1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር መቋጫ ሊያገኝ ይሆን?

ሐሙስ፣ ጥር 7 2012

በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ባደረጉት ውይይት "ጠቃሚ ውጤቶችና ትርጉም ያላቸው ምዕራፎች" ላይ መድረሳቸውን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ኦስማን አብደል ኻሊክ እንደሚሉት ሶስቱ አገሮች በመጨረሻው ሥምምነት ላይ ለመወያየት የሚገናኙባቸው ቀናት "ወሳኝ" ናቸው

https://p.dw.com/p/3WHX8
Karte Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre EN

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና የሥራ ክዋኔ ሥምምነት ላይ ለመወያየት ከሁለት ሳምንታት በኋላ በዋሽንግተን ለመገናኘት ተስማሙ። ግድቡ በሐምሌ እና በነሐሴ እንደ ሁኔታው በመስከረም በውኃ እንዲሞላ መስማማታቸውን የሶስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ እና የውኃና መስኖ ምኒስትሮች የዓለም ባንክ እና የአሜሪካ ታዛቢዎች በተገኙበት ለሶስት ቀናት ካደረጉት ውይይት በኋላ ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል። 

ሶስቱ አገሮች ለረዥም አመታት በተወዛገቡበት የታላቁ የኅዳሴ ግድብ አሞላል እና አስተዳደር ጉዳይ ከአንዳች ሥምምነት ለመድረስ የተቃረቡ ይመስላል። 
የታላቁ የኅዳሴ ግድብን የውኃ አሞላል እና የሥራ ክዋኔ የተመለከተ አጠቃላይ ሥምምነት ላይ ለመወያየት ከሁለት ሳምንት በኋላ በዚያው በዋሽንግተን ዲሲ ይገናኛሉ። እስከዚያው በቴክኒካዊ እና ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ በሶስቱ አገሮች መካከል ውይይት ይደረጋል።

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ በውይይቱ "ጠቃሚ ውጤቶች እና ትርጉም ያላቸው ምዕራፎች" ላይ ደርሰናል ብለዋል። 
በአሜሪካ ግምዣ ቤት ድረ-ገጽ በኩል ይፋ በሆነው የጋራ መግለጫ ሶስቱ አገሮች ታላቁ የኅዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚገኙ የውኃ ግድቦችን ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ ምዕራፎች ለመሙላት መስማማታቸውን ገልጸዋል። ይህ በወንዙ ይዞታ እና በሱዳን እና በግብጽ የሚገኙ ግድቦች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ ይሆናል። 

በሶስቱ አገራት ሥምምነት መሠረት ግድቡ ውኃ የሚሞላው በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ይሆናል። በሐምሌ የሚጀመረው ግድቡን በውኃ የመሙላት ሒደት እንደ ሁኔታው እስከ መስከረም ሊዘልቅ ይችላል። 

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ መጠን ከባሕር ጠለል በላይ 595 ሜትር እስኪደርስ እና ለመጀመሪያ ደረጃ የኃይል ማመንጨት እስኪበቃ በመጀመሪያው ምዕራፍ ውኃ እንዲሞላ መስማማታቸውን ሶስቱ አገሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠቁመዋል። በዚህ ምዕራፍ ግድቡ በውኃ ሲሞላ አስከፊ ድርቅ ቢከሰት ግብፅ እና ሱዳን መቋቋም የሚችሉበት መንገድ ሊዘጋጅ ይገባል ተብሏል። 

ግድቡ ውኃ የሚሞላባቸው ቀጣይ ምዕራፎች በተጨማሪ ሥምምነቶች የሚወሰን ይሆናል። ይኸ ያለ ውጤት በተበተነው የአዲስ አበባው ድርድር በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል መሠረታዊ ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። በአዲስ አበባው ድርድር የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ከ12 እስከ 21 አመታት እንዲቆይ ግብፅ ጠይቃ ነበር። የግብፅን ጥያቄ ግን የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ "በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም" ሲሉ ውድቅ አድርገዋል። 

BG Grand Renaissance Dam | Standort des Grand Ethiopian Renaissance Damms (2013)
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Asmare

ሶስቱ አገሮች በዋሽንግተን የደረሱበት ሥምምነት የመጨረሻ አይደለም። የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ የስምምነቱ "ውጤቶች ወደ ሕግጋት እና መመሪያዎች ይቀየራሉ" ብለዋል። 
በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ኦስማን አብደል ኻሊክ በበኩላቸው ሶስቱ አገሮች በመጨረሻው ሥምምነት ላይ ለመወያየት የሚገናኙባቸው ጥር 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም.  "ወሳኝ" ናቸው ብለዋል። 

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለጉብኝት ወደ ደቡብ አፍሪካ ባቀኑበት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ኢትዮጵያ እና ግብፅን እንዲያደራድሩ መጠየቃቸው አገራቸው ከዋሽንግተኑ ድርድር ገሸሽ የማለት አዝማሚያ እያሳየች ነው የሚል ጥቆማ ሰጥቶ ነበር። በየካቲት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነትን የሚረከቡት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያና ግብፅን ለማደራደር የቀረበላቸውን ጥያቄ በአዎንታ የተቀበሉ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከግብፁ አቻቸው መወያየታቸውንም ገልጸው ነበር። አሁን ድርድሩ ባለበት ደረጃ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል ባይታወቅም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ከሚያደርጉት ሌላ የዋሽንግተን ውይይት በኋላ ጉዳዩ መልስ ያገኛል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ