1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ የግጭት ማስቆም ጥሪ

ሰኞ፣ ሐምሌ 18 2014

በኢትዮጵያ ውስጥ ተባብሶ የቀጠለው ግጭትና የዜጎች የኑሮ ውድነት ፈተና እልባት ካላገኘ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ኮከስ አስታወቀ፡፡ ኮከሱ በሳምንቱ መጨረሻ ከተወያዬ በኋላ የዜጎችን ሰቆቃ ለማብቃት አካታች፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ብሔራዊ መግባባት ባፋጣኝ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

https://p.dw.com/p/4EboI
Karte Äthiopien Region Tigray DE

የአስራ አንዱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ለመንግስት ያቀረቡት ጥሪ

ኢትዮጵያ ውስጥ ተባብሶ የቀጠለው ግጭትና የዜጎች የኑሮ ውድነት ፈተና እልባት ካላገኘ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ኮከስ አሳሰበ፡፡ የ11 ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ኮከሱ በሳምንቱ መጨረሻ ከተወያየ በኋላ በግጭት ምክንያት የሚፈናቀሉና ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ ያሉትን ዜጎች ሰቆቃ ለማብቃት አካታች፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ብሔራዊ መግባባት በአፋጣኝ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ ኮከሱ በደቡብ ኢትዮጵያ በሰፊው እየተነሱ ነው ላለው የተለያዩ ብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቋል።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የወላታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን)፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ ከፋ ግሪን ፓርቲ፣ ሞቻ እና ሌሎችም የተካተቱበት የ11 የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ ኮከስ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተወያይቶ ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ አሁንም መቋጫ ያልተበጀላቸው ግጭቶች የዜጎችን መረጋጋት አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባቱን ቀጥሏል ፤ ብሏል፡፡

ኮከሱ በመግለጫው እንዳመለከተው፤ ግጭቶቹ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከመዋል ይልቅ በፍጥነት እየተስፋፉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዜጎችን ውሎ መግባት ፈተና ውስጥ ከማስገባትም ባለፈ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር በመዳረጉ የምግብ ዋስትናቸውንም አጠያያቂ አድርጓል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ)ን ወክለው በኮከሱ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ  በሰጡን አስተያየት «መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አልቻለም አልያም አልፈለገም» ብለዋል፡፡

በግጭቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ነፍጥ አንግበው መንግሥትን የሚፋለሙ አካላት እንደመኖራቸው የፖለቲካ መፍትሄው ላይ ኮከሱ ስላስቀመጠው አቅጣጫ የተጠየቁት ፖለቲከኛ ሙላቱ፤

«ወደ ትጭቅ ትግል የገቡትን የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር ቀርቦ ማወያየት የግድ እንደሚሆን» መወያየታቸውን አመልክተዋል፡፡

የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ ኮከሱ ባሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ በሰፊው ስለሚስተዋለው የተለያዩ አደረጃጀቶች ጥያቄም መምከሩን በመግለጫው አስታውቋል፡፡ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ እንደሚሉት፤ «በአከባቢው የሚነሱትን የክልልና የተለያዩ ጥያቄዎችን በኃይል ማስቆም መሞከር ግጭቶችን ሊያባብስ ስለሚችል ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ እንዲያገኙ» ኮከሱ ጠይቋል፡፡

አስቀድሞም በአገር ደረጃ በተዋቀረው የብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳው የ11 ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ ኮከሱ ተስፋፍቷል ላለው ግጭት እልባቱ አካታች፣ ገለልተኛ እና ግልጽ ብሔራዊ መግባባት ባፋጣኝ ማድረግ ነው ብሏል፡፡

አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን መሳሪያ ያስቀመጠ የትኛውም አካል በብሄራዊ ምክክሩ ላይ እንደሚሳተፍ አሳውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የተለያዩ የሰላም አማራጮችን ማየት እንደሚያስፈልግና ለዚያም ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ አንስቷል፡፡ ይሁንና በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ለሚነሳው ግጭት የኃይል እርምጃም በመውሰድ ላይ መሆኑን መንግሥት እያመለከተ ነው፡፡ ከትናንት በስትያ ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌደራል የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው ሰፋ ያለ መግለጫ ከሰኔ 07 እስከ ሐምሌ 07 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደ ዘመቻ ከ153 በላይ «የሽብር ቡድን አባላት» ያላቸው ተደምስሰው፣ ከዘጠኝ መቶ በላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ