ከሚያደርጉበት መንገድ ጋር መመሳሰሉ ደግሞ ጉዳዩን ‹ሌላ የፖለቲካ ድራማ ነው› ብለው ለሚከራከሩት ማጠናከሪያ ሆኖላቸዋል፡፡

የሆነ ሆኖ አጋጣሚው አዲሱን የኢትዮጵያ አመራር ቡድን ለመፈተሽ መልካም አጋጣሚ ይሆናል፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች በነጻ፣ ፍትሐዊ እና ቀልጣፋ የምርመራ ብሎም የፍትሕ ሒደት አልፈው ፍርድ ያገኛሉ፣ ወይስ እንደቀድሞ የፖለቲካ እስሮች እና እስረኞች የመብት ጥሰቶች፣ የፍርድ ሒደት መጓተቶች፣ ግልጽነት የሚጎድላቸው እና አድሎአዊ ፍርዶች ይስተዋሉባቸው ይሆን? ጊዜ ለሁሉም መልስ ይሰጣል፡፡

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

ነጋሽ መሐመድ

መርጋ ዮናስ