1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጥሪ ከኢትዮጵያውያን አንጻር

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8 2014

«ችግሩ ጋዜጠኛ ሙያዊ መሆኑን ለይቶ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ጋዜጠኛም ሀኪምም ካጠፋ በህግ ይጠየቃል፡፡ አሁን በህግ ለምን ተጠየቁ ነው ወይስ ሂደቱን እና አያያዙን ነው የምንተቸው፡፡ የአያያዙን ግልፅ አለመሆን ከሆነ ትክክለኛ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ መጠየቅ የለባቸውም ፤እኛ ነን የምናውቀው ከሆነ ግን ፍትህ እምን ይግባ? ማስተዋል!»

https://p.dw.com/p/44OSe
Bildkombo Äthiopien | Eyasped Tesfaye Meaza Mohammed Tamrat Negera
ምስል privat

ኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኞች እስራት እየጨመረ መምጣቱ ፣የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ስለጠራው እንዲሁም  ቱርክ ከአፍሪቃውያን ጋር የትብብር ጉባኤ ስለማካሄዷ ላይ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ያሰባሰበው የዕለቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን ተጀምሯል። መልካም ቆይታ

በኢትዮጵያ ባሳለፍነው አንድ ሳምንት ውስጥ ለሀገር ውስጥ እና የውጭ የመገናኛ ብዙኃን የሚዘግቡ 6 ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከትናንት በስትያ ረቡዕ« ከሽብር ቡድን » ግንኙነት ፈጥራችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ 3  ጋዜጠኞችን ጨምሮ በተለያዩ የዩትዩብ ቻናሎች ይሰሩ እንደነበር የተነገረላቸው ጋዜጠኞቹ የሰሞንኛ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ አድርጓል። አስቀድመው በቁጥጥር ስር የዋሉት 3 ጋዜጠኞች የት እንዳሉ አለመታወቁ  ደግሞ በመንግስት ላይ ትችት ከማስከተላቸውም በላይ ዓለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተጋቹ ሲፒጄን ጨምሮ መንግስት ጋዜጠኞችን በአስቸኳይ እንዲፈታ ጥሪ እያደረገጉ ነው።  የጋዜጠኞቹን መታሰር እና ሀገሪቱ አሁን ከምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ተቃኝተው የተንሸራሸሩ ሃሳቦች በርካታ ቢሆኑም ጥቂቶቹን እንዲህ ተመልክተናል።

አስፋው ትራሶ ባሰፈሩት መልዕክት «የጋዜጠኝነት ነፃነት መብት ይጠበቅ እንደምትሉ ሁሉ ጋዜጠኞችም የሀገረና የሕዝብን የፍትህና የነፃነት መብትን መጠበቅ አለባቸው ። የሀገርንና የሕዝቧን መብት የሚጥስ ዘገባ ከሰሩ የማይጠያቁበት ምክንያት የለም ። ትክክለኛ ሥራ እየሠሩ ቢያዙ የሰሩት እውነት ነፃ ያወጣቸዋል። የሌላውን መብት ሰይጣብቁ የራሳቸውን መብት መጠየቅ ሚዛን ያጣ ጥያቄ ይመስለኛል። ስህተት ለሠሩ ጋዜጠኞች መብት እቆማለሁ የሚለው ድርጅት ከለም ያ ድርጅት ራሱ መጠየቅ አለበት።» አለበት በማለት ጽፈዋል።

የሺ ሴቤሆ ደግሞ የጋዜጠኞቹ አድራሻ አለመታወቁን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት « ማንስ ቢሆን እንዴት መንግሥት በቁጥጥር ሥር ያዋለው ሰው አድራሻ ይደብቃል? ሰለእስራቸው መረጃ ከሌለው ዜጎቹን ማፈላለግ አለበት» ብለዋል።

ዮናታን ይመኑ በበኩላቸው «ጋዜጠኝነት ከሀገር በታች ነው ጠቅላይ ሚኒስተሩንም ቢሆን የሚገዛቸው ህግ ተሰንዶ የተቀመጠ ሀቅ ነው።» ሲሉ ድርጊቱን ከህግ አንጻር ለማየታቸው የገለጹበት ሃሳብ አስፍረዋል።

ኩካ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ ደግሞ  «ሚዲያ ላይ የጻፈ ሁሉ ...ለሀገር አለመረጋጋት አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሁሉ...ውሸትን ለህዝብ የሚያሰራጭ ሁሉ...እንደ ጋዜጠኛ ተቆጥሮ መብቱ መብቱ ከተባለለትማ ..ቅድሚያ የህግ ማስከበር ስራ ከማህበሩና ከአጥፊዎቹ ሊጀምር ይገባል። CPJም...እስኪ እነ CNN ጋ ሄዶ የጋዜጠኝነት ስነምግባር ጥሳችሃል ይበልልን።» ሲሉ ሌሎች ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ለመተቸት የሞከሩበትን ሃሳብ አስፍረዋል።

ደረጀ መኮንን ደግሞ እንዲህ ይላሉ «ችግሩ ጋዜጠኛ ሙያዊ መሆኑን ለይቶ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ጋዜጠኛም ሀኪምም ካጠፋ በህግ ይጠየቃል፡፡ አሁን በህግ ለምን ተጠየቁ ነው ወይስ ሂደቱን እና አያያዙን ነው የምንተቸው፡፡ የአያያዙን ግልፅ አለመሆን ከሆነ ትክክለኛ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ መጠየቅ የለባቸውም ፤እኛ ነን የምናውቀው ከሆነ ግን. ፍትህ እምን ይግባ? ማስተዋል!ማስተዋል!» ብለዋል።

መንጌ ኒው የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው «ሁሉም ነገር ከሀገር እና ከህዝብ ጥቅም በታች መሆኑን ዘንግተውት ነው ለሚከፈላቸው ደመወዝ ብለው የሀገርን ጥቅም የሚጻረር ዘገባ ላይ የተጠመዱት?» በማለት ይጠይቃሉ።

መኮንን ኃይሌ « ጋዜጠኝነት በእንደነዚህ አይነት ሰዎች ከታየ እጅግ የሙያውን ክብር ማሳነስ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት ገንዘብ ለሰጠህ ሁሉ መዋሸት ከሆነ ትልቅ ቅሌት ነው፡፡ የምትጠላውን ሰው መስደብ ጋዜጠኝነት ከሆነም በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ የታሰሩትም ገዜጠኝነትን የሚመጠን ሚዛናዊ ዘገባ ባለ ማቅረባቸው ነው፡፡» በማለት ወቀሳ አዘል አስተያየት አኑረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ ላይ ለመነጋገር አዲስ የጠራዉን ስብሰባ ኢትዮጵያ ተቃወመች።ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ዳግም እንዲነጋገር የጠየቀዉ የአዉሮጳ ሕብረት ነዉ።ሕብረቱ ለምክር ቤቱ ያቀረበዉ ረቂቅ ደንብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚዋጉ ወገኖች በሙሉ በሠላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሱት የሰብአዊ ምብት ረገጣና ግፍ በገለተኛ ወገን እንዲጣራ ይጠይቃል። ምክር ቤቱ ለዛሬ በጠራው ይህንኑ ስብሰባ በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች ሲንሸራሸሩ ተስተውለዋል።

Bildgalerie 50 Jahre Römische Verträge I Frankreich: Europäisches Parlament, Straßburg
ምስል Daniel Kalker/picture alliance

ኑርሜካ አህመድ « አለም አቀፍ ተቋማት ብለን የምናቆለጳጵሰው የትኛውም ተቋም የምዕራባውያን እና የአሜሪካን ተላላኪዎችን ለማዳን ነው ጥረታቸው ። ስለዚህ የትኛውም ጥቁር ህዝብ ለራሱ ህልውና አስቦ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማውገዝ አለበት።» ሲሉ ፤ እንግዳኀት ከበደ በበኩላቸው

«እነ የመንና ሶርያ በእርስ በእርስ ጦርነት 10 ዓመት ሞላቸው!! እና ለእነዚህና ተመሳሳይ አይነት ሁኔታ ላይ ላሉ ሃገሮች የሚከናወኑ ጥፋቶችን ምነው ለማስቆም አልቻሉም ነው ወይስ ሌላ ፕላኔት ላይ ነው ያሉት?» በማለት ይጠይቃሉ።

Bildgalerie 50 Jahre Römische Verträge I Frankreich: Europäisches Parlament, Straßburg
ምስል Daniel Kalker/picture alliance

አዲሳለም አየለ « የኢትዮጵያ ጉደይ በእግዚአብሔር እጅ ነው እንጂ በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓውያን እጅ አይደለም ። ከእነሱ ከጠበቅነው ግማሹ ያቀዘቅዛል ግማሹ ያሞቃል ፤ ሁሉ አይተናል ። ኢትዮጵያንም ብሆኑም ሁሉ እኔ ልክ ነኝ ይላሉ ተሳስቻለሁ ሁሉ ነገር ከአገር አይብለጥም ለዜጎች ስል እተወዋለሁ የሚል አካል አጣው ። ግን አንድ ነገር አውቃለሁ እሱም እግዚአብሔር እውነተኛ ፈራጅ  ነው ። ኢትዮጵያ ህዘብ ሆይ የፈለገው ይበሉ እናንተ ግን ወደ እግዚአብሔር ጩኽ ። ማንንም ልክ ነህ አትበሉ። በእውነቱ እርሱ ይፈርድ » ሲሉ ለሀገሪቱ ከምድራዊ መፍትሄ ይልቅ ሰማያዊውን ያሹበትን መልዕክታቸውን አኑረዋል።

ፋንታዬ ታደሰ በበኩላቸው ፍላጓታችሁ በሙሉ ማባባስ እና የሰውን እልቂት ነው:: ጥፋተኛውን እንደ ተበዳይ፤ የተጎዳውን የግፍ ሰለባ የሆነውን ደግሞ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሁለተናዊ ድጋፍ ታደርጋላችሁ ::አሸባሪን ከመንግስት እኩል እውቅና ትሰጣላችሁ እንዴት ሰላም ይመጣል?» ሲሉ

ኦብሲ ሪቂቸ ጂሬኛቲ በበኩላቸው «ጦርነቱን እያባባሱ ያሉት የአውሮጳ ሕብረት እና የአሜሪካ አመራሮች መሆናቸን መዘንጋት የለባችሁም።» በማለት ምዕራባውያኑን የወቀሱበትን ሃሳብ አስፍረዋል።

ዜድ ዘላሊበላ በሚል ስም የሰፈረ ሃሳብ ደግሞኢትዮጵያ ምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ናት እንደ ግን?? ነው ወይስ ሳናውቅ ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አውሮፓ ውስጥ ተገኘች ?» በማለት የህብረቱን ጥያቄ በስላቅ ነቆር አድርገዋል።

ለሁለት ቀናት በሚዘልቀው የቱርክ አፍሪቃ ትብብር ጉባኤ ቱርክ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ከፍ እንደምታደርገው ተገለጸ። ከነገ ዐርብ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ድረስ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ በሚካኼደው ጉባኤ የ39 ሃገራት ሚንሥትሮች እና 13 ፕሬዚዳንቶች ለመሳተፍ ከወዲሁ ማረጋገጫ ልከዋል።ቱርክ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለይ በደኅንነቱ ዘርፍ ይበልጥ ከፍ ማድረግ እንደምትሻ እና አፍሪቃውያን ሃገራትም ከቱርክ ወታደራዊ የጦር መሣሪያዎችን የመግዛት ፍላጎታቸው መጨመሩ ተገልጧል። የቱርክ አፍሪቃ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍን የተመለከቱ አንዳንዶች ባሰፈሩት አስተያየቶቻቸው የተለያዩ ሃሳቦችን አጋርተዋል።

Türkei Staatspräsident Recep Tayyip Erdogan Anhebung Mindestlohn
ምስል DHA

ባንትይርጋ አባይነህ «አይ አፍሪካውያን መሪዎች በዋናነት የጦር መሳሪያ በርካሽ ዋጋ ለመግዛት የሚታደሙበት ጉባኤ መሆኑ ያሳዝናል !!» ሲሉ

ስምዖን አብረሃም በበኩላቸው  «እናትዓለም ቱርክ ውለታሽን አንረሳም።» ብለዋል።

ጸጋዬ ፊጋ በበኩላቸው «የአፍሪካ መሪዎች ለተማሪዎቻቸው ኮምፒውተር ወይም እስኪርብቶ ፤ ለህዝቦቻቸው ዳቦ ከመግዛት ይልቅ መቀነታቸውን ፈተው ዘመናዊ መሳሪያ የሚገዙ ሀገር ወዳድ መሪዎች ናቸው።» በማለት ግንኙነቱን የነቀፉበትን መርህ በመተቸት ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

ደመቀ ንጉሱ በበኩላቸው «ለጋራ እድገት እና ብልጽግና የጎለበተ ወዳጅነት እውነት ነው ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት ይህ ነው ።ይበል ያበርታ ነው የሚባለው ።» ሲሉ

መሀመድ አወል ሳሊያ «ረዥም እድሜ ለኤርዶሃን ፤ ይህ ሁሉ የሆነው በፈጣሪ እርዳታ ነው። አ,ውሮጳውያን እና አሜሪካ ይህን ማመን አይችሉም ።በተለይ አሜሪካኖች ሁሉን ነገር አድራጊ ፈጣሪ የሆኑ ይመስላቸዋል። ይህ እንደማይቻል ቱርክ አቅሟን ማሳየት ጀምራለች። » በማለት ቱርክ ሌላ አማራጭ ሀገር ሆና መምጣቷን የገለጹበትን ሃሳብ ሲያሰፍሩ

ሄኖክ ማህ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው « በዚህ  ስበሰባ ላይ አንድ ትልቅ ዉሳኔ ይኖራል በተለይ ለኢምፔሪያሊዝም ሃገሮች የሚተላለፍ መልእክትም አይጠፋም ሌላው በአንድ ለመቆም የጋራ አጀንዳ የሚቀረፅበት ይሆናል ተብሎ ይገመታል ።» ብለዋል።

ሄኖክ ጌታቸውም « የቱርክ-አፍሪካ ትብብር መድረክ ለጋራ እድገትና ብልፅግና የጎለበተ ወዳጅነት...የቱርክን የሁለትዮሽ እድገትና እንደ ሠንሠለት ተያይዞ በህብረት መቆምን ያሳያል።» ብለዋል። እንግዲህ አድማቾች ለዕለቱ ያልነው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችንም ይህንኑ ይመስል ነበር ፤ ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነን ጤና ይስጥልኝ !

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ