1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቲምቡክቱ ሥመ-ጥር ልሒቅ፦አሕመድ ባባ

ሐሙስ፣ ሰኔ 28 2010

በሰሜናዊ ማሊ የምትገኘው ቲምቡክቱ በአንድ ወቅት በነበራት ሐብት ሥመ-ጥር ነበረች።  ከሰሐራ በርሐ ጠርዝ የምትገኘው ከተማ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእስላማዊ ትምህርት የከበረ ስም የተቸራት በንግድ ግንኙነትም የደመቀች ነበረች። ለቲምቡክቱ ዝና የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ካበረከቱ መካከል አፍሪካዊው ታላቅ ምሁር አሕመድ ባባ አንዱ ናቸው። #ARAMH

https://p.dw.com/p/30uVj
frican Roots Ahmed Baba
ምስል Comic Republic

አሕመድ ባባ

“የተከበሩ አሕመድ ባባ እኛ የቱት ነዋሪዎች እና የቲምቡክቱ ታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች ስለ ባርነት ያለንን ጥያቄ ያብራሩልን ዘንድ እንሻለን። ጥቁር አፍሪቃውያን በተፈጥሯቸው ባሮች ስለመሆናቸው ማወቅ እንሻለን። ወይስ ዕምነታቸውን ወደ እስልምና ከቀየሩ በኋላ ነፃ ሊሆኑ ይገባልን? በዚህ ጥያቄ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? ምሥጋናችን ላቅ ያለ ነው። …”
አሕመድ ባባ ይኸ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ዘመኑ የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ነበር።  ምሁሩ በ1556 ዓ.ም. ሳይሆን አይቀርም በተወለዱባት እና በሰሜናዊ ማሊ በምትገኘው ቲምቡክቱ ይኖሩ ነበር። የከተማዋ የብልፅግና መሠረት በምዕራብ አፍሪቃ የከበረ ስም የተሰጣቸው እስላማዊ ዩኒቨርሲቲዎቿ እና ባርነትን የሚጨምረው የንግድ እንቅስቃሴዋ ነበሩ። አሕመድ ባባ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ታዲያ የእስልምና ሐይማኖትን መሰረት አድርገው በፈትዋ መልክ ነበር። 
በርናርድ ሳልቫን ጡረታ የወጡ የታሪክ ፕሮፌሰር ናቸው። የማሊን ጥንታዊ ጽሁፎች እና ባሕል በጥልቀት የመረመሩት ሳልቫ ይዘቶቻቸውን እንዲህ ያብራራሉ።

DW Videostill Projekt African Roots | Ahmed Baba, Mali
ምስል Comic Republic

“አንድ ሰው ከየትም ይምጣ ከየት፤ ጥቁርም ይሁን ነጭ የዘር ጉዳይ ሳይሆን ባርነት ሕጋዊ የሚሆነው የእስልምና እምነት ተከታይ ላልሆኑ ሰዎች ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ብዙዎች ጥቁር ሰዎች በተፈጥሯቸው ባሪያ እና እምነት የለሽ ናቸው የሚል በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ ድምዳሜ እንደነበራቸው መታወቅ አለበት። ከዚህ አኳያ የአሕመድ ባባ ምላሽ እንደ አዲስ አተያይ ሊወሰድ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ምላሻቸው በእስልምና ሕግጋት መሠረት በጂሐድ ወቅት የሐይማኖት የለሾችን በባርነት መያዝ ሕጋዊ ያደርጋል። 

ከባርነት ባሻገር አሕመድ ባባ ሞሮኮዎች ከተማቸውን መገንጠላቸውን ተቃውመዋል። ግንቦት 30 ቀን 1591 ዓ.ም. ቲምቡክቱ በሞሮኮው ሱልጣን አሕመድ አል-ማንሱር እጅ ሥር ወደቀች።  

አሕመድ ባባ እና ሌሎች በርካታ ልሒቃን እጆቻቸው በሰንሰለት ታስሮ ወደ ሞሮኮ ተወሰዱ። ለበርካታ ወራት በእስር ቤት በእስር ቤት ከቆዩ በኋላ በማራካሽ ለቁም እስር ተዳረጉ። በእውቀታቸው የተደነቁት የሞሮኮ ሱልጣን እንዲያስተምሩ ፈቀዱላቸው። ዝናቸውም በማግረብ ቀጣና ሁሉ ናኘ። ኪፋያት አል-ሙኽታጅ የተባለውን ሥመ-ጥር የጽሁፍ ሥራቸውን ያጠናቀቁት በስደት በነበሩት በዚህ ወቅት ነበር። ይኽ ስራቸው በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እና አሕመድ ባባ በኖሩበት ዘመን የኖሩ ታላላቅ ምሁራንን የሕይወት ታሪኮች የተመለከቱ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ጽሁፎች ተካተውበታል። 

frican Roots Ahmed Baba
ምስል Comic Republic

“ለታሪክ አጥኚዎች በእርግጥ የዘመኑን ልሒቃን ታሪክ ለማወቅ እጅግ ጠቃሚ ምንጭ ነው። ሁለተኛው ነገር እነዚህ አብዛኞቹ የማግረብ እና የስፔን ልሒቃን ናቸው። በሜድትራኒያን የእስልምና ባሕል እና የቲምቡክቱ የእስልምና ልሒቃን ባሕል መካከል ያለውን ተከታታይነት ይጠቁማል። በሜድትራኒያን የእስልምና ዓለም ሁለቱ እጅግ የተቆራኙ ናቸው” 

አሕመድ ባባ ወደ ትውልድ አገራቸው ይመለሱ ዘንድ የተፈቀደላቸው ከሱልጣን አሕመድ አል-ማንሱር ሞት በኋላ ነበር። በ1627 ዓ.ም. በ71 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በሕጋዊ ጉዳዮች፣ ሐይማኖታዊ ተግባራት፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶች የአረብኛ ቋንቋ ሰዋስው እና ትምህርትን የተመለከቱ ከስድሳ በላይ ፅሁፎቻቸውን ትተው አልፈዋል። ዛሬ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች በአሕመድ ባባ ማዕከል ወደሚገኘው የከፍተኛ ትምህርት እና እስላማዊ ጥናት ተቋም ተጉዘው ቅጂዎቻቸውን መመልከት እና ማድነቅ ይችላሉ። 

“በዛሬዋ ማሊ ብሔራዊ ተምሳሌት ሆነዋል። አሕመድ ባባ እና ዘመናቸው የቲምቡክቱ ታላቅነት ማብቂያን ይወክላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ከየትም ይምጡ ከየት የቆዳ ቀለማቸው ነችም ይሁን ጥቁር ሁሉም አማኒያን በፈጣሪ ፊት እኩል ለመሆናቸው አፅንዖት ሲሰጡ ለእኛ ይቀርባሉ። ከዚያ ባሻገር ከአገራቸው ለመባረር ያበቃቸው ለወረራ አሻፈረኝ ማለታቸውም አለ”   

በዛሬዋ ማሊ አሕመድ ባባ ነፃ አሳቢ እና አማጺ ልሒቅ ተደርገው ይታወሳሉ። ዝናቸው ግን በምዕራብ አፍሪቃ ብቻ የተገደበ አይደለም። በሜርኩሪ ፕላኔት ላይ ጭምር በስማቸው የተሰየመ የእሳተ ገሞራ ይገኛል። 

ኮንስታንዝ ፊሸር/እሸቴ በቀለ

አርያም ተሌ 

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.