1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ድሮን ለኢትዮጵያ ማቅረቧን ባስቸኳይ እንድታቆም ተጠየቀች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2016

በኢትዮጵያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ያሉት የሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ጥቃት በእጅጉ ያሳስባቸው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅቶች ለተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ መንግስት አቤቱታ ማስገባታቸውን ዐስታወቁ ።

https://p.dw.com/p/4a9ls
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፤ ዱባይምስል Kamran Jebreili/AP Photo/picture alliance

አሳሳቢው የሰላማዊ ሰዎች የድሮን ጥቃት

በኢትዮጵያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ያሉት የሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ጥቃት በእጅጉ ያሳስባቸው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅቶች ለተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ  መንግስት አቤቱታ ማስገባታቸውን ዐስታወቁ ። ድርጅቶቹ በዚሁ ደብዳቤያቸው፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬተስ መንግስት፣ በኢትዮጵያ ባለው ቀውስ የድሮን አቅርቦትን በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጠይቀዋል ።

አሳሳቢው የሰላማዊ ሰዎች የድሮን ጥቃት

በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ጦርነቶች፣ የጦርነቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰላማዊ ሰዎች፣ በድሮን ጥቃት አየተገደሉ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ እየተዘገበ ይገኛል ።

 የጋራ ፊርማችውን በማኖር ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ደብዳቤ ያስገቡት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሲቪክ ድርጅቶች፤ ይኸው በሰው አልባ አውሮፕላኖች በንጹሐን ዜጎች ላይ የቀጠለው ጥቃት በጥልቀት አሳስቧቸዋል።

ስለሆነም በኢትዮጵያ በሚካሄዱት ግጭቶች፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ መንግስት፣ የድሮን አቅርቦትን በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጠይቀዋል። ደብዳቤውን ካስገቡት ድርጅቶች መኻከል፣ የአሜሪካ ኢትዮጵያ የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተገኑን አነጋግረናቸዋል።

«ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ያስፈለገበት ምክንያት፣ የዚህ ሰው አልባ አውሮፕላን ወይንም ድሮን ያቀርባል ተብሎ የሚታወቀው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ መንግስት ነው። ይህ መንግስት ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለው ወዳጅነት መቀጠሉ ጠቃሚ ሆኖ ብናገኘውም፣ግን በዚሁ ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የድሮን መሣሪያ በማቀበል ብዙ ሰላማዊ ሰዎች ማስገደል ተግባር እያካሄዱ እንደሆነ ለማሳሰብ ነው ።»

የኢትዮ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማኀበራዊ ድጋፍ/ኤክናስ/መስራች የሆኑት አቶ መቆያ ወንድይራድ በበኩላቸው፣ በድርጅታቸው በኩል የተያዘውን አቋም አስመልክቶ ሲናገሩ የሚከተለው ብለዋል።

«በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ባስቀመጠው የጄኔቫ ኮንቬንሽን፣አንቀጽ 10 እስከ 16 ባሉት አንቀጾችን መሰረት፣ሰላማዊ ሕዝብ ፣ሰብል በማጥፋት፣የውሃ ግድቦች በማጥፋት፣ውሃ ሰው የሚጠጣባቸው ሥፍራዎች፣ወንዞች በቦምብ መምታት፣ በአለም አቀፍ ህግ በጣም በጣም የተከለከለ ስለሆነ፣ ይህንን ህግ ጠቅሰን እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለሀገራችን መንግስት የሚሸጡትን ወይም የሚሰጡትን መንግስታት ለማሳወቅ ነው።»

ከ100 በላይ የድሮን ጥቃቶች

ማኀበራቱ በዚሁ ደብዳቤያቸው፣ በዐማራ ክልል ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግና ህገ መንግስታዊ መብቶችን በማገድ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለአደጋ እንዲጋለጥ አድርጓል በማለት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማኀበራዊ ድጋፍ/ኤክናስ/መስራች የሆኑት አቶ መቆያ ወንድይራድ በበኩላቸው፣ በድርጅታቸው በኩል የተያዘውን አቋም አስመልክቶ ሲናገሩ የሚከተለው ብለዋል።

ከክልሉ አሳሳቢ የሆኑ ሪፖርቶች እየወጡ ነው ያሉት ድርጅቶቹ፣በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እና ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀምን የመሳሰሉ ግፎች እንደሚፈጽሙ ጠቁመዋል።

በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ከ100 በላይ የሚሆኑ የድሮን ጥቃቶች ሪፖርት መደረጋቸውን አስታውቀዋል። በመሆኑም፣ከእነዚህ አሳሳቢ ሁኔታዎች አንጻር፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ወታደራዊ ግንኙነት እንደገና እንዲመረምር በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።

የኒውዮርክ ኒውጀርሲ ተስፋ ለኢትዮጵያውያን ድርጅት፣ የኢትዮ አሜሪካዊያን የልማት ምክር ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያውያን የሕዝብ ዲፕሎማሲ ኔትወርክ የተባሉት ድርጅቶች በዚሁ ደብዳቤ የተካተቱ ናቸው።

ኢታማዦር ሹሙ ስለድሮን ጥቃት

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ይሁንና፣ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰሞኑን ለፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ፣የድሮን ጥቃትን አስመልክቶ ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ (በስተግራ የሚታዩት) ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Thomas Mukoya/REUTERS

«ድሮን እኮ የተሰራው ለጦርነት ነው፣ ለውጊያ ነው የተሰራው፣ የገዛነው ልንዋጋበት ነው እንጂ ድሮን አለን እያልን በሚዲያ ልንገልጸው አይደለም። የጦር መሣሪያ ነው ልክ እንደክላሽ፣ ክላሽ  የአቅሙን ይሠራል፤ ሌላው የአቅሙን ይሰራል። ድሮንም የራሱን ስራ ይሰራል። ድሮን እኛ የምንጠቀመው ለስብስብ ዒላማ ነው። በወታደራዊ አባባል ስብስብ ዒላማ የሚባል ነገር አለ። ስብስብ ዒላማ ማለት፣ የጠላት ጠንካራ ቋጠሮ ማለት ነው። የጽንፈኛ ስብስብ ስናገኝ እንመታለን በድሮን።»

 የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጠራው ምስክርነት የኢትዮጵያ ድሮን ጥቃት አጀንዳ ተነስቶ ነበር።

በዚሁ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ወደ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በመጓዝ፣ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለኢትዮጵያ መሰጠቱ አሜሪካን እንደሚያሳስባት፣ድሮኖቹም በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ እያወሳሰቡ ስለመሆኑ ስጋታቸውን እንደገለጹ ለምክር ቤቱ አባላት መናገራቸው አይዘነጋም።

ታሪኩ ኃይሉ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ